Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የተጣጣመ ዕድገት እንዲኖር ምክረ ሐሳብ ቀረበ

በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የተጣጣመ ዕድገት እንዲኖር ምክረ ሐሳብ ቀረበ

ቀን:

ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ባዘጋጁት የኢኮኖሚ መድረክ ላይ፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል የተመጣጠነ ሚዛን ያለው ዕድገት ሊኖር እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ምክረ ሐሳብ አቀረቡ፡፡

ማክሰኞ የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ለግማሽ ቀን በተስተናገደው መድረክ፣ ኢትዮጵያ በምትከተለው የኢኮኖሚ ዕድገት ሞዴልና በመዋቅራዊ ለውጥ ላይ ጥናታዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በዕለቱም ኢትዮጵያ የምትከተላቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና የዕድገት ሞዴሎች በዋናነት ወጥነት እንደሚጎድላቸው ከጥናት አቅራቢዎቹ ተስተጋብቷል፡፡ ከፖሊሲ ወጥነት በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሚታየው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ተፈጥሯዊ ዑደትን ያልተከተለ መሆኑም በምሁራኑ ተመልክቷል፡፡

በመድረኩ ጥናት ካቀረቡ ምሁራን አንዱ የሆኑት ስሜነህ ባሴ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ስትከተላቸው የቆዩ የዕድገት ሞዴሎችን ዳሰሳ አድርገዋል፡፡ በቅርብ ዓመታት አገሪቱ ትከተል የነበረው የልማታዊ ዕድገት፣ ወደ አገር በቀል የኢኮኖሚ ዕድገት መዞሩን ምሁሩ በጥናታቸው ፈትሸዋል፡፡ አገሪቱ ወጥነት ያለው የዕድገት ፖሊሲ በመከተል ሒደት ችግር እንዳለባት ያስቀመጡት ስሜነህ (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህ የዕድገት ሞዴል መለዋወጥ ደግሞ ከፖለቲካ ሥርዓቱ መቀያየር ጋር የሚመጣ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢኮኖሚ ዕድገት ሞዴሎች መካከል ያለው ልዩነት በዋናነት ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት በሚከተሉት መንገድ ላይ ይንፀባረቃል ሲሉ ስሜነህ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ የካፒታሊዝም (ነፃ ገበያ) የኢኮኖሚ ሥርዓት በተለይ የግሉን ዘርፍ የማበረታታት ዝንባሌ አለው ያሉት ምሁሩ፣ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር አካታች ካፒታሊዝም (Inclusive Capitalism) የዕድገት ሞዴል አዋጪ ነው ብለዋል፡፡ የአካታች ካፒታሊዝምን ምንነት ሲያስረዱም፣ ‹‹በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የተመጣጠነ የዕድገት አካሄድ የሚንፀባርቅበት ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ 

ሌላው ጥናት አቅራቢ አረጋ ሹመቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በተለይ የኢትዮጵያ ዕድገት ዑደትንና የኢኮኖሚውን ዋና ዋና መገለጫ ባህሪያት የፈተሸ ግምገማ አቅርበዋል፡፡ ኢኮኖሚው በአሁኑ ጊዜ 40 በመቶ የሚደርስ ዓመታዊ የዋጋ ንረት የሚታይበት መሆኑን ምሁሩ ጠቁመዋል፡፡ ይህ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ከሚሊኒየሙ ወዲህ ባሉ ዓመታት የኢኮኖሚው ዋና መገለጫ ሆኖ መዝለቁንም አረጋ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ 

አያይዘውም የኢትዮጵያን ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳያዎች የዘረዘሩት ምሁሩ፣ ዕድገቱን ‹‹ቅደም ተከተል የጎደለው›› ብለውታል፡፡ በዋናነት በብዙ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ከግብርና ተነስቶ ኢንዱስትሪ እያለ ወደ አገልግሎት ዘርፍ ያድጋል የሚሉት አረጋ (ዶ/ር)፣ ‹‹የኢትዮጵያ ዕድገት ግን ይህን ተፈጥሯዊ የዕድገት ዑደት ባፋለሰ መንገድ ከግብርና ወደ አገልግሎት ዘርፍ ነው ያደገው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሦስቱን  ማለትም የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎችን የዕድገት ልዩነት ለማነፃፀሪያነት አቅርበዋል፡፡

የኢኮኖሚ ውይይት መድረክ ያዘጋጀው የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መድረኩ ለተሳታፊዎች ያለውን ጠቀሜታ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በዛሬው የኢኮኖሚ መድረክ ላይ ተመራቂ ተማሪዎቻችንን እንዲካፈሉ አድርገናል፡፡ እነዚህ ታዳጊ ተማሪዎች አገሪቱ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ስትከተላቸው የቆዩ የኢኮኖሚ ሞዴሎችን አጥርተው እንዲያውቁ ያደርጋል››  በማለት  አረጋ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ መድረኩ የኢኮኖሚ ተማሪዎቻቸውን ከተጨባጩ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ትግበራ ጋር የሚያስተዋውቅ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ተመሳሳይ መድረኮችን ለማዘጋጀት በሰፊው ማቀዱንም ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...