Friday, September 30, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚገኙ ሼዶች በባለሀብቶች የተያዙት ግማሽ ያህል ናቸው ተባለ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው ፓርኮች አንዱ በሆነው፣ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚገኙ 15 ሼዶች፣ በባለሀብቶች የተያዙት ሰባት ብቻ ናቸው ተባለ፡፡

  ይህ የተገለጸው ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት ያለውን አፈጻጸም የተመለከተ ማብራሪያ፣ ዓርብ የካቲት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል በተሰጠበት ወቅት ነው፡፡

  በመግለጫው እንደተመለከተው ሼድ በተገነባላቸው 11 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ካሉት 177 ሼዶች 158 የሚደርሱት በባለሀብቶች የተያዙ ሲሆን፣ በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ካሉት 15 የሚደርሱ ሼዶች በባለሀብቶች የተያዙት ሰባት ብቻ ናቸው፡፡

  የውኃ መሠረተ ልማት እንዲሁም የፓርኩ የመዳረሻ መንገድ ግንባታ በወሰን ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት መጓተቱ፣ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙት ሼዶች በተፈለገው ልክ በባለሀብቶች እንዳይያዝ ካደረጉት ውስጥ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡

  በግማሽ ዓመቱ ለባለሀብቶች በኪራይ ከተላለፉ 158 ሼዶች ውስጥ 98 የሚሆኑት ሥራ ላይ እንደዋሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 60 ሼዶች ተሟልተው ለምርት ሥራ ስላልዋሉ  የሼዶች የመጠቀም ምጣኔ (Utilization Rate) 62 በመቶ ብቻ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

  የኮርፖሬሽኑ የማርኬቲንግና ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሔኖክ አሥራት እንዳስታወቁት፣ በሥራ ላይ ከሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በግማሽ መቱ5,469 ወንድ28,402 ሴት በጠቅላለው ለ33,371 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

  ሐዋሳ፣ ቦሌ ለሚና አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሥራ ዕድል ፈጠራው ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስዱ ያስረዱት አቶ ሔኖክ፣ በተያዘው የግማሽ ዓመት የተፈጠረው የሥራ ዕድል ባለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 21,903 የሥራ ዕድል ጋር ሲነፃፀር የግማሽ ዓመቱ የሥራ ዕድል በ52 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

  በአዳማ፣ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክና አዲስ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል በመቅጠራቸው፣ እንዲሁም የቂሊንጦና የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ኦፕሬሽን መግባት በግማሽ ዓመቱ ለተገኘው የተሻለ  አፈጻጸም  ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

  ሼዶችን ተረክበው ወደ ሥራ የገቡ ባለሀብቶች በተወሰኑት ሼዶች ላይ ብቻ መሥራታቸው፣ እንዲሁም የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በወቅታዊ ችግር ምክንያት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አለመታወቁ ሼዶችን በተመለከተ የተጠበቀውን ያህል አፈጻጸም እንዳይመዘገብ  አድርጎታል ተብሏል፡፡

  ኮርፖሬሽኑ በግማሽ ዓመቱ ከሼዶች ኪራይ፣ ከለማ መሬትና ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች 649.22 ሚሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ 557.11 ሚሊዮን ብር ገቢ እንዳገኘ በመግለጫው ወቅት ተገልጿል፡፡

  በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የፕላኒንግና ሞኒተሪግ መምርያ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ዘካርያስ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተፈጠረው ጦርነት ጋር ተያይዞ በኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም በመቀሌ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተፈጠሩ ቸግሮች በግማሽ ዓመቱ ኮርፖሬሽኑን ያጋጠሙ ተፅዕኖዎች ናቸው፡፡

  ኮርፖሬሽኑ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የደረሰውን ጉዳት የማጥናትና የመሰነድ ሥራዎችን እንዳከናወነ የተናገሩት አቶ ፀጋዬ፣ በፓርኩ ውስጥ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል ነው? የሚለው  የጥናት ውጤት ቀሪ ሥራዎች ሲጠናቀቁ  ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

  በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉዳት ከደረሰባቸው አልሚዎች  ሦስት የሚደርሱ ድርጅቶች ሥራ እንደጀመሩ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ሌላ አንድ ድርጅት ደግሞ የማሽን ማስተካከያ በማድረግ በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ እንደሚገባ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

  የመቀሌ ኢንዱስትሪክ ፓርክ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ምንም ዓይነት የመረጃ ልውውጥ ስለሌለ ለማወቅ አልተቻለም ያሉት አቶ ፀጋዬ፣ በፓርኩ ውስጥ ያለው የመንግሥትና የአልሚው ንብረትና ምርት ምን ያህል ተጎድቷል? የሚለው ከተቋሙ ዕውቅና ውጭ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

  አጎዋ በፓርኩ ውስጥ የተሰማሩ አልሚዎች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቅረፍ ውይይቶች እንደተደረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ እንደ ቻይና ባሉ አገሮች የቀረቡ አማራጮችን እንዲጠቀሙ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል ብለዋል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች