Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮ ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ በተያዘው ዓመት ዕውን ይሆናል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአሥር ዓመታት በፊት በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ትስስር ዕውን ለማድረግ፣ 1.3 ቢሊዮን ዶላር በሚደርስ ወጪ ግንባታው የተጀመረው ፕሮጀክት በተያዘው ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ከዓለም ባንክና ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ድጋፍና በሁለቱ አገሮች በሚሸፈን ወጪ ግንባታው የተጀመረው ፕሮጀክት፣ ከኢትዮጵያ በኩል ተገቢው ሥራ ተሠርቶ ቢጠናቀቅም፣ በኬንያ በኩል ያልተጠናቀቁ ሥራዎች ፕሮጀክቱን እንዳዘገዩት በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

የገንዘብ ሚኒሰቴር ዴኤታ በሆኑትዮብ ተካልኝ (/ር)፣ የተመራ ልዑክ ባላፍነው ሳምንት ከኬንያ የኢነርጂ ሚኒስቴር ሞኒካ ጁማ (አምባሳደር) ጋር በሁለቱ አገሮች የኃይል አቅርቦት ትብብር ላይ ፍሬያማ ውይይት እንዳካሄደ ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የውይይቱን ዝርዝር ይዘቶች በስፋት ማንሳት እንደማይቻል ተናግረው፣ ሆኖም በአጠቃላይ በሁለቱ አገሮች መካከል በአፍሪካ ልማት ባንክ ፋይናንስ የሚደረግ ከአንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታን ተከትሎ ወደ ሥራ የሚገባ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት እንዳለ አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል የኃይል መስመር ዝርጋታው ከዓመት በፊት ተጠናቆ የመሠረተ ልማት ግንባታው መስመር ዝርጋታና ማሽን ገጠማ ሥራው በአግባቡ እንዲፈተሸ መደረጉን የገለጹት አቶ ሞገስ፣ በኬንያ በኩል የሚቀረው የተወሰነ ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ሊጠናቀቅ ይገባል፡፡ በኬንያ በኩል መጠናቀቅ የሚገባው ሥራ ስላልተጠናቀቀ ፕሮጀክቱ ለመዘግየቱ ተጠቃሹ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በመስከረም ወር ከኬንያ የመጡ የልዑካን ቡድኖች ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረው እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ በወቅቱ ከተነሱት ጉዳዮች ውስጥ በተቻለ መጠን በኬንያ በኩል የዘገየው ሥራ እንዲፋጠን የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡

ከዚያ ባሻገር ከኦፕሬሽን አንፃር የኃይል ሽያጭ ታሪፍ ስምምነቱ ምን ያህል ይሆናል? የሚለው ላይ ክለሳ ማድረግ ስለሚያስፈልግ፣ ይህ ጉዳይ እስካሁንም ድረስ ያልተቋጨና በሒደት ላይ ያለ ጉዳይ እንደሆነ አቶ ሞገስ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ናይሮቢ በማቅናት የተደረጉትን ንግግሮች አስረድተው፣ በውይይቶቹም የተደረጉት ፍሬያማ ውይይቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ የኃይል ሽያጭ ታሪፍ ስምምነቱን በተመለከተ የተደረጉት ንግግሮች እስካሁን ድረስ ያልተቋጩ ጉዳዮች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በኋላ የሚኖረው ጉዳይ የዘገየውን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግንባታ በቀጣዮቹ ወራቶች ውስጥ እንዲጠናቀቅ ማድረግ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ሐሳብ፣ ‹‹ከውይይቶቹና ከኬንያ ባለሥልጣናት ጋር በነበረው ግንኙነት እንደተረዳነው፣ እ.ኤ.አ. በ2022 አጋማሽ ወይም የተያዘው የበጀት ዓመት ሳይጠናቀቅ አስፈላጊ ጉዳዮች ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡››

በኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይልና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መካከል በተደረሰው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት 1,068 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የሚገነባ  ሲሆን፣ ከአሥር ዓመት በፊት በተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያ 400 ሜጋ ዋት ኃይል ለኬንያ ወጥ በሆነ የ0.07 ዶላር በኪሎዋት እንድታቀርብ ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች