Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበህፀፅ የተሞላው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ምርጫና ምልመላ

በህፀፅ የተሞላው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ምርጫና ምልመላ

ቀን:

በቢንጎ አ.

ሰሞነኛው የአገራዊ የምክክር መድረክ አመቻች ኮሚሽነሮችን የስም ዝርዝር ከኬንያ ወደ አዲስ አበባ ለማስፈር ናይሮቢ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የመጨረሻ መሰናዶ አድርገን የኢትዮጵያ አየር መንገድን የበረራ ጅማሮ በመጠበቅ ላይ ሳለን፣ ከቀድሞ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች በርዝመቱ ‹‹ጠዊል›› እያልን የምንጠራው የአሁኑ ጡረተኛ ካፒቴን ከረጅም ወራት በኋላ ለኮቪድ ምሥጋና ይግባውና ተገናኘን፡፡ ትንሽ ስለጡረታ ዘመን ካወጋን በኋላ የእጅ ስልኩን ብድግ አድርጎ፣ “ምነው እዚህ ዝርዝር ውስጥ ስምህን አላየሁትም” ብሎ ስልኩን አቀበለኝ፡፡ ዝርዝሩን በአርምሞ ተመልክቼ ስጨርስ እውነትም ‹‹ጠዊል›› ያለው ውስጠ ወይራ ውል ብሎ ታየኝ፣ እንዲህም አልኩኝ ፡፡

‹‹እንኳን ያንቺ ፍቅር ተጨምሮበት

እንዲሁም ከባድ ነው ሰኔና ግንቦት››

ወዲያውም የዛሬ አራት ዓመት ገደማ በኦስካር የፊልም ሽልማት ላይ ተነስቶ የነበረው ውዝግብ ውልብ አለኝ፡፡ ዳይሬክተር የነበረው ፋዬ ዱናዊይና ዋርን ቤቲ የተሸላሚ ፊልም ስም ለመጥራት ስቴጅ ላይ ቆመዋል፡፡ በፕሮግራሙ መሠረት ቤቲ የአሸናፊውን ፊልም ስም ለመጥራት ኤንቨሎፑ ከፈተ፣ ከዚያም በመቀጠል፣ ‹‹የዚህ አካዳሚ አሸናፊ…›› የታዳሚውን ጉጉት ለመሳብ ዝም፣ ቀና፣ ፣ቀስ፣ እንደገና ቀና፣ ዝም ይላል፡፡ ከኤንቨሎፑ ውስጥ የወጣውን ካርድ ያያል፣ እንገደና ወደ ዱናዊይ ይመለከታል፣ እንደገና በአድናቆት በማሞገስ ‹‹ታላቅ ሰው ነሽ›› ብሎ ወደ ኤንቨሎፑ ያቀርባታል፣ ቀጥሎም ካርዱን ያሳያታል…

ዱናዊይ እጅግ በጣም ጮክ ብላ ‹‹ላ ላ ላንድ›› ብላ የአሸናፊውን ፊልም ስም ጠራች፣ ሆኖም ግን አሸናፊው የቤሪ ጀኒክስ ‹‹ሙን ላይት‹‹ የሚለው ምርጥ ፊልም ነበር፡፡ በኋላም የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ሳንድራ ጎንዛሌዝ ‹‹A Timeline of a Historic Oscar Blunder›› ብላ ዘገበችው… የእኛንም ጉድ እስቲ እንቃኘው፡፡

የአገራዊ ምክክር ጽንሰ ሐሳብ ለዘመናት  ሲወርድ ሲዋረድ  ለመጡ፣ እያወዛገቡ ላሉና ወደፊት ኅብተሰባችንን እጅግ አታካችና ውስብስብ ከሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ከባቢያዊ፣ የታሪክ ትርክቶችና ያጠሉት አደጋ፣ በአገራዊ ምልክቶችና የጀግንነት ዓውዶች፣ የሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው የሕገ መንግሥት ጽንሰ ሐሳብና ተግዳሮቶች ላይ በስፋትና በጥልቀት ሁሉንም አካል ያሳተፈ፣ ቀና እና ተስፋ ሰጪ የሆነ አገራዊ ምክክር ነው፡፡

የአገራዊ ምክክር ሒደቱ ዓላማዎች ወደፊት በጥልቀት መዘርዘር ያለባቸው ሰፊ ጽንሰ ሐሳቦች ሆነው ሳለ በግርድፉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን እያወዛገቡ ያሉ ሥር የሰደዱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ደረጃ በደረጃ በቅደም ተከተል ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በማምጣት የሚፈቱበትን መድረክ በማዘጋጀትና በማመቻቸት የጋራ መግባባት ይደርስ ዘንድ በትጋት ማከናወን ነው፡፡ ለአንድ አገራዊ ምክክር ወሳኝ ከሚባሉት መሥፈርቶች ዋናውና ቀዳሚው ከምንም ወገን ጣልቃ ገብነት ነፃና ገለልተኛ የሆነ ተቋም እንዲመራው ማድረግ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችን ልብ ለልብ ተቀራርበው በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ፣ ባለውና ወደፊት በሚጠብቁን ጉዳዮች ዙሪያ ጥልቅ ውይይት ማድረግን ይጠይቃል፡፡

የአገራዊ ምክክሩ ሁለት ዓበይት ውጥኖች አገር በቀል የመሆናቸውና አፅንኦት የሚሰጡት በመፃኢ ዕድላችን ላይ ተስፋ ሰንቀው ምክክር ማድረግ ነው፡፡ አገራዊ ምክክር እርቅና ሰላም ለማምጠት  መንገድ ከፋች እንጂ በራሱ ድርድር፣ እርቀ ሰላም፣ ወይም ሽምግልና አይደለም፡፡ በአገራችን ይታዩ ስለነበሩ ታሪካዊና ነባራዊ ግጭቶች፣ የሰላም፣ የእርቅ፣ የሽምግልናና የድርድር ፋይዳ እጅግ ወሳኝ ወቅታዊና በተጓዳኝ የሚሄድ ቢሆንም፣ ከሁሉም በፊት ግን አገራዊ ምክክር ትልቅ አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡

የአንድን አገራዊ ምክክር መድረክ ጽንሰ ሐሳብ፣ ዝግጅት፣ ሒደት፣ ትግበራና ግብረ መልስ የተቃና እና ስኬታማ ከሚያደርጉት ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ተሳትፎ፣ የአጀንዳ ይዘትና ጥራት፣ የፕሮግራም ቀረፃና ቅደም ተከተል፣ ውስጣዊና ውጫዊ ጣልቃ ገብነትን መከላከል፣ የምክክር ሒደቱ ቀጣይ ሒደትና ዘለግ ያለ መልክ እንዲይዝ ማድረግ፣ ብቃትና ተዓማኒነት ያለው፣ ከአድልዎ ነፃ የሆነና ገለልተኛ አወያይ እንዲኖር ማስቻል፣ እንዲሁም አሳታፊና አካታች መሆን ናቸው፡፡

ከእነዚህ ሁሉ አንኳር የስኬት ምልከታዎች ዋናውና ከሌሎች አገሮች ልምዶች ልንማር የሚገባን ግልጽ የሆነ አደራን የሚሰጥ/የሚጥል (Clear Mandate)፣ በአግባቡ የተቋቋሙ የአሠራር ንድፈ ሐሳብ (Tailored Structure) ወሳኝ ሲሆኑ፣ ይህንን ጽንሰ ሐሳብ አፅንኦት በመስጠት ይመስላል መንግሥት የአገራዊ ምክክር መድረክ አመቻች ኮሚሽን በአዋጅ ያቋቋመው፡፡ በመሠረቱ የዚህ የአገራዊ ምክክር አመቻች ኮሚሽን ውጥን ቀደም ሲል የተለያዩ ስምንት አገር በቀል ተቋማት መንግሥትንም በሰላም ሚኒስቴር ውክልና ያሳተፈው፣ የሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር መድረክ ውጥን ኢትዮጵያ በመባል የሚታወቀው ‹‹MIND Ethiopia›› (Muliti Stakeholders Initiative for National Dialogue in Ethiopia) ቅድመ ዝግጅት ‹‹ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት›› ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ነው ብለን እንለፈው፡፡ ታድያ በዚህ ዕሳቤ አሁን እየተደረገ ያለው የኮሚሽነሮች ጥቆማ ላይ የታዩ ተግዳሮቶችን በግልጽና በገሃድ መወያየት (Dialogue About the Dialogue) የሚለውን ብሒል በአርምሞ እንዲገልጸው በሚል እምነት ይሁን፡፡ በቅድሚያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣው መሥፈርት ምን ይላል?

መሥፈርቶች

  ይህ ከላይ የተገለጸ መሥፈርት በምንና እንዴት ደረጃ/ሚዛን (Weigh) ተሰጠው?

 • ማን ምን አገኘ?
 • ማን ማንን ስለጠቆመ/ስላጩ እንዲመረጥ ሆነ?
 • መራጮች የተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ወኪል፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በታዛቢነት እንዲረግ ለምን ተፈለገ?
 • ምክር ቤቶቹ የገዥው ፓርቲ ወኪሎች/ በምርጫ ተወዳዳሪዎች አልነበሩምን?
 • ይህ ሒደት እንዴት ገለልተኛና ግልጽ ሊሆን ይችላል?
 • የሲቪል ማኅበረሰብ ወኪልና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክክር ቤት በዕጩ ተጠቋሚዎች ላይ ቅሬታቸውን ለምን በመግለጫ መልክ አላወጡም?
 • ገዥው ፓርቲ ለምን ራሱን ከዚህ ውጪ አያደርግም?

ይህ ተደጋጋሚ ድርጊት የጀንሰንትን ትልቅ ንግግር አስታወሰኝ፣ ‹‹Sometimes the Mistake isn’t The Problem, the lack of Remourse is the Real Mistake.”

ተጠቋሚዎች

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከየትኛውም ተጠቋሚ ጋር በግልም ሆነ በጋራ የሚያገናኘው ትውውቅም ሆነ ሌላ ውሎች የለውም፣ ሐሳቡና አስተያየቱም ሆነ ተቃውሞው ሒደቱ ከጅምሩ የፀዳ ሆኖ የሚታሰበው ዘላቂ ሰላም እውነት ይሆን ዘንድ ነው፡፡

ስብጥር

የዕጩ ተጠቋሚዎች ገጽታና ሰብዕና በግርድፉና ያልተሟላ ሆኖ ያገኘሁት ሲሆን፣ ብዙዎቹ ተጠቋሚዎች/ዕጩዎች ውጤቱ ከመታወቁ በፊትና ከመጠቆሚያው ቅጽ ጋር እንዴትና ለምን የትምህርትና የሥራ ማስረጃ (Curriculum Vitae-CV) እንዲያቀርቡ ተደረገ?

 • ለምን ሌሎች ተጠቋሚ ዕጩዎች (CV) እንዲያቀርቡ አልተደረገም?
 • በምን መመዘኛ ነው ከድርጅቶች የተጠቆሙ ዕጩዎች ብቻ እንዲመረጡ የተደረገው?
 • ከሕዝብ የተጠቆሙ ዕጩዎች ለምን አልተመረጡም?
 • ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን እከሌ፣ ከኮንሰልታቲቭ ፈርም እከሌ፣ ከኢትዮጵያ የሽምግልና ግልግል ካውንስል እከሌ፣ ወዘተ… ለምን ተወሰደና በማን ትዕዛዝ?
 • ቀደም ሲል ያልወጣ መሥፈርት ለምን እንደ ዋና መመዘኛ ተደረገ?
 • ለመሆኑ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽነሮች፣ የወሰንና ድንበር ኮሚሽነሮች እንዴት ሁለት ቦታ ኮሚሽነር ለመሆን ተመረጡ?
 • ኢትዮጵያችን ያሏት ሰዎች እነዚህ ብቻ ናቸው?

የፖለቲካ ተሳትፎ

በዕጩነት ከተጠቆሙት ግለሰቦች ውስጥ እስከ 13 የሚሆኑት ዕጩዎች ቀደም ባለው ሥርዓትም ይሁን አሁን ባለው ‹‹የብልፅግና ዘመን›› የማይናቅ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ናቸው፡፡ ለዚህ ይመስላል ግብግቡ በአነግ አባላት፣ በኢሕአዴግ፣ ብሎም በመኢሶን አቀንቃኞች በኩል የገመድ ጉተታው ፀንቶ የታየው፡፡ በተለይ ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የታየው መሯሯጥ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አምባሳደር መሪነት የታየው ሽኩቻና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ውስጥ የታዘብነው ዳንኪራ ‹‹ወይ አንቺ ኢትዮጵያ›› የሚያስብል ነው፡፡

የስሜቴ ለውጡ ምንድነው ሚስጥሩ?

ማስረጃስ ምን ይሆን ዕድል ለመኖሩ

ስሜትና ዕድልስ እውነታነት አለው?

ዕድል ወይስ ስሜት ቀዳሚው የቱ ነው?

(ከዕድል ዓለም ገበየሁ የተወሰደ)

ዜግነትና ዕድሜ

ቀረቡት ዕጩዎች ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ በዕድሜ ባለፀጋነታቸው፣ በተደራራቢ የግልም ሆነ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተጠሪ፣ ኃላፊ፣ እንዲሁም አባላት በመሆናቸው ሙሉ ጊዜያቸውን በዚህ ታላቅ የአገር አደራ ላይ ሊያውሉ የሚችሉ ከቶ አይደሉም፡፡ የተጠቋሚ ዕጩዎች አማካይ ዕድሜ 65 እና ከዚያ በላይ ሲሆን ሥራው የሚፈልገው እጅግ ፈጣን፣ ንቁ፣ ተደጋጋሚ ጉዞ፣ ስብሰባ፣ የማንቂያና የማቀራረቢያ ውይይቶችና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በአገራዊ ምክክሩ የኮሚሽነሮቹ ኃላፊነት የአመራር ብቃት በእጅጉ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ የፕሮግራምና የፕሮጀክት ሥራ አመራር ልምድን በቅጡ ይጠይቃል፡፡ ተጠቋሚ ዕጩዎች በእኔ ግምት ከ90 በመቶ በላይ ምናልባት ምክክሩን በሽምግልና፣ በአደራዳሪነትና በማግባባት ራስ ላይ ሊያግዙ የሚችሉ እንጂ የአገራዊ ምክክሩን በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ከመስበክ ያለፈ ሊያደርጉት የሚችሉት አስተዋፅኦ በጣም ኢምንት ነው፡፡

የአገራዊ ምክክሩን የጽንሰ ሐሳብ (Conceptual Clarity) ለማምጣት የዚህ ስብስብ ብቻ የራሱ የሆነ ጊዜ (Maturity Period) በትንሹ አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ ሊፈጅ ይችላል፡፡ ይህ ስብስብ ራሱን ወደ አንድ የተማከለ የአሠራር ቡድን (Team) ለመሆን ፈታኝና ዘለግ ያለ ጊዜ እንደሚፈጅበት አመላካች ነገሮች አሉት፡፡

ለመሆኑ ምክር ቤቱ ለምን ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ዕጩ ይጠቆም ብሎ ፓስፖርታቸውን የቀየሩ ሰባት ዕጩዎች እንዲካተቱ አደረገ? በአጠቃላይ ከተጠቆሙት 42 ዕጩዎች 13ቱ የፖለቲካ አቋም የነበራቸውና ያላቸው ሲሆኑ፣ ገለልተኝነታቸው በጉልህ ጥያቄ ውስጥ የሚገባና የዕጩነት መመዘኛን የሚፃረሩ ናቸው በተጨማሪም ዕጩዎች ኢትዮጵያዊ ፓስፖርታቸውን ‹‹የሸቀጡ›› በመሆናቸው በወጣው መሥፈርት እንኳን ብቻ በምንም ሁኔታ ሊካተቱ አይገባም፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ አፈ ጉባዔው የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎና የሚመሩት ተቋም ምን እየሠራ ነው? ጉድ አይሰማው የለ እርሳቸውም ሲጠየቁ፣ ‹‹እኔም ሊስቱን ሳይ ደንግጬ ነበር›› እንዳይሉን፡፡ የፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የፆታ ተማፅኖ ጥያቄና ውትወታም ብዙ ትኩረት ያገኘ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ከ42 ተጠቋሚዎች የሴቶቹ ቁጥር 3 ብቻ በመሆኑ፡፡

ልጠለለው እንጂ ከሀሩር ዝናቡ፣

እታገሰዋለሁ ያዝንልኛል ልቡ፣

በካሳ ትዝታ በባቲ ቅኝት፣

አርዓያ እንዳይሆን መስፍን ለሒሩት፣

አንዳርጌም ዘገየም ታግለው ላርነት፣

ምክክሩን መርጠው ከአምባሳደርነት፣

ምንም አል ታደለች ኢትዮጵያዊነት፣

የቲፎዞ ፍጥጫ

ህ አገራዊ ሒደት የሐሳብ ልዩነቶችን ከመፍታት ባሻገር በተሳታፊዎች መካከል መልካም ግንኙነት፣ የአንድ አገር ልጅነትን መንፈስ የማጎልበትና መተማመንን ሊያመጣ የታሰበ ዕቅድ እስከሆነ ድረስ ያ ለማንም ጣልቃ ገብነት እንዲካሄድ ማመቻቸትና ድጋፍ መስጠት የሚገባው መንግሥት ዋናውን ጭልፋ ይዞ ማንጎር ባልተገባው ነበር፡፡ በአመዛኙ የተጠቆሙት ዕጩዎች የባለሙያ ግብዓት በሚያስፈልግበት ጊዜ ብቻ፣ ያውም ከተሳታፊዎች በሚደረጉ ምክክሮችና ርዕሶች ላይ ሐሳብ አቅራቢዎች ተጠቁመው ሙያዊ በሆነ መንገድ ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ሊደረግ እንጂ፣ ያለ ሙያቸው ሁሉንም አንድ ቦታ ማጎር ለሦስት ዓመታት ምንም ሳይፈይድ ሕንፃና የተንጣለለ ግቢ ይዞ የዘለቀውን የኢትዮጵያ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን በድጋሚ መጠፍጠፍ ነው፡፡

ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደታየው አገራዊ ምክክር ከምንም በላይ የሕዝብን ቅቡልነትና ተሳትፎ በእጅጉ ይጠይቃል፡፡ እናም ገና ከመነሻው በዕጩዎች የምርጫ ሒደት የዳከረው ጊዜ ‹‹የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግርግዳው ሰንበሌጥ›› እንዳይሆን፡፡ የተከበርከው ምክር ቤት ዛሬ ነገ ሳትል ይህንን ሒደት ከአሁኑ አርቀው እንደሄዱ አሳስባቸው፡፡ መቼም እንደ ወያኔው ዓይነት ምክር ቤት ሆነህ የታሪክ ተወቃሽ ለመሆን የምትዳዳ አይመስለኝም፡፡

ለመደምደሚያ በሀማ ቱማ (ፍቀዱልኝና) በሚለው ሐረግ ልዝጋው፡፡

ገዥዎችን ልተች መንግሥትን ልቃወም፣

አትናደዱብኝ ጉም የያዝኩ ቢመስለኝ፣

ጭራሽ አትከፉ ቃል ኪዳን ቢከብደኝ፣

ቂም አትያዙብን ቂምም ቢዘውረኝ፣

ተው አትታዘቡኝ እልክ ቢሾፍረኝ፣

ፍቀዱልኝና ህልሜን ልኖር ልመኝ፣

ቀን ያላለፈበት ሐበሻ እኮ ነኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...