በላቀው በላይ
የይዘት ዳሰሳ
የሩቁን ሁሉ አልፈነው ከቅርቡ እንኳን ስንጀምር ‹‹United States Institute of Peace (Making Peace Possible)›› በተባለው ድረ ገጽ ላይ ብሔራዊ ምክክር የኢትዮጵያን የፖለቲካ ቀውስ (ችግር) ሊፈታ ይችላልን? ‹‹Could a National Dialogue Solve Ethiopia’s Political Crisis?›› የሚል ጽሑፍ በየካቲት ወር 2011 ዓ.ም. የወጣ ስለመሆኑ ከድረ ገጹ ለመመልከት ይቻላል፡፡ ሐሳቡ የተወሰደው እመቤት ጌታቸው፣ መሐሪ ታደሰና ዮሐንስ ገዳሙ ከተባሉ ግለሰቦች እንደሆነ በገጹ ላይ ተመልክቷል፡፡ እመቤት ጌታቸው በአዲስ አበባ ‹‹Life & Peace›› የተባለ ተቋም የፕሮግራም ማኔጀር እንደሆኑ፣ መሐሪ ታደለ በአውሮፓ ዩኒቨርሲቲ ተቋም ፍሎረንስ ጣሊያን ፕሮፌሰር እንደሆኑ፣ ዮሐንስ ገዳሙ ደግሞ በ‹‹Georgia Gwinnett College›› የፖለቲካ ሳይንስ መምህር እንደሆኑ የተመለከተ በመሆኑ፣ ጉዳዩ ነገሩን በተገነዘቡ ሰዎች አማካይነት የተነሳ ነው ለማለት ያስችላል፡፡
ሦስቱም ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ በገጠመው ችግር ለመነጋገር ጊዜው አሁን ስለመሆኑ፣ በወቅቱ ከነበረው በርካታ ችግር አኳያ ለብሔራዊ መግባባት ሒደት ቦታ ስለመኖሩና ስኬታማ ብሔራዊ ምክክር እንዴት መካሄድ እንዳለበት አስተያየታቸውን አስፍረዋል፡፡ ሆኖም ግን ብሔራዊ ምክክር ለምን እንዳስፈለገ እንዲሁም ብሔራዊ ምክክር መቼና በእነማን መካከል እንደሚካሄድ የጠቀሱት ነገር የለም፡፡
በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም. ‹‹ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር መጣር›› (Working Towards an Ethiopian National Dialogue) የሚል ይዘት ያለው ጉባዔ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ እንደተካሄደና ጉባዔውንም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴና የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ እንደከፈቱት ተመልክቷል፡፡ ጉባዔው ቤርግሆፍ ፋውንዴሽን በተባለ ተቋም ድጋፍ እንደተደረገ የተገለጸ ሲሆን፣ ፋውንዴሽኑ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ብጥብጦችን (Political and Social Violence) በመከላከል ረገድ የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
ሁሉንም አካታች የሆነ ብሔራዊ ምክክር ለማመቻቸት በሚል የስምንት ድርጅቶች ስብስበ የሆነ ማይንድ ኢትዮጵያ (MIND Ethiopia) በተባለ ተቋም በነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም. እንደተፀነሰ ተመልክቷል፡፡ ስምንቱ አባል ድርጅቶችም ዴስቲኒ ኢትዮጵያ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የሐሳብ መዓድ፣ ፍትሕ ለሁሉም፣ ኢኒሼቲቭ ፎር ቼንጅ፣ የኢትዮጵያ የዕርቅ ኮሚሽን፣ ኢትዮጵያዊያን ለአካታች ምክክርና የሰላም ሚኒስቴር እንደሆኑ ተመልክቷል፡፡ ማይንድ ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የብሔራዊ ምክክር ጽንሰ ሐሳብ ማስታወሻ፣ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ፣ ተቋማዊ አደረጃጀት፣ የሥነ ምግባርና የተግባቦት ሥልት ያዘጋጀ/የነደፈ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡ የብሔራዊ ምክክሩ ዓላማም የፖለቲካና የኅብረተሰብ ክፍሎችን በአንድ ላይ በማቀራረብ ታሪካዊና አሁናዊ ችግሮችን መለየት፣ መፍትሔ መፈለግና የመተግበሪያ ሥልቶችን መንደፍ እንደሆነ ተወስቷል፡፡ የማይንድ ኢትዮጵያ ዘላቂ ዓላማ አገሪቱንና ሕዝቧን ወደ አካታች፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ጎዳና መውሰድ እንደሆነ የተመለከተ ሲሆን፣ ማይንድ ኢትዮጵያ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ቦርድና ጽሕፈት ቤት ያለው መሆኑም እንዲሁ፡፡ ማይንድ ኢትዮጵያ በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም. አንድ ሺሕ የሚሆኑ ሰዎችን በማሳተፍ ብሔራዊ ምክክር ለመጀመር ዝግጅቱን የጨረሰ መሆኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ አሳውቆ የነበረ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
ከላይ ለመመልከት እንደሚቻለው በመጀመርያ በግለሰቦች፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና፣ መንግሥት አንድ አባል በሆነበት ሌሎች ስብስቦች ተጀምሮና ተንቀሳቅሶ የነበረው የብሔራዊ ምክክር ሐሳብና እንቅስቃሴ በምን ምክንያትና አግባብ ወደ መንግሥት እንደመጣ ጸሐፊው የመረጃ ክፍተት ያገጠመው ቢሆንም፣ አሁን ጉዳዩን መንግሥት በባለቤትነት ይዞት የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ያቋቋመ አዋጅ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ የ11 ኮሚሽነሮች መረጣም በሒደት ላይ እንደሚገኝ አሳውቋል፡፡ በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መግቢያ ላይ፣
- በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካና የሐሳብ መሪዎች፣ እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልዩነትና አለመግባባት የሚታይ በመሆኑ፣ ይህንን ልዩነትና አለመግባባት ለማርገብና ለመፍታት ሰፋፊ አገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ አገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፣ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች አገራዊ ምክክሮችን ማካሄድ የተሻለ አገራዊ መግባባትን ለመገንባትና በሒደትም የመተማመንና በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ለማጎልበት የሚያስችል ሥርዓት በሕግ መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
- አገራዊ ምክክሮች ተቀባይነትና ተዓማኒነት ያላቸው እንዲሆኑ ከሚያስችላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ምክክሮቹን የሚያመቻቸውና የሚመራው አካል ብቃትና ገለልተኝነት በመሆኑ፣ ምክክሮቹን በብቃትና በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር የሚችል ሰፊ ቅቡልነት ያለው ተቋም ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ የወጣ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡
የየብሔራዊ ኮሚሽኑ ዓላማ በሚለው ሥር ደግሞ፣
- በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በመለየትና ውይይቶቹ የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት ምክክር እንዲደረግባቸው ማመቻቸት፣
- የሚካሄዱት አገራዊ ምክክሮች አካታች፣ ብቃት ባለውና ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፣ ያለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ የሚያተኩሩ፣ ግልጽ በሆነ የአሠራር ሥርዓት የሚመሩና የምክክሮቹን ውጤቶችን ለማስፈጸም የሚያስችል ዕቅድ ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ውጤታማ የሆኑ አገራዊ የምክክር ሒደት ተግባራዊ ማድረግ፣
- የሚካሄዱት አገራዊ ምክክሮች በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመን የሰፈነበትና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር በሚያስችል አግባብ ውይይቶቹ እንዲካሄዱ ሥርዓት መዘርጋት፣ ከምክክሮቹ የተገኙ የመፍትሔ ምክረ ሐሳቦች በሥራ ላይ እንዲውሉ ድጋፍ በማድረግ በዜጎች መካከል እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲገነባ ማስቻል፣
- ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበርና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላደል መፍጠር፣
- ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ ተፈተው አስተማማኝ ሰላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካና የማኅበራዊ መደላደል ማመቻቸት፣
- ለአገራዊ መግባባትና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው አገረ መንግሥት ለመገንባት ፅኑ መሠረት መጣል ናቸው ተብሎ ተዘርዝሯል፡፡
አዋጁን ለማውጣት ‹‹በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካና የሐሳብ መሪዎች፣ እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልዩነትና አለመግባባት ይታያል›› የተባለው በምክንያትነት ቢጠቀስም፣ በአዋጁ የማብራሪያ ሰነድ (ከአዋጁ ውጪ የሆነ ሌላ ሰነድ) ላይ በኢትዮጵያ እጅግ መሠረታዊ የፖለቲካና የኅብረተሰብ አለመግባባቶች የተባሉት ምን እንደሆኑ አልተመለከተም፡፡ ችግሮቹም በብሔራዊ ምክክር ብቻ የሚፈቱ ስለመሆኑ የተብራራ ነገር የለም፡፡ በተለይ በተለይ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ተራ ቁጥር አንድ ላይ ‹‹በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በመለየትና ውይይቶቹ የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት ምክክር እንዲደረግባቸው ማመቻቸት›› የሚለው ሰፍሮ መታየቱ፣ የመንግሥትን ተጠያቂነት ወደ ኅብረተሰቡ ለማሸጋገር የታሰበ ሴራ ይኖረው ይሆን የሚል ሥጋት የሚጭር ነው፡፡
የአዋጁን መውጣት ተከትሎ ልዩ ልዩ አካላት አስተያየት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በጀርመን ሬዲዮ ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ብሔራዊ ምክክር ለምን? እንዴትና መቼ? በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ልዑል አስፋወሰን (ዶ/ር) የተባሉ ሰው ብሔራዊ ምክክር አሁን ሳይሆን ከ30 ዓመት በፊት መደረግ የነበረበት መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ግን ነገሩ ‹‹የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች›› የሚለው እንዳይደርስ ሥጋት ያላቸው መሆኑን፣ በመጀመርያ ጦርነቱን ማሸነፍ አስፈላጊ መሆኑን፣ ኢትዮጵያና ሕወሓት አብረው መሄድ የማይችሉ በመሆኑ ኢትዮጵያን ከሚያጠፋ ጠላት ጋር ምክክር ማድረግ የማይቻል መሆኑን፣ ቅድሚያ ሕወሓትን ሕገወጥ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን፣ የአገሪቱ ዋናው ችግር ሕወሓት በ1987 ዓ.ም. የጫነብን ሕገ መንግሥት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ባይሳ የተባሉ ሰው ደግሞ የብሔራዊ ምክክር ሐሳብ በመንግሥት አለመጀመሩን ገልጸው፣ በአገራችን ምክክር የሚያስፈልገው ቁስል መኖሩን፣ አሁን የታሰበው ምክክር የተጀመረው ከጦርነቱ በፊት መሆኑን፣ ችግሩ ከመንግሥት ጋር ብቻ አለመሆኑን፣ ኦሮሞው፣ ሶማሌው፣ ትግሬው፣ ወዘተ የሚያነሳው ችግር መኖሩን፣ አንድ ባህሪ፣ አንድ አገር፣ አንድ ቋንቋ ሊኖረን ያላስቻለን ችግር ያለ መሆኑን፣ ምክክሩንም አሁን ለማድረግ የሚቻል መሆኑን፣ ሕገ መንግሥቱ የችግር ውጤት እንጂ የችግራችን መነሻም መድረሻም አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ይልማ የተባሉ ሰው ደግሞ በአገራችን የ50 ዓመት በሽታ መኖሩን፣ የሐሰት ዜና የመንዛት ነገር መኖሩን፣ ዋናው ችግራችን ሕገ መንግሥቱ መሆኑን፣ ጦርነቱ በአሸናፊና በተሸናፊ መጠናቀቅ ያለበት መሆኑን፣ አገሪቱን ችግር ውስጥ የከተታት ለትምህርት ወደ አውሮፓ ሄዶ የተመለሰው ሰው ይዞት የመጣው ‹‹ራዕይ›› የተባለ ቅዠት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጥር 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ‹‹ጉድ ገቨርናንስ አፍሪካ – ምሥራቅ አፍሪካ›› የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባዘጋጀው ወይይት ላይ የተገኙት የታሪክ ተመራማሪው ባህሩ ዘውዴ (ኤመረተስ ፕሮፌሰር)፣ ብሔራዊ ምክክሩ ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነፃ መሆን እንዳለበትና በሒደቱ ውስጥም መንግሥት እጁን የሚያስገባ ከሆነ ምክክሩ የመበላሸት አዝማሚያ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ ብሔራዊ ምክክሩ የብዙኃን ተሳትፎ ሊኖረው እንደሚገባ፣ የልሂቃን ተሳትፎም አስፈላጊ እንደሆነ፣ ውሳኔ የመስጠቱ ሒደት በብዙኃኑ እጅ መሆን እንዳለበት፣ በብሔራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ በሙሉ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት የሚያምኑ መሆን እንዳለባቸው፣ ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳ መቅረት እንዳለበት፣ ተሳታፊዎች በአመፅ የሚደረግ ትግልን የተው መሆን እንዳለባቸው፣ የምክክሩ ተሳታፊዎች በሰላማዊ ትግል፣ በክርክርና በሐሳብ የበላይነት ማሸነፍን የሚቀበሉ ‹‹ነፃነት ግንባር›› የሚባል ነገር መቅረት አለበት ብለዋል (ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ ጥር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ዕትም)፡፡
በውይይቱ ላይ ጽሑፍ ያቀረቡት ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) በ1960ዎቹ ከነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ የመጡ ውርሶች ለአሁኑ ጦርነት መንስዔ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ የተማሪዎች ንቅናቄ ለውጥ ወይም ፍላጎት ጽንፍ በያዘና አመፅ በተሞላበት መንገድ ማምጣት በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ባህል እንዲሆን ማድረጉን አብራርተው ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የወጡና ኋላ ኢሕአዴግን መሥርተው ሥልጣን የያዙት አካላትም፣ በሥልጣን ዘመናቸው አመፅን እንደ ፖለቲካዊ መሣሪያ ሲጠቀሙ መቆየታቸውን፣ የበሰበሰው የኢሕአዴግ ሥርዓት ከመውደቅ ይልቅ ራሱ ገዥው ፓርቲ እየመራ ለውጥ ወደ የሚመጣበት አካሄድ መለወጡን፣ ይህም አዲሱ ለውጥ የቀድሞውን ሥርዓት ችግሮች እንዲሸከምና በዚህም ምክንያት ጦርነት ውስጥ መገባቱን፣ አገሪቱ ውስጥ ትርክት ላይ የተመሠረተ አመፅ እንዳለና ከትርክቶች ውስጥ ቀዳሚው የጭቆና ትርክት መሆኑን፣ በዚህ የተነሳም በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም አካላት የ‹‹ተጨቁኛለሁ›› ሥነ ልቦና መያዛቸውን፣ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ዋነኛው ጨቋኝ አገረ መንግሥቱ ሆኖ ሳለ አንዱ ሌላውን በጨቋኝነት እንዲፈርጅ ማድረጉን፣ ሥልጣን ላይ ባሉ አካላት ተነስቶ ለኅብረተሰቡ የተረፈውን ግጭት ወደ መነሻው መመለስ እንደሚገባ፣ ከዚህ ሁሉ በፊት ግን የጥይትን ድምፅ ፀጥ ማሰኘትና ጽንፈኛ የሆነ የፖለቲካ አመለካከትን ትጥቅ ማስፈታት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል (ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ ጥር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ዕትም)፡፡
ሃያ የሲቪል ማኅበራት ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ ከ14 የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ዕጩዎች ውስጥ የሴቶች ቁጥር ከወንዶች የተስተካከለ እንዲሆን፣ ሒደቱም ግልጽና ተዓማኒነት የተሞላበት እንዲሆን፣ የሴቶች ድርጅቶችና አደረጃጀቶችም ዕጩዎች በሚመረጡበት ሒደት ውስጥ እንዲወከሉና የማጣራቱ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ፣ ሁሉን አካታች ፖለቲካዊ ምክክር ለማድረግ የሚያስችል ከባቢ ሁኔታ እንዲፈጠር ሲባል በአገሪቱ ውስጥ የታጠቁ አካላት በሙሉ ግጭቶችን አቁመው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ጥር 14 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) በምክክር ሒደቱ ውስጥ አካታችና እውነተኛ የሆነ ውክልና እንዲኖር፣ በምክክሩ ላይ ባለድርሻዎች የሚያቀርቧቸው አጀንዳዎች ያለ ምንም አድልኦ ሁሉም የሚስማሙባቸውና ተቀባይነት ያላቸው መሆን እንደሚገባቸው፣ ምክክሩን የሚመሩ ሰዎች አመራረጥ ነፃ፣ ግልጽና አካታች እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ሰው በብሔራዊ ምክክሩ ውስጥ የራሱ አጀንዳና ድርሻ ካለው ብሔር የሚመጣ መሆኑን ማወቅ ጠቃሚ እንደሆነ፣ የውሳኔ መስጠት ሒደቶች ግልጽና ሁሉም የሚስማማባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ አሳውቋል፡፡
ብሔራዊ ምክክሩን በተመለከተ ጥር 13 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫ ያወጡት 63 ዓለም አቀፍ የኦሮሞ ሲቪል ማኅበራት የተባሉ መንግሥት ገለልተኛ የሆነ ሰብሳቢ ያለው ኮሚሽን የማቋቋም ሒደትን ለመምራት የሚያስችል ገለልተኝነት የለውም ካሉ በኋላ፣ ብሔራዊ ምክክሩ ሁሉን አካታች፣ አሳታፊና ነፃ በሆኑ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀባይነት ባላቸው ሰብሳቢዎች እንዲመራ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ኅብረት ጥር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ‹‹ሰላም የተጠማና የተራበ ሕዝብ›› በሚል ርዕስ በወጣው መግለጫ የብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋም የጊዜ መግዣና የአጀንዳ ማስቀየሪያ እስካልሆነ ድረስ ኅብረቱ የሚደግፈው መሆኑን ገልጾ፣ የምክክር ሐሳቡ በተለያዩ ስብስቦች ላለፉት አራት ዓመታት ሲቀርብ የተመለከተ መሆኑን፣ የአገሪቱን አንድነት ለማስቀጠል ከተፈለገ ለችግራችን ሁሉ መነሻ የሆነው ሕገ መንግሥት እስካልተለወጠ ድረስ በዚች አገር ላይ ሰላም ይሰፍናል ማለት ጉም መዝገን ነው የሚል እምነት እንዳለው፣ ኢትዮጵያ ዘረኝነትን በሚያስተናግድ መንግሥት የትም እንደማትደርስ፣ ከሥልጣን የተሰናበተው ሕወሓት በመልኩና በይዘቱ ተመሳሳይ ሆኖ መቀጠሉ ሁሉንም ዋጋ እንደሚያስከፍል አሳስቧል፡፡
ከብሔራዊ ምክክር ጋር በተያያዘ ባይሆንም ደረጀ ገረፋ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ኢንሳይደር ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ (ፊንፊኔ ኬኛ) እና አፋን ኦሮሞን የፌዴራል ቋንቋ ማድረግ የኦሮሞ ጥያቄዎች ናቸው በማለት በምክክር ሒደት ሊያነሱ ያሰቡትን/የተዘጋጁበትን አጀንዳ ከወዲሁ ዘርግተዋል፡፡ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፕሬዚዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ከአሻም ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ በአገራችን በሚደረገው ብሔራዊ ዕርቅ ሕወሓት የጫነብን፣ ለእርስ በርስ ጦርነትና ዕልቂት ምንጭ የሆነው ሕገ መንግሥት በአዲስና ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስማማ የአገር አንድነትና ሉዓላዊነት በሚያስከብር ሕገ መንግሥት መተካት አለበት ብለው፣ በአዲስ አበባ ተረኝነቱ ብሶበታል፣ በሕግ ባይፀድቅም አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል ሆኗል፣ በጉልበት አዲስ አበባን የኦሮሚያ ማድረግ አይቻልም ብለዋል፡፡
በብሔራዊ ምክክሩ ዙሪያ በሸገር 102.1 ሸገር ካፌ ላይ የቀረቡት ሽመልስ ቦንሳ (ዶ/ር) እና ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) ሕዝቡ ይህንን ብሔራዊ ምክክር እንደ እንቁላል መንከባከብ እንዳለበት፣ ይህ ዕድል ካመለጠ መጪው ጊዜ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ ስማቸውን እዚህ ላይ መጥቀስ ባያስፈልግም በደቡብ አፍሪካ፣ በላይቤሪያ፣ በሩዋንዳና በሌሎች አገሮች የተደረጉ ብሔራዊ ምክክሮችን በቦታው ተገኝቼ ተመልክቻለሁ ያሉ ሰው ደግሞ፣ ብሔራዊ ምክክር የሚደረገው መንግሥት በሌለበት ወይም መንግሥት አገር መምራት ባልቻለበት ሁኔታ እንጂ አሁን መንግሥት ባለበትና መንግሥቱም አገር ማስተዳደር በሚችል ቁመና ላይ ባለበት ሁኔታ ብሔራዊ ምክክር የሚደረግበት አግባብ ግልጽ አይደለም፣ ምክክሩም ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነፃ ሊሆን አይችልም በማለት ሥጋታቸውን አቅርበዋል፡፡
ከላይ ከሰፈረው ዳሰሳ በዋናነት አሁን ያለው ሕገ መንግሥት የችግር ምንጭ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ መንግሥት ደግሞ የችግሩ ባለቤት፣ የችግሩ አስቀጣይና የመፍትሔውም እንቅፋት ነው በሚል በችግርነትና በሥጋትነት ተፈርጇል፡፡ አሁን የገባንበትን ጦርነት በአሸናፊነት ማጠናቀቅ የሚገባ ስለመሆኑ የሐሳብ መግባባት ያለ መሆኑን ለመረዳት የሚቻል ሲሆን፣ በልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል አለመግባባት ስለመኖሩ የተጠቀሰ ማስረጃ ባይኖርም በአዋጁ መግቢያና በኮሚሽኑ ዓላማ ላይ ይኸው ተጠቅሷል፡፡ አካታችነትን በተመለከተ፣ ብሔራዊ ምክክሩ የሚደረግበትን ጊዜ በተመለከተ መግባባት የሌለ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡
‹‹ብሔራዊ ምክክር የኢትዮጵያን የፖለቲካ ቀውስ (ችግር) ሊፈታ ይችላልን? (Could a National Dialogue Solve Ethiopia’s Political Crisis?) የሚለው ጥያቄ አሁንም ድረስ ምላሽ ሳያገኝ የቀጠለ ጥያቄ ነው፡፡ የብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋም የጊዜ መግዣና የአጀንዳ ማስቀየሪያ ሊሆን ይችላል የሚለውም በሥጋትነት የቀጠለ ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት በብሔራዊ ምክክሩ ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም የሚለው ድምፅ ደግሞ እጅግ ከፍ ብሎ በመሰማት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ጸሐፊ ደግሞ ከዚህም የዘለገ/የጠለቀ ጥያቄ አለው፡፡ የችግሩ ተጠቃሚ (መንግሥት) ችግሩ እንዲወገድ ይፈልጋልን? የሚለው የዚህ ጸሐፊ ዋና ጥያቄ ነው፡፡ መንግሥት የችግር ተጠቃሚ መሆኑ አዎንታዊ ምላሽ ካገኘ እውነት ችግራችን መፍትሔ ይኖረዋልን? የሚለው የጸሐፊው ተጨማሪ ጥያቄ ነው፡፡ ዓለም ችግሬ ነው ያለውን ለምሳሌ የፈንጣጣ፣ የወባ ወረርሽኝ፣ ወዘተ. እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ ምስቅልቅሎችን እንዴት እንደፈታው የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ዓለም ችግርን መፍታት ብርቁ አይደለም፡፡ ሆኖም ዓለም የሚታወቀው ይጎዳኛል ያለውን ችግር በመፍታት እንጂ፣ ተጠቃሚ ያለውን ችግር የመፍታት ተሞክሮ የለውም፡፡ ኢትዮጵያውያን ዛሬ የገጠመን ችግር በዓይነቱ የተለየ ነው፡፡ እኛን የገጠመን ችግር ጥቅም የሚያስገኝ ችግር ነው፡፡ ለእኛ የጅምላ ዕልቂት፣ ለመንግሥትና በመዋቅሩ ውስጥ ለተሰገሰገው የጥቅም ሠራዊት ደግሞ ጥቅም የሚስገኝ ችግር ገጥሞታል፡፡ ይህንን የተለየ ችግራችንን ዓለም በሄደበት መንገድ ሄደን የምንፈታው ሆኖ አይታይም፡፡ የችግር ተጠቃሚዎችን ከግምት ያስገባና የተለየ የችግር መፍቻ መንገድ ያስፈልገናል፡፡
ጉዳዩ ‹‹ብሔራዊ ምክክር እንዴት?›› በሚለው ክፍል የሚቀርብ ቢሆንም፣ ከዚህ በታች የተመለከተውን ከወዲሁ መጠቆም አጣዳፊ ሆኖ ይታያል፡፡ ከሁሉም በፊት የብሔራዊ ምክክር ሥራውን በኃላፊነት የሚረከቡ ኮሚሽነሮች፣ ይህ ሕዝብ አሁን የተሸከመው ቁስል ሌላ ተጨማሪ ድራማ ለማስተናገድ የሚያስችለው አቅም የሌለው መሆኑን መረዳት አለባቸው፡፡ በተመሳሳይ የብሔራዊ ምክክሩን ሥራ በኃላፊነት የሚረከቡ ኮሚሽነሮች፣ መንግሥት ከአገሪቱ ችግር ተጠቃሚ ሆኗል ከሚለው ክስ ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ መንግሥት ከአገሪቱ ችግር ተጠቃሚ ሆኗል ከሚለው ክስ ነፃ ወጣም አልወጣም፣ የኮሚሽነሮቹ ቀጣይ ሥራ መንግሥት ችግሩ እንዲወገድ ፍላጎት ያለው መሆኑን ብቻ ሳይሆን ችግሩ እንዲወገድ ግዴታ የሚገባ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ለዚህም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዋስትና እንዲሰጥ ማድረግ አለባቸው፡፡ የብሔራዊ ምክክሩን ሥራ በኃላፊነት የሚረከቡ ሰዎች ሥራውን ከመረከባቸው በፊት የአዋጁ መግቢያና የኮሚሽኑ ዓላማ በሚለው ሥር፣ ‹‹… በልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልዩነትና አለመግባባት የሚታይ በመሆኑ…›› በሚል የሰፈረው ከአዋጁ እንዲወጣ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግሥት የችግሩ ፈጣሪ፣ አስቀጣይና ተጠቃሚ ራሱ ሆኖ በሥልታዊ መንገድ ችግሩ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲተላለፍ እንዲያደርግ ሊፈቀድለት አይገባም፡፡ የብሔራዊ ምክክሩን ሥራ በኃላፊነት የሚረከቡ ኮሚሽነሮች ከመንግሥትና ከቅንጡ ሳሎኖች ራሳቸውን አርቀው፣ በጅምላ መቃብሮቻችን ላይ መዋል፣ ማደር፣ እንዲሁም መሰንበት አለባቸው፡፡ የብሔራዊ ምክክሩን ሥራ በኃላፊነት የሚረከቡ ኮሚሽነሮች ከቪኤይት (ቪ8) መኪና ወርደው በግፉዓን ማደሪያ መዋል፣ ማደርና መሰንበት አለባቸው፡፡ ልክ እንደ ግፉዓን ማንባትና ማልቀስ አለባቸው፡፡ ሥራውን የሚረከቡ ኮሚሽነሮች ከቪ8 መኪናቸው ወርደው በድሆች ቤት ማደር፣ የሚበሉትን መብላት፣ የሚጠጡትን መጠጣት አለባቸው (ብሔራዊ ምክክር ለምን? የሚለው በክፍል ሁለት ይቀጥላል)፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው wbdlakew@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