በምሥረታ ሒደት ላይ የሚገኘውና ውግንናውን ለአፍሪካ አገሮች ያደርጋል የተባለው ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ ኦፍ አፍሪካ (ጂቲኤንኤ) የተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ 30 ሚሊዮን ብር የሊዝ ክፍያ በመፈጸም፣ ከአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር መሬት መረከቡን አስታወቀ፡፡
መቀመጫው በአዲስ አበባ የሚሆነው ይህ ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከከተማ አስተዳደሩ የተቀበለው 5,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ ለቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና መሥርያ ቤት ሕንፃ ግንባታ የሚውል መሆኑን የጂቲኤንኤ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋዜጠኛ ግሩም ጫላ ተናግሯል፡፡
ጂቲኤንኤ እስካሁን ያከናወናቸውን ሥራዎች አስመልክቶ የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በተሰጠው መግለጫ፣ የቴሌቪዥን ጣቢያው የፕሮጀክት ፕሮፖዛሉን ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ለከተማ አስተዳደሩ እንዳቀረበና የከተማው ካቢኔ ውይይት አድርጎ ፈቃድ መስጠቱን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት የከተማ አስተዳደሩ ለ99 ዓመት በሚቆይ ሊዝ አንድ ካሬ ሜትር መሬት በ40,000 ብር ገደማ ዋጋ ለጂቲኤንኤ ማስረከቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ቴሌቪዥን ጣቢያውም የአጠቃላይ ክፍያውን 15 በመቶ ወይም 30 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡
ከከተማ አስተዳደሩ በተገኘው መሬት ላይ 63 ወለል ያለው ሕንፃ ለመገንባት ዕቅድ እንደተያዘ የተናገረው ጋዜጠኛ ግሩም፣ ሕንፃው ከቴሌቪዥኑ ዋና መሥሪያ ቤትነት ባሻገር የንግድ ማዕከላትና ሞል፣ እንዲሁም በሕንፃው መጨረሻ ላይ ለመኖሪያ የሚሆኑ አፓርትመንቶችን እንደሚይዝ አብራርቷል፡፡ ሕንፃው እነዚህን አገልግሎቶች እንዲይዝ የታቀደው ቴሌቪዥን ጣቢያው የሚያስፈልገውን የፋይናንስ አቅም በራሱ ለመሸፈን እንዲችልና ጣልቃ ገብነት እንዳይኖርበት በመታሰቡ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አብራርቷል፡፡
የዋና መሥሪያ ቤቱ ሕንፃ የሚኖረው አገልግሎት ከቴሌቪዥን ጣቢያነት የዘለለ በመሆኑ፣ የጂቲኤንኤ የንግድ ፈቃድ ከአንድ በላይ የንግድ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ሆኖ እንደወጣ ለሪፖርተር የገለጸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ሕንፃው ሲጠናቀቅ የቴሌቪዥን ጣቢያውንና ሕንፃው የሚያስተዳደሩት ቦርዶች የተለያዩ እንደሚሆኑ ተናግሯል፡፡
ጂቲኤንኤ የመጀመሪያ የምሥረታ ምዕራፉን አጠናቆ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ እየተሸጋገረ ስለመሆኑ በመግለጫው ላይ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የማግኘት፣ የንግድ ፈቃድ ምዝገባ፣ ባለድርሻ አካላትን የማሰባሰብና ለሕንፃ ግንባታ የሚሆን መሬት የማግኘት ሥራዎች መከናወናቸው ታውቋል፡፡ በቀጣዩ ምዕራፍ ደግሞ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ፈቃድ የማግኘትና የፕሮጀክት ቢሮ ለመክፈት እንደሚሠራ ዋና ሥራ አስፈጻሚው በመግለጫው ላይ አስረድቷል፡፡
በምሥረታ ላይ ያለው ይሄ የቴሌቪዥን ጣቢያ ‹‹ከአፍሪካ ወደ ዓለም›› በሚል ሐሳብ እንደሚንቀሳቀስ የተናገረው ጋዜጠኛ ግሩም፣ ‹‹ዓላማው የምዕራባውያንን ሚዲያ መጋፋት ሳይሆን፣ የአፍሪካን ጉዳዮችና ፈተናዎች በአፍሪካውያን ዕይታ ማቅረብ ነው፤›› ብሏል፡፡ ጂቲኤንኤ ከማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ማንነት ላይ መሠረት ያደረጉ አስተሳሰቦች ነፃ ሆኖ ለአፍሪካዊ አገሮችና ለአኅጉሪቷ ውግንናን ይዞ ይሠራልም ተብሏል፡፡
ቴሌቪዥን ጣቢያው እንደ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ባሉ ከ13 በላይ የአፍሪካ አገሮች፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በኒውዮርክ፣ በቤጂንግና በለንደን ወኪሎች እንደሚኖሩት ተነግሯል፡፡
ጂቲኤንኤ ለምሥረታ የሚያስፈልገው መነሻ ካፒታል ሦስት ቢሊዮን ብር እንደሆነ የተናገረው ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይኼ ካፒታል እስከ አምስት ቢሊዮን ብር ሊሰፋ ይችላል ብሏል፡፡ ሊገነባ የታሰበው የዋና መሥሪያ ቤቱ ሕንፃ በመጀመሪያ በ25 ወለሎች እንዲኖሩት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የጣቢያው የፋይንናስ አቅም የማግኘት ሁኔታ አስተማማኝ እየሆነ ሲመጣ እንዲሁም አጋሮች ሲበዙ ዕቅዱ ወደ 63 ወለል ማደጉን ዋና ሥራ አስፈጻሚው በመግለጫው ላይ ተናግሯል፡፡
ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ይኖረዋል የተባለውን ይኼንን የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም የሚያስፈልገው የፋይናንስ አቅም በአብዛኛው የሚገኘው በውጭ ካሉ ባለድርሻ አካላት እንደሆነ፣ በአገር ውስጥም ድርሻ የሚኖራቸው አካላት እንደሚኖሩ ተጠቁሟል፡፡ ከዚህም ባሻገር የጂቲኤንኤ ድርሻ ለሽያጭ ይቀርባል ተብሏል፡፡