ዓለም አቀፍ የሒሳብ አያያዝ (IFRS) ምን ያህል ተቋማት እየተገበሩ እንደሆነ መረጃው እንደሌለው፣ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አስታወቀ።
ዓለም አቀፍ መሥፈርትን ያሟላ የሒሳብ አያያዝ፣ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ፣ እንዲሁም የኦዲት አሠራርን በግል ንግድ ድርጅቶች፣ በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ለማስተግበር በአዋጅ ቁጥር 847/2006 የተቋቋመው ቦርዱ፣ አሠራሩን ተግባራዊ የሚያደርጉ ተቋማትን ምዝገባና ክትትል ማድረግ በዋናነት የተሰጠው ኃላፊነት ነው።
በዚህ መሠረትም ከሦስት ዓመታት በፊት በአጠቃላይ 1,800 ድርጅቶች ዓለም አቀፍ የሒሳብ አያያዝን ተግባራዊ ማድረጋቸውን መረጃ እንደነበራቸው የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሒክመት አብደላ፣ ‹‹ብሔራዊ የሒሳብ አያያዝ ቀን›› ዓርብ የካቲት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በተከበረበት ወቅት ገልጸዋል።
አተገባበሩን በተመለከተ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለበት የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በአሁኑ ወቅት በምን ያህል ተቋማት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ የሚያሳይ መረጃ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
በቦርዱ የተቀናጀ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ባለመኖሩ፣ ከዚህ ቀደም የሒሳብ አያያዙን የጀመሩት ተቋማትም በምን ያህል ደረጃ እየተገበሩት እንደሚገኙ ማወቅ አለመቻሉን አክለዋል።
በግል ተቋማት ዓለም አቀፍ የሒሳብ አያያዝን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ለመተግበር አስቸጋሪ እንደሆነ የግል ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል። ትግበራው ከፍተኛ ወጪ የሚያስፈልገው በአገር ውስጥ በቂ ባለሙያ ባለመኖሩ ምክንያት እንደሆነ የሚገልጹት ወ/ሮ ሒክመት፣ ያሉት ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ መሥፈርቱን ማሟላታቸውን መለየት የሚያስችል ማረጋገጫ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ባለሙያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያገኙበትና ሙያዊ ማረጋገጫ አግኝተው፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላ የሒሳብ አያያዝን የሚሠሩበትና ሪፖርት የሚያዘጋጁበትን አቅም የሚፈጥር ተቋም እንዲኖር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች እንዲኖሩም ራሱን የቻለ ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም የሚጠይቅ ሰነድ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ወ/ሮ ሒክመት አስረድተዋል።
ዓለም አቀፍ የሒሳብ አያያዝን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚጠበቁት የግል ድርጅቶች ዓመታዊ ገቢያቸውን፣ ዕዳቸውን፣ የሰው ኃይላቸውንና ጠቅላላ ሀብታቸውን መሠረት በማድረግ ሲሆን፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ደግሞ በዓለም አቀፍ ተቋማት የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት (IPSAS) መሠረት እንደሚሠሩ ወ/ሮ ሒክመት ተናግረዋል።