በግንባታ ግብዓቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ከእጥፍ በላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ነጋዴዎች እየገለጹ ነው፡፡
በገበያው ውስጥ እጥረትም ሆነ የተለየ የመግዛት ፍላጎት በሌለበት በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ በግንባታ ግብዓቶች ላይ ከእጥፍ በላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ነጋዴዎቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል። በተለይም በቤት ክዳን ቆርቆሮና በሚስማር ምርቶች ላይ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል ብለዋል።
በግንባታ ዕቃዎች ንግድ ሥራ የተሰማራው መሐመድ ኢብራሂም በተለይ በቆርቆሮ ምርት ላይ ከ150 ብር በላይ ጭማሪ መታየቱን ገልጿል፡፡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከነበረበት 250 ብር ወደ 400 ብር ከፍ ማለቱን ተናግሯል፡፡ የዋጋ ጭማሪው የምርት እጥረት ወይም የፍላጎት መጨመር እንዳልሆነ የሚገልጸው መሐመድ፣ ምክንያቱ ሳይታወቅ በእያንዳንዱ የግንባታ ዕቃ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየታየ መሆኑን አስረድቷል፡፡
በአገር ውስጥ የሚመረቱ የቤት ክዳን ቆርቆሮና ሚስማር የሚሸጠው መሐመድ፣ በሚስማር ዋጋም ላይ በካርቶን እስከ ከ200 ብር በላይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ገልጿል፡፡ አራት መቶ ብር የነበረው የአንድ ካርቶን ሚስማር ዋጋ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ስድስት መቶ ብር መድረሱን ይገልጻል፡፡ በየቀኑም የዋጋ ጭማሪ እያሳየ እንደሚገኝ አክሏል፡፡
የተስፋ ፅዮን ብረታ ብረት ባለቤት አቶ ሳሙኤል ተዛረ ባለፉት ሁለት ዓመታት የግንባታ ዘርፉ መቀዛቀዝ በማሳየቱ፣ በግንባታ ዕቃዎች ላይ ያለው ፍላጎት መቀነሱን ይገልጻሉ፡፡ በምርቶቹ ላይ ያለው ዋጋ እንደ ሌሎች መጠነኛ ጭማሪ እየታየ የመጣ ቢሆንም፣ ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ ያለው የዋጋ ጭማሪ ግን ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በእያንዳንዱ ምርት ላይም ከእጥፍ በላይ ጭማሪ መታየቱን ገልጸው፣ ከዚህ በፊት 500 ብር የነበረው ጋልቫናይዝድ የቤት ክዳን ቆርቆሮ በአሁኑ ወቅት ከ1,000 ብር በላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
‹‹ምክንያቱን መገመት አይቻልም፣ ነገር ግን ዋጋው በየቀኑ ጭማሪ እያሳየ ነው፡፡ በአቅርቦት በኩል ምንም ችግር የለም፤›› ሲሉ አቶ ሳሙኤል ያስረዳሉ፡፡ እንደ ቱቦላሬና አርማታ ብረት ያሉ የግንባታ ምርቶችም በተመሳሳይ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከፍተኛ እጥረት እንዳለበት የሚታይበት የሲሚንቶ ምርትም በየጊዜው ጭማሪ እያሳየ ነው፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሲሚንቶ ነጋዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ እስከ 720 ብር ደርሷል፡፡ በአንድ ወር ውስጥም ከ40 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ልማት ኢንስቲትዩት ሥር የነበረው የቆርቆሮና መሰል ብረታ ብረት ምርቶች፣ እንዲሁም በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሥር ሲሰመራ የነበረው የሲሚንቶ ምርት በማዕድን ሚኒስቴር ሥር እንዲመሩ ተደርገዋል፡፡
በዚህ መሠረት ለግንባታ ግብዓቶቹ ዋጋ ጭማሪ ምክንያትና የምርት ሒደቱን በተመለከተ ከማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት ቢሞከርም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡
በኢትዮጵያ ከ500 በላይ ከፍተኛና መካከለኛ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ያሉ ሲኖሩ፣ በዓመት 11.3 ሚሊዮን ቶን ብረታ ብረት የማምረት አቅም ቢኖራቸውም በግብዓት እጥረት ምክንያት ከአቅማቸው 20 በመቶ በታች እያመረቱ ናቸው፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ደግሞ ዓመታዊ የማምረት አቅማቸው 13 ሚሊዮን ቶን ቢሆንም፣ በማምረት ላይ የሚገኙት ስምንት ሚሊዮን ቶን ብቻ ነው፡፡