የአልጄሪያውን ጂኤስ ካቢሌ ክለብ፣ ባለፈው ሐምሌ 2013 ዓ.ም. ተቀላቅሎ የነበረው ኢንተርናሽናል ተጫዋቹ ሙጂብ ቃሲም ከክለቡ ጋር መለያየቱ ተሰምቷል፡፡ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዓምና አሸናፊ የፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ የፊት መስመር ተጨዋች የነበረው ሙጂብ፣ ለመንፈቅ ከቆየበት የአልጄርያው ክለብ የለቀቀበት ምክንያት ክለቡ ባጋጠመው የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ የተለያዩ ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ሙጂብ ቃሲም በአሁኑ ወቅት ሁሉንም ነገር ትቶ በአዲስ አበባ ይገኛል፡፡ በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ የዋሊያዎቹ ተሠላፊ የነበረው የ26 ዓመቱ ሙጂብ ቃሲም ከጂኤስ ካቢሌ በፊት ለፋሲል ከነማ፣ ለአዳማ ከተማና ለሐዋሳ ከተማ ክለቦች መጫወቱ ይታወቃል፡፡