Saturday, March 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያን የፈተነው የኑሮ ውድነት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በምትገኘው በሆለታ ያለው መሠረታዊ የሸቀጦች ዋጋ ኅብረተሰቡን የሚያማርር መሆኑን ወ/ሮ ዘውድነሽ ላቀው ይናገራሉ፡፡ የደብረዘይት/ቢሾፍቱ የገበያ ሁኔታ የማይተነበይ እንደሆነባት በአነስተኛ የባልትና ምርቶች ማዘጋጀትና መሸጥ ሥራ ላይ የተሰማራችው ውባለም ወልደየስም የኑሮ ውድነቱን ታነሳለች፡፡ ከአዲስ አበባ ብዙም ሳንርቅ የገበያው ሁኔታ ምን ይመስላል ብለን በስልክ ያነጋገርነው በአዳማ/ናዝሬት በድለላ ሥራ የተሰማራው መሐመድ አብዱረዛቅ ደግሞ እህል በመምጫውና በመርከሻው ሰዓት በከተማዋ ዋጋው ሊቀመስ አለመቻን ይገልጻል፡፡

የሐረር ከተማው አዲስ ከፋለ ‹‹የምንወደው ነገር›› የሚለውን የጫት ሰሞነኛ ዋጋ በመጥቀስ የአካባቢው ሕዝብ ራስ ምታት የሆኑ የሸቀጦች ዋጋ መናሩን ነግሮናል፡፡ ዳንኤል በላቸው ከጅግጅጋ ነዳጅ በኮንትሮባንድ እየተቀዳ ወደ ውጭ አገር የሚሰደድባት የሚላት ከተማው በኑሮ ውድነት መወጠሯን ጠቁሞናል፡፡ ለሪፖርተር ሐሳባቸውን የሰጡ ሸማቾችና ነጋዴዎችም የኑሮ ውድነት በአንድ አካባቢ የተወሰነ ሳይሆን በሁሉም ቦታ ተፅዕኖው የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሐሳባቸውን ካጋሩን አንዱ የሆነው የባህር ዳሩ ነጋዴ በላይ አሁነው ከውጥ ከምንዛሪ እጥረትም ሆነ ከሌላ ነገር ጋር ግንኙነት የሌላቸው በባህር ዳር አካባቢ የሚመረቱ ምርቶችንም በገበያ ማግኘት ችግር እንደሆነ ገልጾልናል፡፡

የኑሮ ውድነቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ምን እንደሚመስል ሪፖርተር  ከተለያዩ ነጋዴዎችና ሸማቾች አስተያየት ለመሰብሰብ ሞክሯል፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡ እነዚህ ሸማቾችና ነጋዴዎችም በአካባቢያቸው ኅብረተሰቡን እያስመረሩ ናቸው የሚሏቸውን የሸቀጦች ዋጋ ማሳያ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ገጽታ በየራሳቸው መንገድ ለመግለጽ ሞክረዋል፡፡  

አዲስ አበባ ላይ ከሰሞኑ ነዳጅ ማደያዎች በተለይ ቤንዚን የለንም በማለታቸው በየማደያው ረዣዥም የመኪኖች ሠልፍ ይታይ ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ የነዳጅ አገልግሎት እጥረት የሚፈጥረው የመኪኖች ሠልፍ በአዲስ አበባም ሆነ በብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች መመልከት አዲስ ነገር አለመሆኑ ይታያል፡፡ በተለይ ወር በሚገባደድበት ቀናት ሠልፉ  ሲከሰት ይታያል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ አንድም የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በመንግሥት ሊከለስና ቀጣዩ ወር ዋጋ ሊቀንስ ወይ ሊጨምር ይችላል ተብሎ ስለሚጠበቅ ነው፡፡

ሆኖም ከአዲስ አበባ በ600 ኪሎ ሜትሮች በምትርቀዋ ጅግጅጋ ከተማ ላይ ግን ይህ ችግር በተገላቢጦሽ ሲከሰት ነው የሚታየው፡፡ በውድ የውጪ ምንዛሪ ወደ አገር የሚገባ ነዳጅን ቀድቶ ወደውጪ አገሮች በኮንትሮባንድ አሾልኮ ለመሸጥ ቦቴዎችና ጀሪካኖች ሲሠለፉ የሚታይበት ጅግጅጋ የነዳጅ እጥረትን ሳይሆን የነዳጅ ምርቶች ግብይት መፋለሱን አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡

የጅግጅጋው አስተያየት ሰጪያችን የአነስተኛ ሱቅ ባለቤቱ ዳንኤል በላቸው ነዳጅ ጅግጅጋ ላይ የለም እየተባለ ነገር ግን ወደ ጎረቤት አገር በቦቴና በጀሪካን ይጋዛል ሲል ይናገራል፡፡ ይህ ለጅግጅጋና አካባቢው ሕዝብ የዋጋ ንረት ምንጭ መሆኑን የሚጠቅሰው ዳንኤል፣ ከመሀል ከተማ አንድ ኪሎ ሜትር ወደማይርቅ አካባቢ ፎርስ በሚባሉት አራት ሰው በሚጭኑ ባለሦስት እግር ታክሲዎች ለመጓዝ አሥር ብር ይጠየቃል ይላል፡፡ ብዙ ተማሪዎች የሚገለገሉበት ሁለት ኪሎ ሜትር በማይሞላውና ከመሀል ከተማ ወደ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ መስመር ለመሄድ 20 ብር ነው፡፡ በመሆኑም ኅብረተሰቡ በትራንስፖርትም ተማሯል፡፡ ነዳጅ በቦቴ፣ በርሜልና በጀሪካን በኮንትሮባንድ እየወጣ እንደሚሸጥ ተደጋጋሚ ጥቆማ ለመንግሥት ቢሰጥም ተጨባጭ መፍትሔ እንዳልተገኘ ያስረዳል፡፡  

ቀላፎ የሚመረተው የሽንኩርት ምርት ለጅግጅጋም ገበያ መትረፉንና የሽንኩርት ገበያ መረጋጋቱን የሚገልጸው ዳንኤል፣ በርካታ የቀንድ ከብቶች በሚገኙበት እየኖሩ የሥጋ ዋጋ አልቀመስ ማለቱን ይገልጻል፡፡ ዳቦና ሌሎች መሠረታዊ ምርቶች ላይ የተጋነነ ጭማሪ እንደሚታይና ጅግጅጋ ከዚህ በፊት ተቸግራባቸው የማይታወቁ ምርቶችም እየጠፉ መሆኑን ነው ያመለከተው፡፡ ከጎረቤት አገር የሚገቡ ፓስታ፣ ሩዝ፣ መኮሮኒ፣ ስኳርና ዘይት ላይ ታይቶ የማይታወቅ ጭማሪ አለ ይላል፡፡ በፊት ጅግጅጋ ሰው ሲመጣ ዘይት ወይም ልብስ፣ ጫማና ኤሌክትሮኒክስ ይዘህና ይባል እንደነበር ያስታወሰው ዳንኤል አሁን ግን በሌሎች የኢትዮጵያ  ክፍሎች እንደሚታየው ዓይነት የኑሮ ውድነት በከተማዋ  መታየቱን የአካባቢውን የገበያ ሁኔታ በመጥቀስ አስቀምጧል፡፡

ከጅግጅጋ ብዙ በማትርቀው ሐረር ከተማም በተመሳሳይ የኑሮ ውድነቱና የገበያው አለመረጋጋት ኅብረተሰቡን በከፍተኛ ደረጃ እያስመረረ እንደሚገኝ ከከተማው አስተያየቱን በስልክ ያቀበለን አዲስ ከፋለ ገልጾልናል፡፡ ልክ እንደ ጅግጅጋ ከጎረቤት አገር ይገቡ የነበሩና ገበያውን ለማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው ስኳር፣ ዘይት፣ እሽግ ምግቦች፣ አልባሳትና ኤሌክትሮኒክሶች ሐረር ዓይታ በማታውቀው ሁኔታ ዋጋቸው መጨመሩን ነው የተናገረው፡፡ ‹‹ሐረር ሲነሳ ጫት አብሮ ይነሳል›› የሚለው አዲስ፣ አንድ እስር ጫት 800 ብር ሲሸጥ ከርሞ ከሰሞኑ ነው ወደ 400 ብር የወረደው በማለት የሐረር ገበያ በአካባቢው በሚመረቱ ምርቶች ላይም አለመረጋጋቱን እንደሚንፀባረቅበት የተናገረው፡፡ ሐረር ላይ ነዳጅ ጠፋ መባሉ አዲስ አይደለም የሚለው አዲስ ትራንስፖርትና ቤት ኪራይ ማግኘትም ሌሎች የከተማው ፈተናዎች መሆናቸውን ያስረዳል፡፡

የአዳማው ደላላ መሐመድ አብዱረዛቅ የአደአ ጤፍና ሌሎች የሰብል ምርቶች ለወትሮው በዚህ በጋ ወቅት የሚረክሱበት ቢሆንም፣ ዋጋው እየተወደደ መምጣቱን ያስረዳል፡፡ በቅርበት የሚያውቀው የእህል ግብይት ውስጥ በማኅበር የተደራጁና የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከአርሶ አደሮች በቀጥታ እህል እንዲሸምቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ማድረጉ ትልቅ የዋጋ አለመረጋጋት ምንጭ እንደሆነ መሐመድ ያስረዳል፡፡

‹‹አሁን ላይ አርሶ አደሩ እህሉን በቀጥታ ለነጋዴው ሳይሆን ለማኅበራት እያቀረበ ነው፡፡ እነዚያ ማኅበራት ለገበያው ካላቀረቡት ነጋዴው  እጁ ላይ ምርት ስለሌለ መሸጥ አይችልም፡፡ በዚህ የተነሳ እህል ከገበያው ጠፋ እንዲሁም ተወደደ የሚል ምሬት ኅብረተሰቡ ጋር በሰፊው አለ፤›› ይላል መሐመድ፡፡ የሸቀጦች መመላለሻ የሆኑ ዋና ዋና መንገዶች ለምሳሌ የጅቡቲ መንገድ ሰላም መሆን ለአካባቢው የዋጋ መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን የሚናገረው መሐመድ፣ ነጋዴው እየተፈተነበት ያለው የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት ችግርም ቢፈታ ሲል ሐሳቡን ያጠቃልላል፡፡

ልክ እንደ ናዝሬቱ መሐመድ አብዱረዛቅ ሁሉ የምንዛሪ እጥረት የነጋዴዎችና አከፋፋዮች ችግር መሆኑን የባህር ዳሩ ነጋዴ በላይ አሁነው ይናገራል፡፡ አሁን ላይ ብዙዎቹ ሸቀጥ አቅራቢዎችና አከፋፋዮች እጃችን ላይ ዕቃ የለም ማለታቸው የተለመደ ሆኗል፡፡ ለዚህም መልሳቸው የውጪ ምንዛሪ የለም የሚል መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ አማራ ክልል በተለይ ባህር ዳር አካባቢ በአካባቢው የሚመረተው ጤፍና ሌላም የሰብል ምርት ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ ተወደደ ወይም ጠፋ የሚል መረጃ ሲሰጥ መስማት ያስገርማል በማለትም አቶ በላይ ይናገራል፡፡ በሌላ በኩልም መንግሥት ላይ ብቻ መፍረድም አይቻልም የሚለው አቶ በላይ አገሪቱ የምትገኝበት የጦርነት ሁኔታ ለባህር ዳርና አካባቢው የገበያ ችግር ተጨማሪ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ይገልጻል፡፡

የጋምቤላው ከተማ አከፋፋይ ሰይድ ረሺድ በበኩሉ የኬላዎች መብዛት ለዋጋ ውድነት አስተዋጽኦ እንዳለው ይጠቁማል፡፡ ዕቃዎችና ሸቀጦች አንድ ጊዜ ተቀርጠው ወደ አገር ቤት ከገቡ በኋላ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ወስዶ ለመሸጥ ብዙ ቦታዎች ላይ በተቋቋሙ ኬላዎች ላይ ቆሞ ማስቀረጥ የግዴታ ሆኗል ይላል፡፡ ከመሀል አገር ወደ ጋምቤላ ሸቀጦችን ለማምጣት ካለው ፈተና አንዱ ይህ የኬላ መብዛት መሆኑን ሚናገረው ሰይድ በከተማዋ ለሸቀጦች ዋጋ መናር አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲል ያስቀምጣል፡፡ በነጋዴዎች መሀል ረጃጅም እጆች ያላቸው ደላሎች መኖራቸውንም የተናገረው ሰይድ፣ የነዚህ ሰዎች በዋጋ አለመረጋጋት ላይ ያለ ተፅዕኖም ከባድ መሆኑን ነው የጠቆመው፡፡

