ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገባውን ሙሉ በሙሉ በመተካት ራሷን ከቻለችባቸው የኢንዱስትሪ ምርቶች አንዱ ሲሚንቶ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሦስት ዓመታት ወዲህ ሄድ መለስ የሚለው የምርት እጥረት እየሰፋ ሄዶ፣ በአሁኑ ጊዜ በሲሚንቶ ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለው ክፍተት ከአምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ደርሷል፡፡ አገሪቱ የምትፈልገው ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም. አጠቃላይ ምርቱ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነበር፡፡ በእርግጥ የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ ማቋረጥም ከምርቱ ወደ 1.2 ሚሊዮን ኩንታል ቀንሷል፡፡
መንግሥት አንድ ጊዜ ‹‹የመለዋወጫ ችግር ነው፣ ደላሎች የፈጠሩት ሰው ሠራሽ እጥረት ነው፣ የኢኮኖሚ አሻጥር ነው›› ሲል ከቆየ በኋላ ሁለት መመርያዎችን ለማፅደቅ፣ የመጨረሻ ውይይት ከሳምንት በፊት ተደርጎባቸዋል፡፡
አንደኛው ረቂቅ መመርያ በማዕድን ሚኒስቴር የተዘጋጀ ሲሆን፣ ‹‹የሲሚንቶ ምርትና ጥራት ቁጥጥር›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተዘጋጀው ሌላኛው ረቂቅ መመርያ ደግሞ፣ ‹‹የሲሚንቶ አቅርቦትና ግብይት›› የሚል ባለ19 አንቀጽ መመርያ ነው፡፡
ከዋና ዋና ለውጦችና በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ካልተወደዱት ውስጥ፣ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች የምርቶቻቸውን 30 በመቶ ፋብሪካው ባለበት አካባቢ ለሚገኙ ወጣቶች እንዲሰጡ፣ የተረፈውን ደግሞ በዋናነት ለመንግሥት ፕሮጀክቶችና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንዲሸጡ መገደዳቸው ነው፡፡
‹‹ለገበያ የምንሸጠው ሲሚንቶ በጣም ያነሰ ነው የሚሆነው፡፡ ኤጀንቶቻችን የነበሩት ከገበያ የሚወጡ ከሆነ ዞሮ ዞሮ ግን አብዛኛው የአካባቢ ወጣት 30 በመቶ ሙሉ ስለማይጠቀም ከእነሱ ወደ መግዛት ይዞራሉ፤›› በማለት በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ የአንድ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹አዲሶቹ መመርያዎች ከፀደቁ ትርፋችን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ክልሎች መቶ በመቶ ምርቱ ከክልላችን እንዳይወጣ ብለው የነበረ ቢሆንም፣ ሚኒስቴሮቹ ግን 30 በመቶ አደረጉት፤›› ብለዋል፡፡
ሌላው ትልቅ ለውጥ ደግሞ የሲሚንቶ አከፋፋዮችንና ቸርቻሪዎችን ይመለከታል፡፡ ከአከፋፋዮች ሲሚንቶ ከፋብሪካ ለመግዛት 30 ሚሊዮን ብር በዝግ አካውንት ማስያዝ ያለባቸው ሲሆን፣ ለቸርቻሪዎች አምስት ሚሊዮን ብር ነው፡፡ የሚገዙት ሲሚንቶም 80 በመቶ በብትን ሲሆን፣ ቀሪው ብቻ ነው የታሸገው፡፡ በተጨማሪም ሁሉም ሽያጭ በደረሰኝ መከናወን ይኖርበታል ይላል፡፡
ሦስተኛው አከራካሪና ትልቁ ለውጥ ደግሞ የሲሚንቶ ጥሬ ዕቃ ማውጫ ቦታዎችን (Quarries) ይመለከታል፡፡ ከላይምስቶን (Limestone) ውጭ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የራሳቸው ኳሪ ባለቤት መሆን እንደማይችሉ፣ ሌሎች ጥሬ ዕቃዎች በሙሉ በአካባቢው ወጣቶች ብቻ መውጣትና መቅረብ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡
በአጠቃላይ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ለወጣቶች ብቻ ከተሰጠ ዋጋውን እንደፈለጉ ይሰቅሉታል፡፡ ‹‹ይህ ከዚህ በፊትም በኦሮሚያ ክልል ተሞክሮ ያልተሳካ ዕርምጃ ነው፤›› ይላሉ ሥራ አስኪያጁ፡፡ ከሁለቱም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
መመርያዎችን ለማዘጋጀት በተደረጉት ጥናቶች ውስጥ የተሳተፉ አንድ ከፍተኛ የሲሚንቶ ባለሙያ ግን፣ ረቂቅ መመርያዎቹ የተቀረፁት የሲሚንቶ ዘርፉን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ነው ይላሉ፡፡
‹‹30 በመቶ ምርት ፋብሪካው ላለበት አካባቢ እንዲሰጥ መባሉ እንዲያውም ያንሳል፡፡ ምክንያቱም 90 በመቶ የሲሚንቶ ግብዓት ከዚያ አካባቢ እየወጣ ማኅበረሰቡና ወጣቶች የጥሬ ዕቃ ዋጋን እንደፈለጉ እንዳይጨምሩ፣ መንግሥት ዋጋዎችን በየስድስት ወራት ራሱ ሊያስተካከል ይችላል፤›› ይላሉ ባለሙያው፡፡
ይሁን እንጂ የሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር በበኩሉ ዘርፉ ወደ ባሰ ውስብስብ ችግር ሊገባ እንደሚችል ሥጋቱን ይገልጻል፡፡
በተለይ ያለፈውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ በተቋቋመው አዲሱ ካቢኔም፣ የመንግሥት ተቋማት አወቃቀር ውስጥ የሲሚንቶ ምርትና ቁጥጥር ከቀድሞው ንግድና ኢንዱስትሪ ወጥቶ ወደ ማዕድን ሚኒስቴር ሄዷል፡፡ በተለይ ከሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የዘርፉን ችግር በጥናትና በድጋፍ ሲፈታ የቆየው የኬሚካልና የግንባታ ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በአዲሱ ካቢኔ በመፍረሱ፣ ከአሁኑ ከፍተኛ ክፍተት መፍጠሩ እየታየ ነው፡፡
‹‹በመጀመርያ ተቋማዊ ርክክቡ ጤናማ ያልሆነና እስካሁንም በቅጡ ያልተከናወነ ነው፡፡ ሁለተኛ ማዕድን ሚኒስቴር ከዜሮ ስለሚጀምር ስለሲሚንቶ ዘርፉ በደንብ ለማወቅ ቢያንስ ሦስት ዓመት ይፈጅበታል፤›› ይላሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የማኅበሩ ተወካይ፡፡ ‹‹የማዕድንም ሆነ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴሮች ስለሲሚንቶ ዘርፍ ዕውቀት የላቸውም፡፡ በአጭሩ በሲሚንቶ ላይ ከባድ የግል ፍላጎቶች ስላሉ ነው ተጠሪነቱ የተቀየረው፡፡ በአጠቃላይ የሲሚንቶ ዘርፍ ችግሮች እንዲባባሱ መንግሥት የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች መስተካከል አለባቸው፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡
አሁን ለመፍረስ በሒደት ውስጥ ባለው ኢንስቲትዩት የሲሚንቶ ልማት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ስመኝ ደጉ በበኩላቸው፣ የሲሚንቶ እጥረት በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው አዳዲስ ፋብሪካዎች ማምረት ሲጀምሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
‹‹የግንባታ ዘርፉ በፍጥነት ሲያድግ ስለነበር ከሳምንት በፊት ከተቋቋሙት አብዛኞቹ የአገሪቱ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች አቅም በላይ ፍላጎት ጨምሯል፡፡ ይኼንን ከፍተኛ ፍላጎት አሟልቶ ወደ ጎረቤት አገሮችም ለመላክ በሒደት ውስጥ ያሉት አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ ኢንቨስትመንቶችና የነባሮች ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ማለቅ አለባቸው፤›› ይላሉ አቶ ስመኝ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከአምስት የማያንሱ አዳዲስ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የተጀመሩ ሲሆን፣ የአገሪቱን የሲሚንቶ ምርት በእጥፍ ያሳድጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