Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ኢኮኖሚውን ለማነቃቃትና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመታደግ የተደረገው የብድር ስምምነት

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ የሚታየውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመታደግና በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የአፍሪካ ኤክስፐርት ባንክ (አፍሪ ኤግዚም ባንክ) ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ለማቅረብ የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር ተፈራረመ፡፡

  በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና በአፍሪ ኤግዚም ባንክ መካከል ትናንት የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲፈረም እንደተገለጸው፣ ስምምነቱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደፊት በሚያራምዱ የንግድና የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ነው፡፡

  የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሊያሳድጉ ለሚችሉ የንግድና ኢንቨስትመት ክንውኖች የሚያስፈልገውን ፋይናንስ አፍሪ ኢግዚም ባንክ ከብድር የሚቀርብ ሲሆን፣ በመጀመርያው ምዕራፍ የሚሰጠው ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር በኢትዮጵያ ባንኮች በኩል ለተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ለብድር የሚውል ነው፡፡  

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ እንደገለጹት ደግሞ፣ ከአፍሪ ኤግዚም ባንክ ጋር የሚቀረፀው የሁለትዮሽ ትብብር ስምምነት ለማኅበረሰብ አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት፣ የሥራ ፈጠራና የድህነት ቅነሳ ላይ አስተዋጽኦቸው ከፍ ላሉ የንግድና ኢንዱስትሪ መስኮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ነው፡፡

  ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የአገር በቀል ሪፎርም ዕውን እንዲሆንና የኢትዮጵያ ልማት የዕድገት ጉዞን የሚደግፍ በመሆኑ፣ ከባንኩ ጋር የተደረገው ስምምነት በእጅጉ ዋጋ የምንሰጠው ነው በማለት የስምምነቱን ጠቃሚነት ገዥው ገልጸዋል፡፡

  ወደዚህ ስምምነት የተገባበትን ሁኔታ በማስመልከት ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት ይናገር (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በተለያዩ የንግድና የኢቨስትመንት ሥራዎች ውስጥ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚቻል ከገለጹ በኋላ፣ ውይይቶች ሲደረጉ ቆይተው አሁን ለተደረገው ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል፡፡

  ከባንኩ የሚገኘው ብድርም ለመንግሥትና ለግል ባንኮች ተሰጥቶ፣ እነሱም ለተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች የሚያበድሩት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

  የአፍሪ ኤግዚም ባንክ ከሚሰጠው ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ሌላ የአፍሪካ የእርስ በርስ ንግድን ለማበረታታት፣ እንዲሁም የቦርደር ንግድን የሚያበረታቱ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችሉ አንቀጾች በስምምነቱ ውስጥ መካተቱን ይናገር (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

  ባንኩ የአፍሪካ ባንክ እንደመሆኑ መጠን የአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን የሚያበረታታ እንደመሆኑ፣ ኢትዮጵያም ትልቅ ቦታ እንዲኖራትና የበኩሏን እንድትጫወት ይህ ስምምነት አጋዥ እንደሚሆንም ይናገር (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

  ባንኩ ኢትዮጵን በሙሉ አቅሙ እንዲደግፍም የአፍሪ ኤግዚም ባንክ ወኪል ቅርጫፉን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከፍት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም በስምምነት ሰነዱ ውስጥ መካተቱ ታውቋል፡፡

  በጣም ወሳኝ የሆኑ ምርቶችን ከውጭ ለማምጣት የሚያስችለውን ፋይናንስ ለማቅረብ አፍሪ ኤግዚም ባንክ የተስማማ ስለመሆኑ የገለጹት ይናገር (ዶ/ር)፣ ግብርናን፣ የማኑፋክቸሪንግና ሌሎችንም ዘርፎችን ለማሳደግ ወሳኝ የሚባሉ የፍጆታና የጥሬ ዕቃዎች ግዥ የሚውል የውጭ ምንዛሪ ለማቅረብም መስማማቱን ተናግረዋል፡፡

  ይህ ስምምነት በርካታና አዳዲስ አሠራሮችን ጭምር ለመተግበር የሚያስችል መሆኑን፣ ስምምነቱን አስመልክቶ የአፍሪካ ኤግዚም ባንክ ፕሬዚዳንትና ቦርድ ሊቀመንበር ሚስተር ቤኔዴክት አርማህ (ፕሮፌሰር) ካደረጉት ንግግር መገንዘብ ተችሏል፡፡ ወደዚህ ስምምነት የተገባበትን ዋነኛ ምክንያት ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ውስጥም ሆና ያሳቸው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና አጠቃላይ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በተጨባጭ እየታየ በመሆኑ፣ ይህንን ማገዝ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ብለዋል፡፡

  በአፍሪካ ኤግዚም ባንክና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መካከል ተግባራዊ የሚሆነው የትብብር ስምምነት ለተመረጡ የግሉ ዘርፍ ተቋማትና ንግድ ባንኮች፣ እንዲሁም የወጪና ገቢ ንግድ ሥራዎችን የማቀላጠፍ ተግባራት ላይ የሚውል የብድር አቅርቦት መስመሮችን የሚከፍት እንደሆነ የገለጹት ይናገር (ዶ/ር)፣ ስምምነቱ የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ከአፍሪ ኤግዚም ባንክ የቀረቡ የአገልግሎት መርሐ ግብሮችን በመጠቀም የአፍሪ ኤግዚም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍን ለማግኘት የሚያስችል እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡  

  ይህ ስምምነት አዳዲስ አሠራሮችን ይዞ የሚመጣ ስለመሆኑ የሚጠቁመው የማስተር ቤኔዴክት፣ ስምምነቱ ከሚያካትታቸው ተግባራት መካከል ወሳኝ የሚባሉ የቢዝነስ ዘርፎችን በተጨባጭ የሚያግዝ ነው፡፡

  ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ከሌሎች የተመረጡ ባንኮች ጋር አብረን መሥራታችን የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለመጨመር፣ ውጤታማና ምርታማ ዘርፎችን የማሻሻል፣ በተለይም አነስተኛ አምራቾችን እንደ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የቱሪዝምና መሰል ዘርፎችን ለማሻሻል ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል፡፡

  እንዲሁም እጀግ ወሳኝ የሆነውን የኢትዮጵያን የገቢ ንግድ ለመደገፍ ይህ ስምምነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡ የፋይናንሱንና አጠቃላይ የኮርፖሬት ዘርፉን የሚያጠናክር ተግባራትን ያከናውናሉ ብለው እንደሚያምኑም ገልጸው፣ ስምምነቱ ቀጣይነት ላለው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገትም እንደ ሞተር የሚሆን ነው ብለዋል፡፡

  የአፍሪ ኤግዚም ባንክ ፋይናንስ የሚያደርጋቸውና የማማከር አገልግሎት የሚሰጥባቸው ዘርፎች የኢትዮጵያን ዕድገት በተለይም በኢንዱስትሪውና በተለያዩ ንግዶች ኢትዮጵያ ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም በእጅጉ የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትንም ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚተገበር ስምምነት ስለመሆኑ በዕለቱ ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

  የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት አዲስ አሠራርን ይዞ ስለሚመጣ፣ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ አገሮች ወደ ተሻለ ጉዞ ይዞ የሚሄድ መሆኑንም ያስታወሱት ማስተር ቤኔዴክት፣ ይህንን የንግድ ቀጣና ስምምነት ዕውን ለማድረግ ብዙ ሥራ የሚጠበቅ መሆኑንና ባንኩም የአፍሪካን የእርስ በርስ ንግድ እንዲቀላጠፍ ዕገዛ እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡

  የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ለአፍሪካውያን ወሳኝ ጉዳይ ስለመሆኑ ያመላከቱት ሚስተር ቤኔዴክት የአፍሪካ ገበያ መፈጠር ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አጎዋ የአፍሪካ አነስተኛ አምራቾች አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ዕድል የፈጠረ ቢሆንም፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት በራሱ ለ1.2 ቢሊዮን ሕዝብ የሥራ ዕድልና ገበያ የሚፈጥር፣ የወጪ ንግዱን የሚያሳድግ በመሆኑ ትኩረት የሚያስፈልገው ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም አፍሪካ ኤግዚም ባንክም ኢትዮጵያንና ሌሎች አፍሪካ አገሮች፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ስምምነቱን መሠረት በማድረግ የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴ የሚያግዝ ሲሆን፣ እንዲህ ያሉ ስምመነቶች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዙ ናቸውም ብለዋል፡፡ 

  ‹‹ጠንካራና የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ቀጣይነት ያለውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማረጋገጥ በእጅጉ አስፈላጊ በመሆኑም፣ ከአፍሪካ የንግድ ባንኮች ጋር ዘላቂ የሆኑ የትብብር ስምምነቶችን ለማድረግ አስበን እየሠራንበት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይህም የባንኩን አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ሁነኛ መንገድ መሆኑ ታምኖበት ከበርካታ የኢትዮጵያ የንግድ ባንኮች ጋር በጋራ ለመሥራት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡  

  በዕለቱ የተደረገው ስምምነት በርካታ አንቀጾችን ያካተተ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል  የኢትዮጵያ ባንኮች ከሌሎች የአፍሪካ ባንኮች ጋር እንደሚሠሩና ዕገዛ የሚያገኙባቸውን መንገዶች አንዱ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ አኳያ ፕሬዚዳንቱ እንደ ምሳሌ የጠቀሱት የአፍሪ ኤግዚም ባንክ ‹‹ሌተር ኦፍ ክሬዲት›› መስመሮች የኢትዮጵያ ባንኮች እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የገቢ ዕቃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ፣ እንዲሁም የወጪ ንግድ ገቢያቸውን ሊያሳድግ የሚችሉ ሁኔታዎችን የሚያመቻች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ለንግድ እንቅስቃሴው ጠቃሚ ይሆናሉ ተብለው እንዲተገበሩ ከሚጠበቁት መካከል፣ በጥሬ ገንዘብ የሚደረጉ ግብዓቶች ለድንበር ተሻጋሪ ንግዶች ማነቆ በመሆናቸው፣ ይህንን ሊፈታ የሚችል አሠራር መተግበር አስፈላጊ ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡

  በዚህ ረገድ ሚስተር ቤኔዴክት በአፍሪካ ኤግዚም ባንክ አማካይነት የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓትን በመጠቀም፣ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ የንግዶች ሥጋት የሆኑ አሠራሮች እንዲወገዱ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋት የስምምነቱ አካል ነው፡፡

  የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት ሲስተም በመጠቀሙ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ክፍያቸውን በብር ጭምር እንዲጠቀሙ፣ በዚያኛው ያለው የንግድ ሸሪክም በራሱ ገንዘብ የንግድ ልውውጡን የሚያደርግበት አሠራር የሚፈጠር ስለመሆኑም ከተደገረው ንግግር ለመረዳት ተችሏል፡፡ ድንበር ተሻጋሪ ንግድን በእጅጉ የሚሳድጉ የክፍያ ሥርዓት የሚያረጋግጥ፣ የአገር ውስጥ የመገበያያ ገንዘብን ጥንካሬ የሚያሳድጉና ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎች የሚሠሩ ሲሆን፣ ለዚህም የኢትዮጵያ ባንኮች መረጃ የሚያገኙበት ዕድል በባንኩ ስለመዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡

  እንዲህ ያለውን አገልግሎት ዳር ለማድረስም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፓን አፍሪካ ‹‹ፔይመንት ኤንድ ሴትልመንት ሲስተም›› እና በሌሎች ማዕቀፎች አባል እንዲሆን እንጠብቃለን በማለት የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ በማጠቃለያቸው ላይ በዕለቱ በተደረገው ስምምነት መሠረት ከብሔራዊ ባንክ፣ ከንግድ ባንኮችና ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ የሚሠሩት ሥራ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነቱን ከግብ ለማድረስ የሚያስችላቸው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በበኩላቸው፣ በዕለቱ የተደረሰውን የጋራ ትብብር ከግምት በማስገባት፣ የጋራ መግባቢያ ስምምነት መርሆዎችን ለማሳካትና ውጤታማ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

  አያይዘውም የትግበራ መርሐ ግብሩ ለሦስት ዓመታት የፀና እንደመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት በመሥራት ሊገኝ የሚችለውን የመጨረሻ ውጤትና ጥቅም እናሳካለን ብለዋል፡፡

  በተለይ አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሪ ችግር ከማቃለል አኳያ ያለውን ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ይህ ስምምነት እንዲፈጸም ትኩረት ተሰጥቶት ሲሠራበት እንደነበር የገለጹት ይናገር (ዶ/ር)፣ ከባንኩ የሚገኘውን ብድር የግልና የመንግሥት ባንኮች ካገኙ ኢኮኖሚው ይበልጥ እንዲነቃቃ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

  አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሪ ከማቃለል አኳያ ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ከአፍሪ ኤግዚም ባንክና ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ግንኙነታቸው ያን ያህል ያልነበረ ሆኖ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ግን ይህንን ግንኙነት ለማጠናከር በሁለቱም ወገን በኩል ቁርጠኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡

  አፍሪ ኤግዚም ባንክን ከመሠረቱት አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን፣ በዚህ ባንክ ውስጥ ባለድርሻም ናት፡፡

  በብሔራዊ ባንክና በአፍሪካ ኤግዚም ባንክ መካከል ትናንት ስምምነቱ ሲፈረም የመንግሥትና የግል ባንኮች ፕሬዚዳንቶችና ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡      

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች