Saturday, June 10, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ፖለቲከኞች እንደ አስፈላጊነቱ መቀደስና ማርከስ የሚችሉበት የኢትዮጵያ ታሪክ አተያይ

ክፍል ፪

በያሬድ ነጋሽ

በዘመኑ በሃይማኖት አፈና መልኩ ከሚነሱት ነጥቦች መካከል የፌስቡክ ፀረ አሕባሽ ቡድን ‹‹የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የትግል ውሎ በኢንተርኔት›› በሚል የበርካታ ጸሐፍትን ሥራ በመጽሐፍ መልክ በ2004 ዓ.ም. ባቀረበበት ጥንቅር (ኡባህ አብዱ ሰላም ሰዒድ እንደ ጻፈው)፣ ‹‹አፄ ዮሐንስ አራተኛ (እ.ኤ.አ. ከ1870 – 1888) ‹በአንድ አገር አንድ ሃይማኖት› በሚለው ፖሊሲያቸው ይታወቃሉ። ይህንን ፖሊሲ በሥራ ላይ ለማዋል ሲሉ ከታናሻቸው ከንጉሥ ምኒልክ ጋር እንኳን ተጣልተዋል (ምኒልክ በሃይማኖት ፖሊሲያቸው ጥሩ ባይባሉም ከአፄ ዮሐንስ ይሻላሉ)። አፄ ዮሐንስ ፖሊሲያቸውን ለመተግበር ሲነሱ በቅድሚያ የመረጡት የወሎን ክፍለ አገርን ነው። በዚሁ መሠረት ለብዙ ምዕት ዓመታት እምነታቸውን አስጠብቀው የቆዩ የወሎ ሙስሊሞች በአንድ ወር ውስጥ ክርስትና ካልተነሱ በሰይፍ እንደሚቀጡ አዋጅ ተነገረ። ወላዋዩና ሹመት ፈላጊው (እንደ ራስ ሚካኤል ዓይነቱ) የአፄውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ተሽቀዳደሙ። አብዛኛው ሕዝብ ግን እስልምናን በምንም ዋጋ እንደማይለውጡ ለአፄው ቁርጡን ነገሯቸው። በነገሩ የተናደዱት አፄ ዮሐንስ የሽብርና የጦርነት ጅራፋቸውን በወሎ ሕዝብ ላይ መዘዙ። ሙስሊሙ ሕዝብ በሼህ ጠለሃ ጃፋር፣ በአባ ዋጠውና በሌሎችም ሙጃሂዶች ዙሪያ በመሠለፍ እብሪተኛውን አፄ ተጋፈጡ። የአፄው ጥቃት እየባሰ ሲሄድ ሕዝቡም ለሃይማኖቱ ሲል ወደ ሐረር፣ ባሌ፣ ጅማና ጉራጌ ተሰደደ። ነገሩ አንጀቱን ያሳረረው ደግሞ ወደ ሱዳን እየተሰደደ ከኢማም አህመድ አልማህዲ ጦር ጋር ተቀላቀለ። አፄው በጦርነት ፖሊሲያቸው ገፉበት። ሆኖም ጦርነቱ ሃይማኖትን ሊያስለውጥ አልቻለም። እንዲያውም የእሳቸው ሕይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆነ፤›› ይላል። (ሁሴን አህመድ ‹‹Islam in Nineteenth century; Wallo, Ethiopia›› በሚል የጻፈውን መጽሐፍ ለማግኘት ዕድሉ ላላችሁ፣ የጉዳቱን መጠን በዝርዝር በመያዙ በርካቶች እንዲነበብ ይመክራሉ)፡፡

በሃይማኖት አፈና ረገድ በዘመኑ ላይ በተለይም በአፄ ዮሐንስ አራተኛ ላይ ለሚነሱ ጉዳዮች፣ አህመድ ኢብራሂም አል – ጋዚ (ግራኝ አህመድ) ከ1529 እስከ 1543 ከነበሩት የመካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍል ነገሥታት ጋር ባደረጋቸው ጦርነቶች ወቅት በክርስቲያኑና በቤተ እምነት ላይ አድርሷል ተብሎ የሚታሰቡትን ጉዳዮች በመዘርዘር ‹‹አንድ እኩል›› በሚመስል መልኩ ከማስቀመጥ በዘለለ ማስተባበያ ሲሰጥበት አልተመለከትኩም። እንዲያውም በታሪክ ጸሐፍት ዘንድ ነገሩን የማጠናከር አዝማሚያ ይታያል። ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት›› በሚለው መጽሐፋቸው የአፄ ዮሐንስ መሠረታዊ ሐሳብ፣ በክርስቲያኑ ሕዝባቸው መካከል ‹የፀጋ ልጅ፣ የቅባት ተከታይ› የሚለው ሁሉ ተደምስሶ ሁሉም ክርስቲያን በተዋህዶ እንዲያምን ነበር። በዚሁ ጎን በኢትዮጵያ ያለው እስላም ሁሉ በክርስትና እንዲጠመቅ በየአውራጃው ትዕዛዝ ስላስተላለፈ፣ በዚሁ በ1870 ዓ.ም. በያለበት ያለው እስላም ሁሉ በጭቃ ሹም ወደየአቅራቢያው ቤተ ክርስቲያን እየተነዳ በግድ እንዲቆርብ ተደረገ። በዚሁ ጊዜ አንዱ እስላም፣  

‹‹ታናሽ ታላቅ በላን ከርካ አደባባይ

ክርስቲያን ሆይ፣ ያለ ልብ ሥጋ ይጣፍጣል ወይ›

ብሎ ገጥሟል›› በሚል ጽፈውታል።

ከላይ ያየነው ከ1847 – 1906 ዓ.ም ያለውን ወቅት በታሪክ ጸሐፊያን ዘንድ የኢትዮጵያ መልሶ የመሰባሰብ ጊዜ መባሉንና ወቅቱን አስመልክቶ በየፈርጁ የሚነሱትን አስተያየቶች ነበር። ለአንባቢያንም እኔን ጨምሮ ወቅቱን በአራት ዓይን ለማየት የሚያስችል ይመስለኛል። እንደዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከዚህ በፊት ጊዜውን አስመልክቶ በተለያዩ ሰዎች የሚሰነዘረውን በጎ የሆነም፣ ያልሆነም አስተያየት እያገላበጥኩ ከማየትና ከማንበብ ውጪ ወቅቱን አስመልክቶ ይኼ ነው የምለው ሐሳብ ሰንዝሬ አላውቅም። ነገር ግን የአፄ ምኒልክ የዓድዋ ጀግንነታቸው፣ የአፄ ቴዎድሮስ እስከ ሞት ያደረሳቸውን አሻፈረኝ ባይነትና በብሔርና በክልል ሳይገደብ አንዱ ለአንዱ ከመኖር እስከ መሞት መስዋዕትነት ይከፈልበት የነበረውን ቀደምት ኢትዮጵያዊ አኗኗራችንን በሚያስታውሰኝ መልኩ አፄ ዮሐንስ ከትውልድ ሥፍራቸው ተነስተው ጎንደር መተማ ላይ የሕይወት ዋጋ የከፈሉበትን ሒደት በማገናዘብ ለነገሥታቱ ልዩ የሆነ ልባዊ ክብር ያለኝና ከኢትዮጵያ ነገሥታት ደረጃ አውርጄ የአካባቢ ወኪል አድርጌ ያየሁበትም አጋጣሚ የለም።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በቴሌቪዥን ከሚያስተላለፋቸው ዝግጅቶች መካከል ‹‹ወቅታዊና ነጋሪት›› የሚሉ ዝግጅቶች ባሳለፍነው ወራት ውስጥ ሕወሓት ደብረ ብርሃን ደርሻለሁ ባለበት፣ በፌዴራል መንግሥቱ ላይ በሕወሓትም ይሁን በውጭ ኃይላትና ሚዲያዎች በኩል የኘሮፓ ጋንዳ ዘመቻ ተጠናክሮ በተከፈተበት፣ በርካቶቻችን እየተፈጠረ ስላለው ነገር ግራ መጋባት ውስጥ በነበርንበት ወቅት ‹‹ከፌዴራል መንግሥቱ ጎን በመሠለፍ አፀፋዊ መልስ በመስጠት፣ የአገሪቱ ወጣቶችን (በተለይም የአማራ አካባቢ) ቀስቅሶ ወደ ትግል በማስገባቱና ሕወሓት ከያዛቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች ተገፍቶ በማስወጣት ሒደት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የተወጡ ዝግጅቶች ነበሩ፤›› ብዬ አምናለሁ። በተለይም በየፕሮግራሙ ተጋብዘው የድርሻቸውን በመወጣት ተሳታፊ ከነበሩት ምሁራን ውስጥ የጋዜጠኝነትና የተግባቦት መምህሩ አሰግደው፣ ወቅቱ በሚፈልገው ልክ በኃይል፣ በሐሳብ ብስለትና በቋንቋ አጠቃቀም የላቀ ከመሆኑ አኳያ ‹‹የፖለቲካ አመራሮቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በወቅቱ ሊኖራቸው የሚገባ ቁመና ይኼንን መምሰል ነበረበት፤›› ለማለትም ያስደፍረኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከወራት በፊት ‹‹ወቅታዊ›› በተሰኘው ዝግጅት ላይ ‹‹የትሕነግ ባንዳነት›› በሚል የመወያያ ነጥብ ሥር ታሪካዊ ምንጩን ለማስቀመጥ በተሞከረበት ወቅት በአፄ ዮሐንስ አራተኛ ላይ ሁለት ክሶች ቀረቡ። አንደኛው ‹‹አፄ ዮሐንስ አራተኛ፣ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ለማጥፋታቸውና ሥፍራቸው በእንግሊዞች ለመያዙ ከህንድ ለመጣው የእንግሊዝ ሠራዊት ስንቅ በማቅረብ፣ አቅጣጫ በመጠቆምና መሰል ድጋፍ በማድረጋቸው ‹‹ባንዳ›› እና ‹‹ሁለተኛው ወሎ ድረስ ወርደው በተለይም ‹ክርስትናን ተቀበሉ› በሚል በርካታ ሙስሊሞችን ጨፍጭፈዋል›› የሚሉ ክሶች ነበሩ። የክሱ እውነት፣ ውሸትነት ላይ ሳይሆን ክሱ የተነሳው ኢትዮጵያዊነት በሰፊው ተቀንቅኗል ብዬ ከማምንበት አካባቢ በመሆኑ፣ ለዝግጅቱ ሰጥቼው ከነበረ ሥፍራ አኳያና በአካባቢው ከዚህ ቀደም ነገሥታቱን ከእነ ጥፋታቸውም ቢሆን ከሚገባቸው የኢትዮጵያ መሪነት ሥፍራ አውርደው የማየቱ አዝማሚያ ልምዱ ባለመኖሩ ያልጠበቅኩትና ለጥፋቱ ጠበቃ ለመሆን ባልደፍርም፣ በርካታ ጥያቄዎችን እንዳነሳ ያስገደደኝ ሲሆን፣ በወቅቱም ወዲያው ጥያቄዬን ለማንሳት ሳልችል የቀረሁበትም ምክንያት ጥያቄዬን በመረጃ አስደግፌ ለማንሳት በማሰቤ ነበር።

በቀደመው ወቅት በአማራ ሕዝብም ይሁን በልሂቃኖቹ ዘንድ አፄ ዮሐንስን ከእነ ጥፋታቸው፣ ከእሳቸው በፊትም ይሁን በኋላ ከነገሡት የኢትዮጵያ ነገሥታት ልክ በሚገባቸው ሥፍራ የማስቀመጡ ልማድ የነበረ በመሆኑ፣ ክሱ እንዴት ሊቀርብ ቻለ? የሚለው የመጀመርያ ጥያቄዬ ነበር። በገብረ ጻድቅ ደገፋ፣ ‹‹የአማራ ሕዝብ ህልውና፣ አስተዋጽኦና ከሌሎች ጎሳዎች ጋር ያለው ግንኙነት›› በሚለው መጽሐፍ ‹‹አፄ ቴዎድሮስ እጃቸውን ለጠላት ከመስጠት የሽጉጣቸውን ጥይት በገዛ እጃቸው ጠጥተው ሲሞቱ፣ አፄ ዮሐንስ ደግሞ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር ከደርቡሽ ጋር ሲዋጉ ለኢትዮጵያ ክብር ሕይወታቸውን ሰጥተዋል፤›› ይል ነበር። ለፖለቲካ ትርፍ እንደ አስፈላጊነቱ የሚቀደስና የሚረክስ፣ ‹በአንድ ራስ ሁለት ምላስ› የሚያስብል የታሪክ አተያይ ተገቢነት ይኖረዋል?

