Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ኢኮኖሚውን  ለመታደግ አዋጭ ፖሊሲዎችን ቀርፆ መተግበር ያስፈልጋል

በኢትዮጵያ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመወጣት በሁሉም ዘርፎች አዋጭ ፖሊሲዎችን መቅረፅና መተግበር እንደሚገባ የተለያዩ ወገኖች ከሚሰጡት አስተያየቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ካሉባት በርካታ ችግሮች ለመውጣት ደግሞ በዋናነት ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት ያለበት ኢኮኖሚው ላይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን ተፈጥሯዊ አቅሟን በመጠቀም በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ደግሞ የተመቻቸ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡

ዛሬ ላይ ኢኮኖሚውን ወደኋላ እየጎተቱ ከሚገኙ ጉዳዮች አንዱ ጥርት ያለ ፖሊሲ ካለመቀረፁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እስካሁን አሉ የሚባሉ ፖሊሲችም ቢሆኑ ኢትዮጵያን በሚፈለገው ደረጃ አላራመዱም፡፡ እንዲያውም አለ የሚባለውን ፖሊሲ እንኳን በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችል አሠራርና ሥርዓት አለመቀረፁም እንደ ጉድለት ሲገለጽ የቆየ ነው፡፡

አሁን ላይ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተለያዩ ፖሊሲዎች እየተቀረፁ መሆኑ እየተሰማ ነው፡፡ ይህ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን የተመቻቸ ፖሊሲ መቅረፅ ደግሞ ብቻውን ግብ አይሆንም፡፡ ፖሊሲውን በአግባቡ ሊያስፈጽም የሚችል አመራር ያሻል፡፡ አመራሩም በፖለቲካ ተሿሚነት የሚሰየም ሳይሆን፣ ለቦታው የሚመጥን ዕውቀት ያለው ማድረግ የእስከ ዛሬውን ስህተት ያርማል፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን የኑሮ ውድነት ጨምሮ በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚታዩትን ተግዳሮቶች ለማሸነፍ ከተፈለገ ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ቀውስ ከግምት የሚያስገባ ፖሊሲ ያስፈልገናል ሲባልም፣ ለጊዚያዊ መፍትሔ የሚሆን ብቻ ሳይሆን ዘለቄታውንም ታሳቢ አደርጎ መቀረፅ አለበት፡፡ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ እንዲሻሻል የሚያስችል መሆን ይገባዋል፡፡  

እዚህ ላይ የአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ሲታሰብ የግሉ ዘርፉ ሚና ወሳኝ በመሆኑ፣ ኢኮኖሚውን ለማሳደግም ሆነ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዙ አሉ የሚባሉ ችግሮችን ለመፍታት የግሉ ዘርፉ ሚና ወሳኝ መሆኑ ከግምት መግባት ይኖርበታል፡፡

እስካሁን ባሉ የተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ውስጥ የግሉ ዘርፍ ሚና ወሳኝና አንቀሳቃሽ መሆኑን የሚገልጹ ቢኖሩም፣ በተግባር በበቂ ሁኔታ እየታየ ባለመሆኑ የአገር የጀርባ አጥንት መሆናቸውን በሚያሳይ መልኩ የግል ዘርፉ ሚና በጉልህ መውጣት አለበት፡፡

ስለዚህ አሁን በአገር ደረጃ የሚታሰቡ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ማሻሻያዎች የግሉን ዘርፍ ሚና ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት ሲባል በቃላት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አስተዋጽኦዋቸው ምን ምን እንደሆነ በግልጽ ተለይቶ መቀመጥም ይኖርበታል፡፡ የግል ዘርፉ የሚጠበቅበትንና መንግሥትም ማድረግ የሚገባው ይህ ነው ብሎ የሚያሳይ መሆን አለበት፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ያሉት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዝ፣ የኑሮ ውድነት፣ በቂ ምርት አለማምረት፣ ኢንዱስትሪዎች ከአቅማቸው በታች ማምረትና የመሳሰሉ ችግሮች አገራችንን ያጋጠማት ተደራራቢ ችግሮች የፈጠሩት ብቻ አይደለም፡፡ ግልጽ የሆነ ፖሊሲና እያንዳንዱ ቢዝነስ የሚመራ ፖሊሲ ካለመኖር ጋር የተያያዘም ነው፡፡

ዛሬ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከልክ በላይ የሆነውና በጥቁር ገበያና በመደበኛው የባንክ አገልግሎት የምንዛሪ ልዩነት ሰፊ የሆነበት አንዱ ምክንያት ከውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ግልጽ ፖሊሲ ባለመኖሩ ነው፡፡ በየጊዜው እያሻቀበ የመጣው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበትን መያዝ ያልተቻለውና ሁልጊዜ እሳት የማጥፋት ወይም ጊዜያዊ መፍትሔዎችን በመፈለግ የምንባጀውም አጠቃላይ የገበያ ሥርዓቱ የሚመራበት ግልጽ የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት፣ እንዲሁም ለዚህ የሚሆን ፖሊሲ ካለመኖር ጋር ይያያዛል፡፡

የግብይት ሥርዓቱ ወጥ የሆነ አሠራር የለውም፡፡ በሕግ የተቀመጡ ድንጋጌዎች በአግባቡ ተፈጻሚ አይሆኑም፡፡ ኮንትሮባንድ የአገሪቱን ገበያ እንዳሻው ሲበርዝ የሚወሰደው ዕርምጃ ዘላቂ መፍትሔ ያለማምጣቱ ሁሉ በፖሊሲ የታገዘ አሠራር ያለመኖሩን ያመለክተናል፡፡

ስለዚህ አሁን ላይ እየተሰናዱ ናቸው የተባሉ የኢኮኖሚና ንግድ ነክ አገራዊ ፖሊሲዎች ዝግጅት፣ ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ቅልጥፍና የሚበጁ ቢሮክራሲውን የሚያሳጥሩና ከሙስና የፀዱ አሠራሮችን መዘርጋት የሚያስችሉና ተጠያቂነትንም የሚንያፀባርቁ መሆን አለባቸው፡፡ ያለውን የተዝረከረከ የግብይት ሥርዓት ፈር የሚያስይዝ መሆን አለበት፡፡

የግል ዘርፉም ከልማዳዊ ንግድና ግብይት ወጥቶ ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲራመድ የሚያስችል መሆን አለበት፡፡ እዚህ ላይ ግን የግል ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ ያለው ሚና የማይተካ መሆኑ ባይካድም በሕግና በሥርዓት መጓዝ ያለበት መሆኑም መረሳት የለበትም፡፡      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት