በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች የትራንስፖርት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ የሕዝብ ብዛት እየጨመረ መምጣትና ከተሸከርካሪው ጋር የሚመጣጠን መንገድ አለመኖሩ የችግሩ መባባስ እንደ ምክንያት ይነሳል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በርካታ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ሁኔታዎች ቢፈጠሩም ችግሩን ሊፈቱ አልቻሉም፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ረዣዥም ሠልፎችን መመልከት የከተማው መለያ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ለማቃለል የግል የተሽከርካሪ ባለንብረቶችን ያካተቱ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ካምፓኒዎች ሥራ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በሞባይል መተግበሪያ አገልግሎት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት ካምፓኒዎች ከ40 ሺሕ በላይ የግል ተሽከርካሪዎች አማካይነት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡም የተለያዩ የመተግበሪያ አማራጮችን ያካተተና በአንድ ጉዞ ላይ የተለያዩ ተጠቃሚዎችን በጋራ የሚያስጠቅም እንዲሁም ተገልጋይንና አሽከርካሪን በእኩል ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለ ራይት ራይድ መተግበሪያ ይፋ ሆኗል፡፡ አሽከርካሪና የታክሲ ተገልጋይን በእኩል ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለው የዕይታ ቢዝነስ ሶሊዩሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ሁሴን ከትራንስፖርት መተግበሪያው አጠቃላይ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በበይነ መረብ በመታገዝ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ድርጅቶች ተበራክተዋል፡፡ የእናንተ የታክሲ አገልግሎት ምን የተለየ ነገር ይዞ መጥቷል?
አቶ ተመስገን፡- በዋነኝነት ተጠቃሚዎች ለብቻቸው ሆነው ሳይሆን በአንድ መስመር ላይ ሁለትና ሦስት ገብተው የሚጠቀሙበትን አፕልኬሽን ይዘን መምጣታችን ነው፡፡ ይኼንንም ከአጋር አሽከርካሪዎች ጋር በመሆን አገልግሎትን እንዴት መስጠት እንደሚቻል ተወያይተናል፡፡ አገልግሎቱን በምሳሌ ለማስረዳት አንድ አሽከርካሪ ከመገናኛ ተነስቶ ወደ ሜክሲኮ አንድን ተጠቃሚ ሲያደርስ፣ የሚያወጣው ዋጋ አለ፡፡ በዚህም ጉዞውን ሲያደርግ የሚያወጣውን ወጪ ለሁለትና ሦስቱ ተጠቃሚዎች ማካፈል ቢቻል፣ ደንበኞች በቅናሽ ክፍያ የሚያገኙበት እንዲሁም አሽከርካሪውም ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበት አማራጭ የያዘ መተግበሪያ ነው ይዘን የመጣነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ነዳጅ መጨመሩን ተከትሎ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ካምፓኒዎች የዋጋ ማሻሻያ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር የእናንተ አገልግሎት ምን ይመስላል?
አቶ ተመስገን፡- ባለፉት ዓመታት በዚህ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ካምፓኒዎች የመነሻ ዋጋ ተመን አስቀምጠዋል፡፡ ተጠቃሚዎችም ከመነሻ ዋጋው ጨምሮ የተጓዙበትን ኪሎ ሜትር ጨምረው እንዲከፍሉበት አሠራሩ ተዘርግቷል፡፡ የእኛ ካምፓኒ የሚያደርገው የመነሻ ዋጋውን ቀንሶ፣ ነገር ግን የሚሄዱበትን ኪሎ ሜትር አሁን ካለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከግምት በማስገባት ማሻሻያ አድርገናል፡፡ በቅርቡ በመንግሥት እንደተገለጸው የነዳጅን ድጎማ መንግሥት ስለሚያቆም፣ ይኼ ደግሞ አሽከርካሪዎች ላይ ጫና ስለሚፈጥርና ለአሽከርካሪዎቹ ዋጋ የማይጨምር ከሆነ፣ ቢዝነሱን ለማስቀጠል አዳጋች ይሆናል፡፡ ስለዚህ ተሳፋሪዎችን በማይጎዳ መንገድ የመነሻ ዋጋውን ቀንሰን፣ ነገር ግን በሚሄዱበት ኪሎ ሜትር የዋጋ ማስተካከያ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡ ይኼ ማለት ኪሎ ሜትሩ እየጨመረ በሄደ ቁጥር መጠነኛ የሆነ ጭማሪ እንዲኖረውና አሽከርካሪም እንዲሁም ተጠቃሚው ተጎጂ የማይሆኑበትን አሠራር ዘርግተናል፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ካምፓኒዎች የሚያስከፍሉት ኮሚሽን በተሽከርካሪ ባለንብረቶች ዘንድ ከፍተኛ ነው የሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ ይደመጣል፡፡
አቶ ተመስገን፡- በዘርፉ የተሰማሩ የተለያዩ ተቋማት ተጠቃሚውንና አሽከርካሪውን በማገናኘታቸው የሚያገኙት የኮሚሽን ክፍያ አለ፡፡ እነዚህ ተቋሞች አሁን ባለው መረጃ መሠረት 17 በመቶ፣ 12 በመቶ እንዲሁም በአማካይ አሥር በመቶ የሚያስከፍሉ አሉ፡፡ እኛ ከተሽከርካሪዎች የምንወስደው ኮሚሽን አምስት በመቶ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ከሌሎቹ ካምፓኒዎች ቅናሽ በሆነና አሽከርካሪውን ከዚህ በፊት ሲከፍል ከነበረው ከፍተኛ የኮሚሽን ክፍያ በዝቅተኛ ክፍያ ዋጋ ተጠቃሚ የሚያደርገውን ክፍያ አቀርበናል፡፡ ተጠቃሚዎች 9919 በመደወል ወይም በቀጥታ መተግበሪያውን (አፕሊኬሽን) ከስቶር በማውረድ አገልግሎቱን ማዘዝ ይችላሉ። ከዚህም ባሻገር በቀጣይ ሦስት ወራት የእኛን መተግበሪያና የደንበኛ አገልግሎት አሰጣጣችንን የምንሞክርበት ጊዜ ስለሆነ ምንም ዓይነት ክፍያ አንቀበልም፡፡ ከሦስት ወር በኋላ ግን መደበኛ ሥራው ይቀጥላል፡፡ በዚህም መሠረት መተግበሪያችን ይፋ ባደረግን አንድ ወር ውስጥ ከ4,000 በላይ አሽከርካሪዎችን መመዝገብ ችለናል፡፡
ሪፖርተር፡- በርካታ ባለንብረቶች የግል ተሽከርካሪዎችን እያስመዝገቡ የታክሲ አግልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልጉ መሥፈርቶች ምንድናቸው?
አቶ ተመስገን፡- በእኛ በኩል አሽከርካሪዎችን ለመመዝገብ የምንጠይቃቸው ሰባት ዋና ዋና ዶክመንቶች አሉ፡፡ ከዚያ ውስጥ በአትኩሮት የምናያቸው አንደኛ መኪናው የተሠራበት ሞዴል፣ ሁለተኛ የኢንሹራንስ ጉዳይና ጊዜው ያላለፈበት መንጃ ፈቃድ ናቸው፡፡ በዘርፉ የተለያዩ ሞዴል ያላቸው ተሽከርካሪዎች ሲገቡ ይስተዋላል፡፡ በዚህም መሠረት ሦስት ዓይነት መኪኖችን እናስገባለን፡፡ አንደኛው ዓይነት ሁሉም መኪኖች የሚካተቱበት (ቪትስና ያሪስ የምንላቸውን ጨምሮ)፣ ሁለተኛው ዓይነት ሲዳን መኪኖች የሚካተቱበት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ኤስዩቪ (SUV) ስድስትና ሰባት ወንበሮች ያላቸው ተሽከርካሪዎችን እናስገባለን፡፡ ሁሉም ተሽከርካሪዎች ሞዴላቸው ከ2000 በላይ መሆኑን፣ መሠረታዊ የደኅንነት ፍተሻን ማለፋቸውን እናረጋግጣለን።
ሪፖርተር፡- በከተማው ከሚኖረው የግል ተገልጋይ ባሻገር ለተቋሞች በልዩነት የሚሰጥ አገልግሎት አለ?
አቶ ተመስገን፡- በአገልግሎት በግለሰብ ከሚጠቀሙ ደንበኞች ባሻገር እኛ ያነጋገርናቸው ኤምባሲዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የተለያዩ የንግድ ተቋማት አሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ቤት ለቤት የተለያዩ ሽያጭ ከሚያከናወኑ ተቋማት ጋርም ለመሥራት ዕቅድ አለን፡፡ ይኼ ለአሽከርካሪዎች ተጨማሪ ሥራ የሚያመጣ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በስልክ መተግበሪያ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ በኋላ አሽከርካሪዎች ላይ የሚደርስ አደጋ እየተበራከተ መጥቷል፡፡ ይኼን ለመቆጣጠር የምትጠቀሙት መተግበሪያና አቅጣጫ መጠቆሚያ ቴክኖሎጂ ተደራሽነት ምን ይመስላል?
አቶ ተመስገን፡- በከተማችን አሽከርካሪዎች በዋናነት የደኅንነት ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡ አሽከርካሪዎች በቀንም ሆነ በማታም ጥቃት እየደረሰባቸው ሲሆን ከዚህም አለፍ ሲል እስከ ግድያ እየደረሰባቸው ነው፡፡ ያንን ለመቅረፍ አንደኛው በመተግበሪያው ላይ ያስቀመጥነው የአደጋ ጊዜ ግንኙነት መፍጠሪያ (Emergency Contact) የሚፈልጉት ቁጥር በማኖር፣ ችግሩ ሲከሰት ቁጥሩን በመጫን ወደ እነዚህ ቁጥሮችና ወደ እኛ ካምፓኒ አሽከርካሪው የገጠመውን ጥቃት መድረሱን መረጃ ለማግኛነት የሚያስችል መንገድ ፈጥረናል፡፡ ስለዚህ በመረጃው መሠረት አቅጣጫውንና የተጠቃሚውን ማንነት በማወቅ ለጥቃቱ መልስ የምንሰጥበትን ዕድል ይሰጠናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ተሽከርካሪዎቹ ላይ በምንገጥመው የአቅጣጫ መቆጣጠሪያን ከስልካቸው ጋር በማገናኘት የመኪና ስርቆትን የመቆጣጠርያ መተግበሪያ እናካትታለን፡፡ ስለዚህ አሽከርካሪው በእጅ ስልኩ ተሽከርካሪውን የሚቆጣጠርበትን መንገድ ለማካተት ከአሽከርካሪዎቹ ጋር በቀጣይ ለመነጋገር ዕቅድ ይዘናል፡፡