ለጤና የትምህርት መስክ የሚሰጠውን የብቃት መለኪያ አጠቃላይ ምዘና ወይም የመውጫ ፈተና ለመውሰድ ከተቀመጡ 7,818 ተማሪዎች፣ የመጀመሪያውን ዙር ለማለፍ የቻሉት 30 በመቶ ብቻ እንደሆኑ ታወቀ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የግማሽ ዓመት ዕቅድ ሪፖርት አንዳመለከተው፣ በ2014 ዓ.ም. ለጤና ትምህርት ክፍል ተማሪዎች የሚሰጠውን የሙያ ብቃት መለኪያ ፈተና ወይም በተለምዶ ‹‹የመውጫ ፈተና›› ለመውሰድ ከተቀመጡት 7,818 ተማሪዎች ውስጥ የመጀመሪያውን ዙር ፈተና ለማለፍ የቻሉት፣ 2,404 የሚሆኑት ወይም 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የዕቅድና ሀብት ማፈላለግ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ግርማ እንዳስታወቁት፣ በሕክምና ትምህርቶች የምዘና ውጤት የተገኘው ቁጥር የሚያሳያው የጤና ትምህርቱ ጥራት ምን ያህል አደጋ ላይ እንደሆነ ነው፡፡
የመጀመሪያ ዙር የመውጫ ፈተናውን ወስደው ካለፉት ተማሪዎች ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ የሕክምና ትምህርት ፕሮግራም ተመዛኞች ሲሆኑ፣ በተቀሩት የሕክምና ትምህርት ፕሮግራሞች ተመዛኞች ላይ የተመዘገበው ውጤት ግን እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
እንደ ጤና ትምህርት ሁሉ 2,852 የሚደርሱ ተማሪዎች የመጀመሪያ ዙር የሕግ ትምህርት መውጫ ፈተና የወሰዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በመጀመሪያው ዙር የተቀመጠውን የማለፊያ ነጥብ ያሟሉት 1,447 ተማሪዎች ወይም 50 ከመቶ የሚሆኑት ናቸው ተብሏል፡፡ ምንም እንኳን ተመዛኞች የመጀመሪያውን ዙር ፈተና ማለፍ ባይችሉም፣ እስከ ሦስት ዙር የመፈተንና የማለፍ ዕድል የሚሰጣቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበ ሪፖርት ላይ በሰጡት ግብረ መልስ እንዳስታወቁት፣ የትምህርት ጥራቱ በዝርዝር ሲፈተሽ በርካታ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጣው የሰው ኃይል ምን ያህል ብቁ ነው የሚለውን መፈተሽ እንደሚገባ ያስረዱት ሚኒስትር ደኤታው፣ የመውጫ ፈተናዎች በተለይ የሕግ ትምህርት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ2003 ዓ.ም. አንስቶ ተግባራዊ መደረግ እንደ ጀመረ፣ ፈተናው ተግባራዊ መደረጉ በሕግ ትምህርት ክፍሎችም ሆነ በጤና ትምህርት ክፍሎች ላይ ዓይነተኛ ለውጥ እንዳመጣ አስታውቀዋል፡፡
የመውጫ ፈተና በሚወስዱ የመደበኛና የማታ ተማሪዎች መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ምዘናው የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸው፣ ምንም እንኳን ተመሳሳይ ሥርዓተ ትምህርትና ፕሮግራም የሚተገበርባቸው የትምህርት መስኮች ቢሆኑም፣ አተገባበሩ ላይ ያለው ክፍተት ምን ያህል እንደሆነ በመውጫ ፈተናዎቹ የሚገኘው ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
‹‹በአንዳንድ የትምህርት መስኮች ላይ ያለው የተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ፣ የተቀበልናቸው ተማሪዎች በምን ያህል የወረደ ደረጃ እንደ ተቀበልናቸው ማሳያ ነው፤›› ያሉት ሳሙኤል (ዶ/ር)፣ የሕክምና ትምህርት ከዚህ ውስጥ ተጠቃሹ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ለአብነትም በሚድዋይፍ ተማሪዎች ውጤትና በሜዲካል ተማሪዎች ውጤት መካከል ሰፊ ልዩነት እንደሚታይ አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ በሕግ ትምህርት በመደበኛውና መደበኛ ባልሆነው የትምህርት ፕሮግራም በሚከታተሉ ተማሪዎች መካከል ያለው የማለፍ ምጣኔ ማሳያ ከሆኑት ውስጥ፣ የመውጫ ፈተና ውጤት ተጠቃሹ እንደሆነ በቀረበው ግብረ መልስ ተጠቅሷል፡፡
በመሆኑም ይህንን በሁለቱ የትምህርት መስኮች ሲሰጥ የቆየውን አሠራር የሰጠውን ትምህርትና ተሞክሮ በመውሰድ ትምህርት ሚኒስቴር ከ2015 ዓ.ም. መጨረሻ አንስቶ፣ በሁሉም የቅድመ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞች ላይ የመውጫ ፈተና እንደሚሰጥ ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡
እንደ ትምህርት ሚኒስቴር መረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ 30 ሚሊዮን ተማሪዎች፣ 750 ሺሕ መምህራን፣ 47 ሺሕ ትምህርት ቤቶች፣ 45 የመንግሥት፣ እንዲሁም 334 የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይገኛሉ፡፡