Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትሴኔጋል: ለታላቁ ቡድን ታላቅ ክብር

ሴኔጋል: ለታላቁ ቡድን ታላቅ ክብር

ቀን:

ኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ዕትሙ በስፖርት ዓምዱ ላይ ባወጣው ጽሑፉ ‹‹በመፈንቅለ መንግሥትና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የታጀበችው አፍሪካ እጅግ ጠቃሚ በሆነው እግር ኳስ ላይ ትኩረቷን አድርጋለች፤›› ይላል፡፡ አባባሉ አፍሪካውያንን ከማንኳሰስ የሚመነጭ ቢሆንም፣ አፍሪካውያን በችግሮቻቸው ታጥረው እየቆዘሙ ብቻ እንዲኖሩ የመሻት ዝንባሌንም ያንፀባርቃል፡፡

ባለፈው እሑድ ፍፃሜውን ያገኘው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ግን ለአፍሪካውያን በበረሃ መሀል የተገኘ የውኃ ምንጭ ይመስል ብርቅ እንጂ፣ በተራ መነጽር ሊታይ እንደማይገባ እግር ኳስ የእምነት ያህል በሚዘወተርበት በምድረ እንግሊዝ በነገሡት ከዋክብት ሳዲዮ ማኔና መሐመድ ሳላህ መካከል የተደረገውን የፍፃሜ ውድድር መመልከቱ ከበቂ በላይ እንደሆነ መመልክት ይቻላል፡፡

ሁለቱን የእግር ኳስ ከዋክብትን ጨምሮ በርካቶች አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በሚረሱበትና በደስታ ዕንባ የሚታጠቡበት የኳስ ፍቅር ለአፍሪካ ስጦታዋ ከሆነ ሰነባብተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ባለፈ ምስክር ሊኖር አይችልም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለአያሌ አፍሪካውያን ተጫዋቾች ከድህነት መውጫ መንገድ የሆነው እግር ኳስ ታሪኩ በሴኔጋላውያን የቴሪንጋ አንበሶች ውስጥ በጉልህ ታይቷል፡፡ ከድሃ ማኅበረሰብ ወጥተው ቁሳዊ ሀብት ያካበቱ ለመላ አኅጉሪቱ ደስታን ማጎናፀፍ የቻሉ ሲሆን፣ ማኅበረሰባዊ ትስስርን በማጉላት ረገድም ያለው ሚና አሌ የማይባል ሆኖ ታይቷል፡፡

በዚሁ የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ፍፃሜ ሳምንት የአፍሪካ ኅብረት የሊቀ መንበርነት መንበር የተረከቡት የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል፣ የፍፃሜውን ጨዋታ በአዲስ አበባ በስሜት እየተወራጩ ሲመለከቱ የታዩ ሲሆን፣ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳችው ሴኔጋል፣ ይህንን ቀን ብሔራዊ በዓል አድርጋ እንድታከብር ወስነዋል፡፡ አኅጉራዊ ኃላፊነትን የተረከቡት ሴኔጋላውያንም የኳስ ድላቸው በልጦባቸው በደስታ ሲቦርቁ ታይተዋል፡፡

ለብዙዎች የሴኔጋል ድል ያሳየው ጉዳይ ቢኖር፣ እግር ኳስ ለአፍሪካ የተለያዩ የፖለቲካ ጽንፎችን ማስታረቂያ፣ የአገራዊ አንድነት መግባቢያ፣ ትስስር መፍጠሪያና ማጎልበቻ መሆኑን ነው የሚሉት በርካቶች ናቸው፡፡            

ከምዕራብ አፍሪካ አገሮች የተረጋጋ የፖለቲካ ባህል እንዳላት የሚነገርላት ሴኔጋል ዋና ከተማዋ ዳካርን ጨምሮ በሁሉም ከተሞቿ ውድና ታታሪ ልጆቿ ባሳዩት የኳስ ተዓምር፣ በአንድ ዓይነት ቋንቋና ስሜት በደስታ ማዕበል እንዲዘፈቁ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡

ልጆቻቸው ሴዲዮ ማኔ፣ ኤድዋርዶ መንዲና ሌሎችም ባልሸነፍባይነት ያሳኩት ድል ብዙዎች የጓጉለትን አሸናፊነት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ዕውን አድርገውላቸዋል፡፡

በሴኔጋል የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ዝቅተኛ የማኅበረሰብ ክፍል በሚኖሩባት ባቤሌ ተወልዶ፣ ብዙ የሕይወት ውጣ ውረድ አሳልፎ ዛሬ ላይ ከታላላቅ በእግር ኳስ ከዋክብት መዝገብ የተካተተው ሴዲዮ ማኔ፣ የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከመጀመሩ በፊት፣ ትንበያው ይሳካለታል፣ ያውቃል የተባለው ተንባ፣ ‹‹ማኔ ሜዳ ገብቶ እንዳይጫወት፣ መጫወት ካሰበ ግን ሕይወቱ ያልፋል፤›› ማለቱን ተከትሎ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፣ ‹‹የእኔ ሕይወት በፈጣሪ እጅ እንጂ በጠንቋይ አይወሰንም፣ ከሆነም ፈጣሪ ያሰበው ብቻ ነው የሚሆነው፤›› ማለቱም ተዘግቧል፡፡

በሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን የኃላፊነት ቆይታውን በመጥቀስ ብዙዎች ዕድለኛ አድርገው ይገልጹታል፡፡ የቴራንጋ አንበሶች ዋና አሠልጣኝ አሊዩ ሲሴ፣ በተጨዋችነት ዘመኑ ማሳካት ያልቻለውን የአፍሪካ ዋንጫን ከብዙ ዓመታት በኋላ በአሠልጣኝነት ዘመኑ አሳክቷል፡፡

ቀድሞ የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች በነበረበት ወቅት የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ ካስተናገደችው የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ጋር በ23ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ተሳትፎ የነበረው አሊዩ ሲሴ፣ በወቅቱ መለያ ምት መሳቱን ተከትሎ የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ዋንጫ ማጣቱ አይዘነጋም፡፡

በፀፀት ውስጥ ሆኖ ከሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ጋር እስከ ካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ በትዕግሥት የዘለቀው አሊዩ ሲሴ፣ ከካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ድል በፊት እ.ኤ.አ. በ2019 በግብፅ አስተናጋጅነት በተካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሴኔጋልን በዋና አሠልጣኝነት እየመራ ለፍፃሜ ደርሶ ዋንጫውን በአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን የተነጠቀበት አጋጣሚም የሚዘነጋ አይደለም፡፡

የብዙ አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ በተለይም አፍሪካ ውስጥ አንድ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ውጤት የማያመጣ ከሆነ የአሊዩ ሲሴ ዓይነት ዕድል ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡ ለዚህም በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በጋናና በናይጄሪያ እንዲሁም በሌሎችም አገሮች የስንብት ዕጣ የገጠማቸውን አሠልጣኞች መመልከቱ በቂ ይሆናል፡፡

የሴኔጋል አሠልጣኝ አሊዩ ሲሴ የአፍሪካ ዋንጫ ምኞቱን ለማሳካት ረዥሙን መንገድ እንዲጓዝ ላደረጉ የአገሪቱ ስፖርት ኃላፊዎች ምሥጋና ይግባቸውና አሰልቺውን የአሠልጣኝነት ጉዞ የተጓዘው ሲሴ፣ በካሜሩን ለእሱም ሆነ ለአገሪቱ የመጀመርያ የሆነውን የአፍሪካ ዋንጫን ከቴራንጋ አንበሶች ጋር አሳክቷል፡፡

አሠልጣኙ የአፍሪካ ዋንጫን በተደጋጋሚ በመውሰድ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት የግብፅ ብሔራዊ ቡድን (ፈርዖኖቹ) በመለያ ምት 4ለ2 ከረታ በኋላ፣ ጨዋታውን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹‹የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ነኝ፣ በእግር ኳስ ሕይወቴ ረዥም፣ አስቸጋሪ፣ እንዲሁም ውስብስብ መንገዶችን እኔም ሆንኩ ቡድኔ ተጉዘናል፣ አሳልፈናልም፣ ነገር ግን ይህን አስቸጋሪና አሰልቺ የእግር ኳስ ሕይወት ተስፋ ባለመቁረጣችን የዓመታት ህልማችንን አሳክተናል፤›› በማለት ነው አስተያየቱን የሰጠው፡፡

አሠልጣኙ በተለይ በመደበኛውና በተጨማሪው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መጠናቀቅ ሳይችል ወደ መለያ ምት በሄደው የፍፃሜ ጨዋታ፣ ግብፅ በመድረኩ ካላት ስምና ዝና እንዲሁም ጥንካሬ አንፃር ዋንጫውን ማንሳት መቻል ትርጉሙ ብዙ እንደሆነ የተናገረው ሲሴ፣ ‹‹በአፍሪካ ዋንጫ ስኬታማ ቡድንን ማሸነፍ ደግሞ ስሜቱ ሌላ ነው፡፡ የካሜሩንን የአፍሪካ ዋንጫ ጨምሮ ሌሎችም መድረኮች ለሰባት ተከታታይ ዓመታት ያህል ጠንክረን ስንዘጋጅ ነው የቆየነው፣ ድሉም ይገባናል፤›› በማለት ጭምር ነው አስተያየቱን ያከለው፡፡

አገራቸው ሴኔጋል የግብፅ አቻዋን በመለያ ምት 4 ለ 2 በማሸነፍ ካሜሩን ያውንዴ ላይ ዋንጫውን ስታነሳ፣ በ35ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የነበሩት ማኪ ሳል፣ ዕለቱ የአገሪቱ የድል በዓል እንዲሆን መወሰናቸውን ጭምር አስታውቀዋል፡፡

አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ማኪ ሳል በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ ካጠናቀቁ በኋላ፣ ኮሞሮስን ለመጎብኘት የነበራቸውን ጥሪ ሰርዘው ብሔራዊ ጀግኖቻቸውን ለመቀበል ወደ ሴኔጋል ዳካር ስለመብረራቸውም ተዘግቧል፡፡ የቴራንጋ አንበሶች በዳካር ቤተ መንግሥት ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት እንደሚጠብቃቸው ጭምር እየተነገረ ይገኛል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ቀድሞ ለውድድሩ አሸናፊ ይሰጥ የነበረውን 2.5 ሚሊዮን ዶላር፣ በዚህ ዓመት በእጥፍ በማሳደግ ለአሸናፊው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን አምስት ሚሊዮን ዶላር ለሽልማት አቅርቧል፡፡

ግብፅና ሴኔጋል በቅርቡ ለኳታር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አንድ የደርሶ መልስ ጨዋታ ይጠብቃቸዋል፡፡ ይህንኑ የማጣሪያ ጨዋታ ተከትሎ የግብፁ መሐመድ ሳላህ፣ ለቡድን ጓደኞቹ ከወዲሁ ሴኔጋላውያንን ለመበቀል መዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው ያሳሰባቸው ስለመሆኑ ጭምር እየተነገረ ይገኛል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...