ሪፖርተር በተለያዩ ክልል ከተሞች ያሉ ንግድ አንቀሳቃሾችን ሲያናግር በተለይ የመሠረታዊ ሸቀጦችን የዕለት ተዕለት ዋጋ ለውጥ መታዘብ የሚችሉ ሴቶችን ለማናገር ጥረት ያደረገ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥም የቢሾፍቱዋ ውባለም ወልደየስ አንዷ ናት፡፡ መለስተኛ የባልትና ውጤቶች ንግድ የምትሠራው ውባለም በቅርብ ጊዜ በኪሎ ከአሥር ብር በማይበልጥ ዋጋ ይገዛ የነበረው ገብስ ወደ 50 ብር ማሻቀቡን የገበያውን የቅርብ ዓመታት ከፍተኛ ጭማሪ ማሳያ በማድረግ ታቀርባለች፡፡ አጃ፣ በርበሬ፣ የሽሮ ሽምብራም ሆነ ሌላ ሸቀጥ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የምታነሳው ውባለም፣ ጤፍ በቢሾፍቱ 45 ብር በኪሎ እየተሸጠ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ለደንበኞች የሚፈልጉትን ዓይነት ባልትና ለማቅረብ ዋጋው ቢንርም የተሻለ የምትለውን ምርት እንደምትገዛ የምትናገረው ውባለም፣ የቢሾፍቱ ገበያ ግን ከዕለት ዕለት የሚዋዥቅና ይህ ነው ብሎ ለመተንበይ አስቸጋሪ እንደሆነባት ጠቁማለች፡፡

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወ/ሮ ዘውድነሽ ላቀው ከሆለታ በበኩላቸው፣ አካባቢያቸው ላይ ከአዲስ አበባ የተለየና የተጋነነ የዋጋ ማሻቀብ እንደማይታይ ይናገራሉ፡፡ በዋናነት ለቤት ውስጥ ፍጆታነት የሚውለው የመብራት ኃይል ታሪፍ ወቅታዊ ጭማሪ ግልጽ እንዳልሆነላቸው የሚናገሩት ወ/ሮ ዘውድነሽ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክፍያው ማሻቀቡን ጠቅሰዋል፡፡ መብራት ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሸቀጦች ምርቶች ላይም የገበያው ነገር ቆንጠጥ እያደረገ መምጣቱን የሚናገሩት ወ/ሮ ዘውድነሽ፣ ኅብረተሰቡ በእርግጥም ኑሮ እየከበደው እንደመጣ በአካባቢያቸው እንደሚያዩ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቻችን እንደሚሉት፣ በየአቅጣጫው ቢኬድ ወይም በየክፍለ አገሩ ቢዞር የገበያ አለመረጋጋትና የኑሮ ውድነት ያፈጠጠ ወቅታዊና አሳሳቢ ችግር ሆኗል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም ቢሆን ሪፖርተር ቅኝት ባደረገባቸው የሸቀጦች ገበያ ንሯል፡፡  አንዲት ነጠላ ዳይፐር (የሕፃናት ሽንት ጨርቅ) በፍሬ አሥር ብር ሲሸጥ ማየት የከተማውን ነዋሪ የኑሮ ውድነት ጫና የሚያሳይ ነው፡፡  በአዲስ አበባ ከተማ ዱቄት፣ ዘይት፣ ፓስታ፣ ሞኮሮኒና ዘይት የመሳሰሉ መሠረታዊ ሸቀጦች በየጊዜው እየጨመሩ መሆኑም አኗኗርን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች