Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመጀመርያው የአዲስ አበባ ከተማ ጉባዔ የግልጸኝነት ጥያቄ አስነሳ

የመጀመርያው የአዲስ አበባ ከተማ ጉባዔ የግልጸኝነት ጥያቄ አስነሳ

ቀን:

አፈ ጉባዔዋ ማስጠንቀቂያ ሰጡ

መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም. የተመሠረተው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት፣ ከአምስት ወራት በኋላ ለሁለት ቀናት ማለትም የካቲት 3 እና 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደ መደበኛ ጉባዔ ላይ የምክር ቤቱ አባላት አስተያየት ለመስጠት የተሰጣቸው ዕድል የግልጽነት ጉድለት አለበት የሚል ጥያቄ አስነሳ፡፡

በምክር ቤቱ ጥያቄ የተነሳው፣ በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ / ቡዜና አልቃድር እየተመራ የተካሄደው የምክር ቤቱ ጉባዔ፣ የከተማ አስተዳደሩ የስድስት ወራት አፈጻጸም አሥራ አምስት ገጽ ሪፖርት በከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በንባብ ከቀረበ በኋላ፣ የምክር ቤት አባላት አስተያየትና ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል በተሰጠበት አካሄድ ምክንያት ነው፡፡

አፈ ጉባዔዋ ለመጀመርያ ዙር ዕድል የተሰጣቸውን አባላት ስማቸውን እየጠሩ በቀረበው ሪፖርት ላይ አስተያየትና ያላቸውን ጥያቄ እንዲያቀርቡ ዕድል ሰጥተው፣ የመጀመርያው የምክር ቤት አባል ጥያቄያቸውን ካቀረቡ በኋላ፣ ፈትያ መሐመድ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል መናገሪያቸውን በማብራት የተናጋሪዎች ዕድል አሰጣጥ ላይ ተቃውሟቸዋን አሰምተዋል፡፡

የምክር ቤት አባሏ፣ ‹‹አካሄድና የግልጸኝነት ጉድለት›› በማለት ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ ‹‹በፍላጎት ወይም በውይይት የሚሰጥ ዕድል መቆም አለበት፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ፈትያ ከሕዝብ ዘንድ እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ተጠይቀው፣ አስፈጻሚው አካል በተገቢው መንገድ አብራርቶ መተማመን መፈጠር እንዳለበት ከተናገሩ በኋላ፣ ‹‹የሽወዳ ዘመን ሊደገም አይችልም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይኼ ዘመን የብልፅግና ዘመን ነው፡፡ የኢሕአዴግ ዘመን አይደለም፤›› ያሉት የምክር ቤት አባሏ፣ ለውጥ የመጣውም፣ ‹‹በብዙ የሕይወት፣ የደምና የአጥንት መስዋዕትነት›› እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የምክር ቤት አባላት ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚደርስ የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥያቄ ይዘው እንደተቀመጡ በመግለጽም፣ ‹‹እዚህ የመጣነው ዕድር ልንሰበስብ፣ ወይም ዕቁብ ልንሰበስብ፣ ወይም ማኅበር ልንጠጣ አይደለም፤›› በማለትም ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት አስተያየትና ጥያቄያቸውን ለማቅረብ የሚሰጣቸው ዕድል አግባብነት ባለው መልኩ እንጂ፣ እከሌ እከሌ ተብሎና ተመርጦ ስም ተዘርዝሮ መሆን እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡ አክለውም፣ ሁሉም የምክር ቤት አባል ዕድል አግኝቶና ውይይት ተደርጎ አጀንዳዎች ላይ መተማመን እንዲኖርም አሳስበዋል፡፡

ለምክር ቤት አባሏ ቅሬታ መልስ የሰጡት አፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ ቡዜና ዕድል እየተሰጠ ያለው የምክር ቤት አባሏ ፈትያ ቅሬታ ባቀረቡበት መንገድ እንዳልሆነና ሁሉም አባላት ጥያቄ የማንሳት መብታቸው የተጠበቀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ተመልሼ እመጣለሁ ብዬ ነው የመጀመርያ ዙር ዕድል የሰጠሁት፣ ሰፊ ጊዜ ወስደን በዚህ ሪፖርት ላይ እንወያያለን፤›› ያሉት አፈ ጉባዔዋ፣ የአካሄድ ችግር አለመኖሩን ገልጸው፣ ውይይቱ በቀጣዩ ቀንም መቀጠል እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ይሁንና የዕድል አሰጣጡ ፈትያ ቅሬታ ባነሱበት አንፃር የሚታይ ከሆነ ስህተት እንደሆነ አስረድተው መታረም እንዳለበት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

አፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ ቡዜና ይኼንን ተናግረው የምሳ ዕረፍት እስኪወጣ ድረስ የምክር ቤት አባላት በተሰጣቸው ቅደም ተከተል መሠረት ጥያቄና አስተያየት አቅርበዋል፡፡ ይሁንና ምክር ቤቱ ከምሳ ዕረፍቱ ተመልሶ ጉባዔውን ከመቀጠሉ በፊት አፈ ጉባዔዋ ጉዳዩን በማንሳት በድጋሚ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

የምክር ቤት አባሏ የሰጡት የአካሄድ አስተያየት፣ የምክር ቤት አባላትን ስብዕና በሚነካ መልኩ መቅረቡን የተናገሩት ወ/ሮ ቡዜና፣ በአፈ ጉባዔ ዕድል ሳይሰጥ ንግግር መጀመር እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ ይኼ ድርጊት በምክር ቤቱ የአስተዳደር ደንብ መሠረት የሚያስቀጣ መሆኑን በመጥቀስም፣ ድርጊቱ ቢደገም ቅጣት እንደሚያስከትል በመናገር አስጠንቅቀዋል፡፡

በምክር ቤቱ የመጀመርያ ቀን ውሎ 17 የምክር ቤት አባላት ዕድል ተሰጥቷቸው፣ በስድስት ወራት አፈጻጸሙ ላይ ጥያቄና አስተያየት ካቀረቡ በኋላ፣ አፈ ጉባዔዋ አስተያየትና ጥያቄ የመቀበል ሒደቱ መጠናቀቁን በመግለጽ የዘርፍ ኃላፊዎች መልስ እንዲሰጡ መድረኩን ክፍት አድርገዋል፡፡

ለጥያቄና አስተያየት ዕድል ያልተሰጣቸው የምክር ቤት አባሏ ፈትያ ግን በድጋሚ መናገሪያቸውን በማብራት፣ ‹‹የተከበሩ አፈ ጉባዔ አሁንም ዕድል አልተሰጠም፤›› ብለዋል፡፡ ይኼንን ተከትሎ አፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ ቡዜና፣ ‹‹ሥነ ምግባር›› በማለት ቢናገሩም፣ የምክር ቤት አባሏ፣ ‹‹እየታፈንኩ ስለሆነ ነው፤›› ብለው ቀጥለዋል፡፡ ቢሆንም አስቀድሞ በተሰጠው ዕድል መሠረት ጥያቄና አስተያየት ተጠናቆ ወደ ምላሽ የመስጠት ሒደቱ ቀጥሏል፡፡

በጉባዔው የመጀመርያ ቀን ውሎ የዘርፍ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተው ሳያጠናቅቁ በመምሸቱ ጉባዔው በነጋታው እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ ነገር ግን፣ ‹‹ዕድል አልተሰጠኝም፤›› የሚል ቅሬታ ባነሱት የምክር ቤት አባሏ ፈትያ አማካይነት በጉባዔው ውስጥ የተነሳው ጉዳይ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ቀጥሏል፡፡

የምክር ቤት አባሏ በፌስቡክ ገጻቸው በምክር ቤቱ ውስጥ ስለተፈጠረው ሁነት ገልጸው፣ ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ እየሄድን እንደሆነ ባላውቅም፣ የሕዝብ ተወካዮች ጥያቄ እንዳያቀርቡ በማፈን፣ በቀጥተኛ ሁኔታ መድረክ መከልከልና ዛቻ የተቀላቀለበት ነበር፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በቀጥታ ሲተላለፍ የነበረው የምክር ቤቱ ጉባዔ መቋረጡን በማንሳት፣ ምክንያቱ ግልጽ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህ አካሄድ ጁንታን ከሰሜን ነቀልን ስንል፣ ማንም አይጠይቀኝ የሚል ጁንታን መሀል አዲስ አበባ መትከል እንዳይሆን ያሳስበኛል፤›› ያሉት የምክር ቤት አባሏ አክለውም፣ ‹‹የፖለቲካ ጥያቄን ወደ ሠለጠነው ምክር ቤት ማምጣት፣ የጎዳና ፖለቲካን ወደ ሠለጠነ አዳራሽ ፖለቲካ ለማምጣት ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም፤›› የሚል ጽሑፍ አጋርተዋል፡፡ ፈትያ በከተማው ጉዳይ ላይ ያሏቸውን ሌሎች ሐሳቦች በተለያየ ጊዜ ወደፊት በተከታታይ እንደሚያቀርቡ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል፡፡

ምሽቱን በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ሲዘዋወር ያመሸው የምክር ቤት አባሏ የፌስቡክ ጽሑፍ በማግሥቱ ጠዋት ስብሰባው በተደረገበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀድመው በተገኙ የምክር ቤቱ አባላት ዘንድም መነጋገሪያ ነበር፡፡ የምክር ቤት አባላት የፈትያን ደኅንነትን አስመልክተው ሲነጋገሩና የምክር ቤት አባሏ ያላቸውን ያለመከሰስ መብትን ጠቅሰው ሲወያዩ ተስተውሏል፡፡

የምክር ቤት አባሏ ፈትያ መሐመድ ለሁለተኛ ቀን የተካሄደውን የምክር ቤቱን አንደ መደበኛ ጉባዔ እስከ ግማሽ ቀን ተሳትፈዋል፡፡

ምክር ቤቱ የሁለተኛ ቀን ውሎውን የጀመረው ከመጀመርው ቀን የቀጠለውን የዘርፍ ኃላፊዎች ምላሽ በማዳመጥ ሲሆን፣ ይኼ ሲጠናቀቅ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ለሁለት ሰዓት ገደማ የዘለቀ አጠቃላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ቀጥሎ አፈ ጉባዔዋ የስድስት ወራት የአፈጻጸም ሪፖርቱን ለማፅደቅ ድምፅ እንዲሰጥ ቢጠይቁም፣ ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) የተባሉ የምክር ቤት አባል መናገሪያቸውን በማብራት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡

በጥያቄ ማቅረቢያው ጊዜ ከምክር ቤት አባላት መካከል የመጀመርያ ዕድል አግኝተው ጥያቄ ያቀረቡት ሲሳይ (ዶ/ር) ቅሬታቸውን ያነሱት በኃላፊዎች የተሰጡ ምላሾች ላይ የምክር ቤት አባላት በድጋሚ ማብራሪያ እንዲጠይቁ ዕድል ሳይሰጥ ሪፖርቱ ሊፀድቅ መሆኑን ተቃውሞው ነው፡፡

የምክር ቤት አባሉ ዕድል ሳይሰጣቸው መናገራቸውን ተከትሎ በአፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ ቡዜናና በምክር ቤት አባሉ መካከል ምልልስ ታይቷል፡፡ አፈ ጉባዔዋ ዕድል ሳይሰጥ መናገር እንደሚከለከል ሲናገሩ ሲሳይ (ዶ/ር) ደግሞ እጃቸውን ቢያወጡም ዕድል እንዳልተሰጣቸው በመጥቀስ መናገሪያቸውን ለማብራት መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡ ይሁንና አፈ ጉባዔዋ የምክር ቤት አባሉ ሪፖርቱ ላይ ያላቸውን ተቃርኖ ድምፅ ሲሰጥ እንዲገልጹ አሊያም ለአፈ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት በጽሑፍ እንዲያስገቡ በመናገራቸው ሪፖርቱን የማፅደቅ ሒደቱ ቀጥሏል፡፡

በተሰጠው ድምፅ መሠረትም ሪፖርቱ በጉባዔው ላይ ከተገኙት 105 የምክር ቤት አባላት መካከል 101 ያህሉ ድጋፍ ሰጥተውት ፀድቋል፡፡ ሪፖርቱ አንድ ተቃውሞና ሦስት ድምፀ ተዓቅቦ የተሰጠበት ሲሆን፣ ድምፀ ተዓቅቦ ካደረጉት የምክር ቤት አባላት መካከል አንዱ ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ከሰዓት በኋላ በቀጠለው የምክር ቤቱ ውሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች 2014 .ም. የመጀመርያ ስድስት ወራትቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ሪፖርቱ ቀርቦ ለጥያቄና አስተያየት ዕድል ሲሰጥ ካሳ ተሻገር (ዶ/ር) የተባሉ የምክር ቤቱ አባል፣ ‹‹የጉባዔው ቀጥታ ሥርጭት ለምን ተቋረጠ፤›› የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ውይይት እየተደረገ ያለው ፍርድ ቤቶች የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት እንጂ የአስፈጻሚ አካሉ ሪፖርት ባለመሆኑ ይኼ ጥያቄ ከአጀንዳው ውጪ መሆኑን በመናገራቸው ጥያቄው ሳይመለስ ቀርቷል፡፡

የምክር ቤት አባሉ ጥያቄውን ያነሱት የምክር ቤቱ አስተዳደር ደንብ ላይ ተመሥርተው መሆኑን ለሪፖርተር የተናገሩት ካሳ (ዶ/ር)፣ ደንቡ ጉባዔው ሲካሄድ ለሕዝብ በግልጽ መቅረብ እንዳለበት እንደሚደነግግ አስረድተዋል፡፡

ለሁለት ቀናት የዘለቀው ጉባዔ የፍርድ ቤቶች የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከተወያየ በኋላ፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ማስለቀቅና ካሳ ጉዳዮች አቤቱታ ሰሚ ጉባዔን ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ ደንብን አፅድቆና የቋሚ ኮሜቴ ሰብሳቢና አባላት ሹመት ሰጥቶ ተጠናቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...