Wednesday, February 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ሥር ነቀል ለውጥ ላይ ነኝ አለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • 24 ሰዓት የሚሠራ የሳተላይት ቴሌቪዥን እጀምራለሁ ብሏል

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ወቅቱን የሚመጥን ሥር ነቀል የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና የግሉን ዘርፍ በማጠናከር በኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ እንደሆነ አስውቋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ከረዥም ጊዜ በኋላ በእንቅስቃሴው ዙሪያ ባወጣው መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት ንግድ ምክር ቤቱ የተጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ለመወጣት ያስችለው ዘንድ የአገልግሎት ብቃቱንና የንግዱን ኅብረተሰብ የመወከል አቅሙን ለማሳደግ ሥር ነቀል ለውጦችን በማድረግ ላይ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

ከመንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠርና በመቀራረብ በትልልቅና አንኳር አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቀጣይነት ያለው እንቅስቃሴ ለማድረግ በዝግጅት እንደሚገኝ ገልጾ፣ በቅርቡ የተለያዩ ዕርምጃዎችን መውሰዱን አሳውቋል፡፡

ከዚህም ውስጥ በቅርቡ ንግድ ምክር ቤቱ ወቅቱን የሚመጥን የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ስለመገኘቱ ጠቅሷል፡፡ እንደ ንግድ ምክር ቤቱ መግለጫ፣ የምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ተቋማዊ ግንባታ ላይ ያነጣጠሩ ሪፎርሞችን፣ ማለትም ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ስለሚኖሩ ግንኙነቶችና ትብብር፣ አባላትን ማዕከል ባደረገ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ ዘመናዊ የሰው ኃይል ማኔጅመንት በመሳሰሉ ልዩ ትኩረት በሚገባቸው ስትራቴጂያዊና ተቋማዊ ለውጥ ዙሪያ 23 አንኳር ነጥቦችን ለይቶ በምክር ቤቱ ውስጥ ያሉ አሠራሮች እንዲሻሻሉ የማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግሯል፡፡

‹‹በአጠቃላይ የምክር ቤቱ አሠራር ዘመናዊና የአባላትን ፍላጎት ያማከለ እንዲሆን የውስጥ አሠራር ማሻሻያ ለማድረግ አባላቱን ሊወክሉ የሚችሉ የምክር ቤታችን የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮች በተጠናከረ መንገድ እንዲሳተፉ በማድረግ ለውጡ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል፤›› የሚለው መግለጫው፣ አላሠራ ያሉ አሠራሮችም እንዲስተካከሉና አንዳንዶቹም እንዲሻሩ ስለመደረጋቸው ያመለክታል፡፡

እንቅስቃሴዬን በተለያየ መንገድ እያደረኩ ነው የሚለው የአዲስ አበባ ንግድ ምከር ቤት፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ፣  የንግዱን ኅብረተሰብ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚያዊ ዕድገት ድርሻውን ከፍ ለማድረግና ጠንካራ የቢዝነስ ዘርፍ እንዲፈጠር በሚል በተመረጡ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ለመንግሥት የአምስት ዓመት የምክረ ሐሳብ ሰነድ ማቅረቡንም አስታውሷል፡፡

‹‹በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ጥምረት (PPP) በሚባለው የዘመናችን የትብብር ፍልስፍና በፅኑ የሚያምነው ምክር ቤታችን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በተለያዩ የማኅበረ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ስትራቴጂ አጋርነት ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ ነው›› ብሏል፡፡

‹‹ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት እንዲያስችላቸው የዳያስፖራ ዴስክ በማቋቋም ዕገዛችንን ቀጥለናል፤›› የሚለው  መግለጫ፣ ይህ አገልግሎት ዳያስፖራዎች ባሉበት አገርም በሚገኙ አጋር ምክር ቤቶች በኩል አገልግሎት እንዲያገኙ ተገቢው አሠራር ስለመነደፉ አስታውሷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ለተሰማራው ኅብረተሰብ ወቅታዊና አስተማማኝ መረጃ የሚቀርብበት የራሱን የ24 ሰዓት የሳተላይት ቴሌቪዥንና የኤፍኤም ራዲዮ ጣቢያ ለማቋቋም የሚያስችል የአዋጪነት ጥናት አስጠንቶ ለተግባራዊነቱ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ መግለጫው አመልከቷል፡፡

ይህ ጣቢያ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረውና የአገራችን ላኪዎች ምርታቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማስተዋወቅ እንዲያስችል ማድረግ ከያዘው የሪፎርም ሥራ አንዱ አካል እንደሆነም ጠቁሟል፡፡

የግሉ ዘርፍ ዋነኛ የኢኮኖሚ ሞተር ሆኖ እንዲቀጥልም ከኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንዲሁም ከክልልና ከከተማ ምክር ቤቶች ጋር በአንድነት በመምከር የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ለመሥራት ማቀዱንም በዚሁ መግለጫው አመልክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ በበርካታ የልማት ሥራዎችና በተለያዩ ወቅቶች በዜጎችና በአገር ላይ ችግር ሲገጥምም የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን በመግለጽ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለተጎዱና በጦርነት ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎች፣ ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ በማድረግ ወገናዊ አጋርነቱን አሳይቷል ብሏል፡፡

 በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች 3.2 ሚሊዮን ብር፣ በተመሳሳይ ምክር ቤቱ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚውል 2.5 ሚሊዮን ብር በመለገስ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ስለመወጣቱም ገልጿል፡፡ በቀጣይም በጦርነቱ ወቅት የወደሙትን አካባቢዎች መልሶ በማቋቋም ድጋፍ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

 

 ምክር ቤቱ ስላለው እንቅስቃሴ ቢገልጽም፣ በአባላት ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ የሚፈጥረውና ከሕግ ውጪ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ሳያካሂድ ሦስት ዓመታት ስለቆየበት ምክንያት ምንም የተነፈሰው ነገር የለም፡፡

በቅርቡ በምክር ቤቱ ጸሐፊና በቦርዱ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባትና የዋና ጸሐፊውን ስንብትም ይሁን ተያይዞ  የተነሱ ጉዳዮች ላይ መግለጫው ምንም አላነሳም፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች