Wednesday, October 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት መስፋፋቱና በአዲስ አበባ የነዳጅ እጥረት መከሰቱ ተገለጸ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ በዋናነት ለተሽከርካሪዎች ፍጆታ በውጭ ምንዛሪ የሚገባው ነዳጅ፣ በሕገወጥ መንገድ ለገበያ እየቀረቡ መሆኑና አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች የነዳጅ እጥረት መከሰቱ ተገለጸ፡፡

  ለግብርና በተለይ ለመስኖ ሥራ ለሚውሉ ሞተሮችና ተንቀሳቃሽ የእርሻ መሣሪያዎች፣ እንዲሁም እስከ ጎረቤት አገሮች የተዘረጋው የነዳጅ ኮንትሮባንድ ንግድ ግብይቱን ተፅዕኖ እንዳሳደረበት የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

  የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የነዳጅ ምርት በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ አገሮች ጭምር እየተላከ እንደሚሸጥ ተናግረዋል፡፡ ለግብርና ምርት መሣሪያዎች በተለይ ለውኃ መሳቢያ ሞተሮችና ፓምፖች በሚል ከማደያዎች በጀሪካን እየተቀዳ፣ አየር በአየር እንደሚሸጥም ገልጸዋል፡፡ ይህ ሁሉ በነዳጅ ምርቶች ግብይት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ችግር ነው ብለዋል፡፡

  ‹‹የኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶች ፍጆታ ቤንዚን በቀን እስከ 2.6 ሚሊዮን ሊትር፣ ናፍጣ ዘጠኝ ሚሊዮን ሊትር፣ እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ ከአንድ እስከ ሁለት ሚሊዮን ሊትር ይደርሳል፤›› በማለት፣ የአገሪቱን የነዳጅ ምርቶች ፍጆታ አቶ ታደሰ ጠቁመዋል፡፡ የነዳጅ ምርቶች አቅርቦት በአገር ደረጃ የሚካሄደውም ይህንንና ሌሎች ፍጆታዎችን ታሳቢ በማድረግ ነው ብለዋል፡፡

  ሆኖም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች የነዳጅ አቅርቦቱን የሚያሰናክሉ ግብይቶች እንደሚካሄዱ ነው አቶ ታደሰ የተናገሩት፡፡ የነዳጅ ምርቶች አቅርቦት ላይ እጥረት ተከሰተ ወይም ግብይቱ ተስተጓጉለ ሲባል፣ ፈጥኖ ዕርምጃ መውሰድና መፍትሔ መስጠት ያለበት የአካባቢው አመራርና ንግድ አንቀሳቃሽ ነው ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

  ሪፖርተር የጎላ ችግር ይታይበታል በተባለው የሐረሪ ክልል፣ በተለይ በሐረር ከተማና በዙሪያው ባሉ ገጠር ቀበሌዎች ላይ የሚታየውን የነዳጅ ግብይት ችግር ለማጣራት ጥረት አድርጓል፡፡  

  በሐረር ከተማ ባሉ ነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ የለም ቢባልም፣ በጀሪካንና በበርሜል ምርቱ አየር በአየር ሲሸጥ እንደሚታይ ለሪፖርተር አስተያየት የሰጡ ቅሬታ አቅራቢዎች ይገልጻሉ፡፡ በሐረርና ዙሪያዋ ለመስኖ ፓምፖችና ለሞተሮች በሚል በጀሪካንና በበርሜል ነዳጅ እየቀዱ መቸርቸር እንደተስፋፋም ይናገራሉ፡፡ አገልግሎት በማይሰጡ ትልልቅ ተሽከርካሪዎች ጭምር ነዳጅና ናፍጣ በመቅዳት ለአገልግሎት ተፈላጊ ለሆኑ ባጃጆች በውድ ዋጋ መሸጥ እየተለመደ የመጣ ሕገወጥ አሠራር መሆኑንም፣ ከሐረር ከተማ ነዋሪዎች የተገኘው ቅሬታ ያመላክታል፡፡

  ይህንኑ በተመለከተ አስተያየት የሰጡት የሐረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ፣ ‹‹በሐረርና በአካባቢው በዋናነት የነዳጅ ምርቶች እጥረት የሚከሰተው በአቅርቦትና በፍላጎት አለመጣጣም ሳቢያ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በክልሉ እጥረት በሚፈጥሩ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ቁጥጥር እናደርጋለን፤›› የሚሉት አቶ ሔኖክ፣ ነገር ግን ዋናው ችግር የነዳጅ አቅርቦት ነው ብለዋል፡፡

  አርሶ አደሮችና ለማምረቻ መሣሪያዎች ነዳጅ የሚፈልጉ ግለሰቦች ከወረዳ ፈቃድ በመውሰድ በሕጋዊ መንገድ ወስደው የነዳጅ ምርቶች እንዲገበዩ ይደረጋል ያሉት አቶ ሔኖክ፣ ‹‹ከዚያ ውጪ ኮንትሮባንድና የአየር በአየር ግብይትን እየተቆጣጠርን ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች