Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን እስከምን ድረስ?

የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን እስከምን ድረስ?

ቀን:

በሕዝቦች መካከል ያለውን አብሮነትና አንድነት ለማበረታታት የመቻቻል እሴቶችን ለማሳደግ ይቻል ዘንድ በየዓመቱ ጥር 27 ቀን (ፌብሪዋሪ 4 ቀን) የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ተብሎ መከበር ከጀመረ ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በዓሉ በተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች መካከል አብሮ የመኖርና የመቻቻል እሴቶችን ለማስ ተዋወቅ ለሚደረገው ጥረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዕውቅና ሰጥቶታል፡፡

ይህንኑ መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ ‹‹የሰው ልጆች ወንድማማችነት/እኅትማማችነት ስለ ዓለም ሰላምና አብሮ ስለ መኖር›› በሚል መሪ ቃል የመታሰቢያ ቀኑ ጥር 27 ቀን 2014 ዓ.ም.  በኢሲኤ የአፍሪካ አዳራሽ ተከብሮ ውሏል፡፡

መድረኩን ያዘጋጀው የአሜን ኢትዮጵያ ቦርድ ሰብሳቢ ሰሎሞን ንጉሤ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ እምነት አማኙ በሌላው መታገዝና መፈቀር ያለበትን ወንድሙን ወይም እህቱን እንዲመለከት ያደርገዋል፡፡ መላውን ዓለም፣ ፍጥረታትንና ሁሉንም የሰው ልጆች በፈጠረው በፈጣሪ ላይ ባለ እምነት ተመሥርተው አማኞች ፍጥረትንና መላውን ዓላም በመጠበቅ፣ እንዲሁም እያንዳንዱን ሰው በተለይም ድሆችንና ብዙ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በመደገፍ፣ ይህንን ሰብዓዊ ወንድማማችነትን/እህትማማችነትን እንዲገልጹ መጠራታቸውን ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡

ሁሉንም የሰው ልጆች ወንድማማችና እህትማማች ያደረገውን ታላቁን መለኮታዊ ጸጋን በመገንዘብና የመከባበር ባህልን ለማዳበር ለቀጣዩ ትውልዶች እንደ መመርያ ሆኖ እንዲያገለግል በአምላክና በሰው ልጆች ወንድማማችነት/እህትማማችነት ላይ እምነት ያላቸው ሁሉ እንዲተባበሩና አብረው እንዲሠሩ መጋበዛቸውን ነው ያመለከቱ፡፡

ማኅበረሰቡ ለዚህም ዕውን መሆን ከራሱ፣ ከተፈጥሮ፣ ከጎረቤቱ፣ ማኅበራዊ ፍትሕን ከሚያሰፍኑ መንግሥታዊ ተቋማትና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት በማድረግ የመፍትሔው አካል መሆን እንዳለበት ሰብሳቢው ጠቁመው ሰላም የሌለው ማኅበረሰብ አገራዊ ችግሮች እንደማይፈታ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በሥነ ሥርዓቱ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ፕሮግራሙን በቡራኬ ያስጀመሩ ሲሆን በሰላምና አብሮ በመኖር ዙሪያ ላይ ያተኮሩ ገለጻና ማብራሪያ አድርገዋል፡፡

በማብራሪያቸውም ላይ ቤተ እምነቶች የሰላምን አስፈላጊነት ለእምነቱ ተከታዮች ሳያስተምሩና ሳይሰብኩ ያለፉባቸው ጊዜያት እንደሌሉ፣ ነገር ግን ትምህርቱን ወይም ስብከቱን ተግባራዊ በማድረጉ ላይ ችግር ሲፈጠር እንደሚስተዋል ነው የተናገሩት፡፡

‹‹የሰው ልጆች ወንድማማችነት/እህትማማችነት ለዓለም ሰላምና አብሮ ለመኖር›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ሰነድ የተፈረመው ጥር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. (ፌብሪዋሪ 4 ቀን 2019) በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ አቡዳቢ ውስጥ ነው፡፡ የፈረሙትም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስና ታላቁ ኢማም የአል አዝሃር አህመድ ኤል ታየብ ናቸው፡፡

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ‹‹ወንድማማችነት ራሳችንን የሁሉም አባት ለሆነው ፈጣሪ እንድንከፍትና ከሌላው ወንድም፣ እህት ጋር ሕይወትን እንድንካፈል ወይም እርስ በእርስ እንድንደጋገፍ፣ እንድንፋቀር፣ እንድንተዋወቅ ያደርገናል፤›› ማለታቸው ይታወሳል።

 

የተባበሩት መንግሥት ድርጅቱም የስምምነት ሰነዱን ተቀብሎ ዕውቅና ከመቸሩም ባሻገር የፊርማው ሥነ ሥርዓት የተከናወነበት ቀን በመላው ዓለም በየዓመቱ ተከብሮ እንዲውል ወስኗል፡፡

ተመድ ተቀብሎ ባፀደቀው በዚሁ ሰነድ ከተካተቱት ዓበይት ነጥቦች መካከል የአምልኮ ቦታዎችን ምኩራቦችን፣ አብያተ ክርስቲያናትንና መስጊዶችን፣ መጠበቅ፣ በሃይማኖቶች፣ በሰው እሴቶች፣ በሕጎችና በዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተረጋገጠ ግዴታ ነው፡፡ ማንኛውም በአምልኮ ቦታዎች ላይ የሚከናወን ጥቃት ወይም የኃይል ተግባር የታከለበት የማስፈራራት ሙከራ፣ የቦምብ ፍንዳታ ከሃይማኖት አስተምህሮ ማፈንገጥ፣ ግልጽ የሆነ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው የሚለው ይገኝበታል፡፡

እንደ ሰነዱ መግለጫ፣ ሽብርተኝነት በምሥራቅም ይሁን በምዕራብ፣ በሰሜንም ይሁን በደቡብ፣ ፍርኃትን፣ ሽብርንና ተስፋ መቁረጥን በማስፋፋት የሰዎችን ፀጥታ የሚያደፈርስና ደኅንነትን የሚጎዳ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን አሸባሪዎች እንደ ሰበብ ቢጠቀሙበትም እንኳን ከሃይማኖት የሚመነጭ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሃይማኖታዊ ጽሑፎች የተሳሳቱ ትርጓሜዎች ስብስብና ከረሃብ፣ ከድህነት፣ ከኢፍትሐዊነት፣ ከጭቆናና ከኩራት ጋር በተዛመዱ ፖሊሲዎች ምክንያት የሚመጣ ውጤት ነው፡፡

ለዚህም ነው በገንዘብ፣ በመሣሪያና በስትራቴጂ አቅርቦ የተደገፉ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎችን መደገፍ፣ ማቆምና እነዚህን እንቅስቃሴዎች መገናኛ ብዙኃንን ተጠቅሞም ቢሆን እንኳን ተገቢ አለመሆናቸውን ለማሳየት መሞከር በጣም አስፈላጊ ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ደኅንነትንና የዓለምን ሰላም አደጋ ላይ የሚጥሉ እንደ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ተደርገው መታየት አለባቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሽብርተኝነት በሁሉም መልኩና መገለጫዎቹ መወገዝ አለባቸው የሚለውም በሰነዱ ከተካተቱ ነጥቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡  

ወንድማማችነትን፣ አብሮነትን፣ መከባበርን እና የጋራ መግባባትን ለማጎልበት የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ምኞትን ወደ ዘላቂ ተሳትፎና ተጨባጭ ድርጊቶች ለመተርጐም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ከፍተኛ የሰብዓዊነት ኮሚቴ በአቡዳቢ በሰዓድት ደሴት ላይ ምኩራብ፣ ቤተ ክርስቲያን እና መስጊድ ያለው አብርሃማዊ የቤተሰባዊ ቤት ለመገንባት ማቀዱ ታውቋል፡፡

ዓምና የሰላም ወንድማማችነት ከፍተኛ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ  ‹‹በዚህ ወሳኝ የሰው ልጅ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እኛ መንታ መንገድ ላይ እንገኛለን፣ በአንድ በኩል የሰው ልጅ በሚደሰትበት ዓለም አቀፋዊ የወንድማማችነት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሰዎችን ስቃይና እጦትን የሚጨምር ከባድ ሰቆቃ›› ውስጥ እንገኛለን ማለታቸውን በወቅቱ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች መዘገባቸው   ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...