Saturday, February 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ የበረታው ጥያቄ

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ የበረታው ጥያቄ

ቀን:

የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው የአገሮች  ወርኃዊ ደረጃ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከነበረበት አንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ 138ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡ ለቡድኑ ውጤቱ ማሽቆልቆል እንደ ምክንያት የተጠቀሰው ባለፈው ሳምንት በቴራንጋዎቹ አናብስት የበላይነት በተጠናቀቀው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ያስመዘገበው ደካማ ውጤት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በዋሊያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተና ረዳቶቻቸው ላይ በዋናነት መገናኛ ብዙኃኑን በመጠቀም የሚደመጠው ትችትና ተቃውሞም እንደቀጠለ ይገኛል፡፡  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ በጉዳዩ የደረሰበትን ድምዳሜ ይፋ ባያደርግም፣ በዚሁ ሳምንት ብሔራዊ ቡድኑ በካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶና ኬፕ ቨርዴ ጋር ያደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ምን ጠንካራና ደካማ ጎን እንደነበረው፣ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ በመንተራስ መገምገሙ ተሰምቷል፡፡

ፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይ በሚኖሩት አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ ምን ማድረግ እንዳለበት አቅጣጫዎችን ማስቀመጡ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ለአፍሪካ ዋንጫ ሲዘጋጅ የቆየው ብሔራዊ ቡድኑ ቀደም ሲል ዋና አሠልጣኙ በሰጡት መግለጫ፣ ከምድብ ማለፍ የዕቅዱ አንደኛው አካል ነበር፡፡ ለዚህም ሲባል ነበር ቡድኑ ቀድሞ ወደ ካሜሩን ያቀናው፡፡ ይሁን እንጂ አሠልጣኙና ስብስባቸው  የመጀመርያ ተሰናባቸው መሆናቸው ይታወሳል፡፡

አሠልጣኙ በመግለጫቸው ለቡድናቸው ውጤት ማጣት መሠረታዊ ችግር ሲሉ  የተናገሩት፣ ቃል በተገባላቸው መሠረት የወዳጅነት ጨዋታ ማግኘት አለመቻላቸው፣ ካሜሩን ከገቡ በኋላ ደግሞ በርከት ያሉት ተጨዋቾቻቸው በኮቪድ-19 ምክንያት ተሟልተው ልምምድ ለመሥራት ተቸግረው እንደነበር ነው፡፡ አሠልጣኙ ማብራሪያ በሰጡበት መድረክ ላይ ከ‹‹ዕቅድ›› ጋር ተያይዞ ለፌዴሬሽኑ ይህ ጥያቄ ቀርቦለት ይቅርታ ማለቱ፣ አሠልጣኙስ ለምን አልጠየቁም? የሚል ቅሬታም ሆነ ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም፡፡

ከቅሬታ አቅራቢዎች መካከል አንዱ ነዋሪነታቸው በአሜሪካ የሆነው አቶ መዝሙረ ዳዊት ናቸው፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ላይ እያለ፣ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም ሙያተኞች ዋና አሠልጣኙን እንዲያማክሩ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አማካይነት ጥያቄ እንደቀረበላቸው የሚገልጹት አቶ መዝሙረ ዳዊት፣ በአሠልጣኙ እምቢተኝነት ሙያዊ ዕገዛ ማድረግ እንዳልቻሉ ተደምጠዋል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይ ለሚያደርጋቸው አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ጠንክሮ ለመቅረብ የሚያስችለውን ሙያዊ አገልግሎት በነፃ ለመስጠት፣ ያዘጋጁትን ምክረ ሐሳብ ለፌዴሬሽኑ ማቅረባቸውን የሚገልጹት አቶ መዝሙረ፣ እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ አላገኘሁም ሲሉ አሠልጣኙንና የፌዴሬሽኑ አሠራር ይተቻሉ፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ በሚጠናከርበት መንገድ ላይ በአሜሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የተለያዩ ሙያተኞች ጋር መመካከርና አጋዥ የሆኑ ሐሳቦችን በግብዓትነት መውሰድ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን የቆየ አሠራር መሆኑን የሚገልጸው ፌዴሬሽኑ በበኩሉ፣ አቶ መዝሙረ ዳዊትም በዚሁ መሠረት ብሔራዊ ቡድኑ በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ ሙያዊ የሐሳብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ መወያየታቸውን የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ይናገራሉ፡፡

ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ የሚደረገውን መደበኛ ዝግጅት ከመጀመሩ በፊት፣ በፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አማካይነት አቶ መዝሙረ ዳዊትን ጨምሮ ሌሎችም ሙያተኞች በፍላጎት ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ድጋፍ እንዲሰጡ ካልሆነ ፌዴሬሽኑ ‹‹ብሔራዊ አሠልጣኙን በዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ድጋፍ ማድረግ ትችላላችሁ፤›› በሚል በደብዳቤ የተደገፈ ማረጋገጫ አለመስጠቱን የሚናገሩት አቶ ባህሩ፣ ‹‹ለብሔራዊ ቡድኑ ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ እንዳልችል ተደርጌያለሁ የሚሉት ሙያተኛ የዋና አሠልጣኙ አለቃ ለመሆን የሚሄዱበትን ዝንባሌ ትተው፣ ሙያዊ የሐሳብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ከተነገራቸው በኋላ በዝግጅት ወቅት ምንም ዓይነት ተሳትፎ ያልነበራቸው ናቸው፤›› ይላሉ፡፡

ቅሬታ አቅራቢው ‹‹ለፌዴሬሽኑ ምክረ ሐሳብ አቅርቤ ተቀባይነት አላገኘሁም፤›› የሚሉትን ጉዳይ በተመለከተም ምክረ ሐሳቡ ሊይዛቸው የሚገቡ ቁም ነገሮችና ቅርፅ ምን መምሰል እንዳለበት እንኳ በውል የማይገልጽ ፕሮፖዛል ብለው በቁራጭ ወረቀት ለፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ማስገባታቸውን ግን አቶ ባህሩ አልሸሸጉም፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት በሚቀጥለው ዓመት 34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያከናውናል፡፡ የማጣሪያ ጨዋታዎችም በቅርቡ እንደሚከናወኑ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም ለብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎቱ ያላቸው አቶ መዝሙረ ዳዊትን ጨምሮ፣ ሙያዊ የሐሳብ ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ የፌዴሬሽኑ በር ክፍት መሆኑን አቶ ባህሩ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከህወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ

የፌዴራል መንግሥትና የህወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር...

ማስተካከያ

በሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትም...

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...