በሁለተኛነት እውነትም ይሁን ውሸት ነገሥታቱ በተለያየ ወገን ለሚቀርብባቸው ክስ ሽንጥ ገትሮ የማስተባበል ባህሉም በአካባቢው ስለነበር አፄ ዮሐንስን እንዴት አጋልጠው ሊሰጧቸው ቻሉ? ብዬ ጠይቄአለሁ። በዚሁ በገብረ ጻድቅ ደገፋ፣ ‹‹የአማራ ሕዝብ ህልውና፣ አስተዋጽኦና ከሌሎች ጎሳዎች ጋር ያለው ግንኙነት›› በሚለው መጽሐፍ ላይ አፄ ምኒልክ በዓድዋ ጦርነት ወቅት ኤርትራ ሳይደርሱ መመለሳቸውን ተከትሎ ኤርትራን ለጣሊያን አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል ለሚቀርብባቸው ክስ መልስ ሲሰጥ፣ ‹‹አፄ ምኒልክ ኤርትራን ለጣሊያን አሳልፈው እንደሰጡ የሚሰነዘረው ትችት በታሪክ ላይ ያልተመሠረተ ልብ ወለድ ወሬ ነው፤›› ይላል። ታዲያ የተከራካሪነቱ ምንጭ ከወገንተኛዊነት የመነጨ ነበር? ‹‹የኢትዮጵያን ታሪክ በአማራ አካባቢ ሰዎች ክንድ እንደ አስፈላጊነቱ ተጋኖ ወይም ኮስሶ ወይም ተገልሎ የሚቀርብ ተረት ነው፤›› በሚል አንዳንዶች የሚያነሱት ነጥብ ‹‹ልክ ነው›› ባንል እንኳን እንድንጠራጠር አያደርገንም?

ሌላው አፄ ዮሐንስን ‹‹ባንዳ›› ያስባላቸው ጉዳይ ከዚህ ቀደም አወዛጋቢ ሐሳቦችን በመሰንዘር በሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ይነሳ የነበረና ‹‹አዳፍኔ፣ ፍርኃትና መክሸፍ›› በሚለው መጽሐፋቸው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የእንግሊዝ ስደት ወቅት በአገር ቤት ለጣሊያን ካደሩ ባንዳዎች ጋር ደባልቀው ሲመለከቱት ይስተዋላል። በአሚኮ ‹‹ወቅታዊ›› ዝግጅት ላይ የተነሳው የአፄ ዮሐንስ ባንዳነት (‹‹ባንዳነት የዘራቸው ነው›› እስከ ማለት ተደርሷል) በአፄ ምኒልክ ግዛት ማስፋፋት ወቅት አጠፉት ለሚባለው ጥፋት ‹‹አጠቃላይ ከበቀሉበት ማኅበረሰብ ጭምር አስታኮ ማየቱ ተገቢነት የለውም፣ ከዘመኑ መንፈስ አንፃር እንጂ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መነጽር አንይባቸው›› እያልን የሞገትንበት መንገድ ለአፄ ዮሐንስ እንዴት ሊሠራ አልቻለም? ነገሥታቱ አንድም ወደ ሥልጣን ለመምጣት ሲቀጥልም ሥልጣናቸውን ለማፅናትና ለማስጠበቅ የማይፈነቅሉት ድንጋይ ነበር? ክሱ በዘመናቸው ከነበሩት ብልጣ ብልጦቹ ራስ ሚካኤልና አፄ ምኒልክ ድርጊት የተለየ ነበር? ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት›› በሚለው መጽሐፋቸው በ1881 ዓ.ም. ኤርትራ የከተመው የጣሊያን ጦር ወደ ደቡቡ በመስፋፋቱ እንዳልጠቃ የሚል ሥጋት ያደረባቸው የአፄ ዮሐንስ የክርስትና ልጅና የወሎው ባላባት ራስ ሚካኤል ‹‹ምናልባት ፈረንጅ ጥበበኛ ነው፣ ኃይለኛ ነው፣ አፄ ዮሐንስን አሸንፎ ኢትዮጵያን የወረረ እንደሆነ እንዳልጠቃ በሚል ሥጋት ለአንቶሎኒ የጻፉት ደብዳቤ ‹እኔም ከጣሊያን መንግሥት ጋር ተባባሪ ነኝ› የሚል ነበር›› በሚል አስቀምጠውታል። በተጨማሪም በዚሁ መጽሐፍ ላይ ‹‹እንዲሁ ምኒልክ ከዮሐንስ ጀርባ ከጣሊያኖች ጋር ሲወዳጁ፣ ሲዋዋሉ፣ ጣሊያኖቹ በርታ እንደግፍሃለን፣ መሣሪያ እንሰጥሃለን› እያሉ ሲያበረታቷቸው ቆይተዋል። . . .በእውነትም ከባላንጣቸው ከአፄ ዮሐንስ ጋር የሚዋጉበትን መሣሪያ ያቀበሏቸው ጣሊያኖች ነበሩ።›› በሚል ይገልጹታል። እንደ ክሱ ከሆነ ይህ ከባንዳነት ይተናነስ ይሆን? ከዚህ አኳያ አፄ ዮሐንስ ዕድሉን አግኝተው የእንግሊዞችን ድጋፍ ተጠቀሙበት እንጂ ሌሎቹስ ቢሆኑ ለመቀበል ዓይን የሚያሹ ነበሩ?

የወሎን ሕዝብ በተለይም ሙስሊሙን ሕዝብ ጨፈጨፉ የሚለውን ክስ ‹‹ሰው በመግደልና ሙስሊሙን በመግደል›› ብለን በሁለት መልኩ ስንመለከተው፣ አፄ ዮሐንስ ሰው ገድለዋል በሚል ለቀረበባቸው ክስ ከቋራው ካሳ ድርጊቶች ጋር አነፃፅሮ ጥያቄ ለማንሳት ያህል፣ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን እንተውና፣ የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ በቅርበት ሆነው ጽፈዋል የሚባሉት አለቃ ዘነበ የንጉሡ በሽፍታ ዘመናቸው አደረጉት ያሉትን አንድ ነጥብ እናንሳ። ‹‹አምባላይ ወደሚባል አገር (ሱዳን ጠረፍ) ኢድሪስ (ዓረብኛ ተናጋሪ) ከሚባል የመተማ እስላም ጋር ተጉዘው የሰውና የከብት ምርኳቸውን ይዘው ሲመለሱ አምስት ቤት አገው አደጋ ጥሎባቸው ሰዎቻቸው መሸሽ ከጀመሩ በኋላ እሳቸው በርትተው በመዋጋት 360 የአገው ተወላጅ ማረኩ። የተማረኩትንም ‹‹ለምን ወጋችሁኝ፤›› ቢሏቸው፣ ‹‹እርሶን ሳይሆን ኢድሪስን ለመውጋት ነበር፤›› ብለው መለሱ። ካሳ፣ ‹‹ኢድሪስስ የእኔ አይደለምን?›› ብለው ለኢድሪስ፣ ‹‹እኔ ምርቱን አፈስሁ (ዋነኞቹን ገደልሁ) አንተ ግርዱን እፈስ›› ብለው ሁለት መቶውን የአገው ተወላጅ መርጠው ሰጥተው ሁሉንም በሰይፍ አስመቷቸው›› ይላሉ። የሟች ቁጥሩ የዮሐንስን አያህልም ካላልን በቀር አይበለውና አገው ከአማራው ጋር ወደ ግጭት ቢገባ፣ ሰዎቹን ለሱዳን ሽፍታ አሳልፈው የሰጡበት መንገድ ለባንዳነት ክስ የተጠመደ ፈንጂ አይመስልም? አገው ምድር ቴዎድሮስን ከእነ አማራው ደባልቆ በጨፍጫፊነት ሊፈርጀው አይችልም? እንዲሁ ምኒልክን ከእስር አስመልጠዋል ያሏቸውን የሸዋ መኳንንት ወደ ገደል ገፍትረው በመጣል የገደሉበትን መንገድ ነገ ሸዋ ጎንደር ላይ ጥርስ እንዲነክስበት አያደርገውም? ወይስ አማራው በአማራው ላይ የሚያደርሰው በደል አይቆጠርም? ወይስ ‹‹አገርን አንድ ለማድረግ ከነበራቸው ጥልቅ መሻት የመነጨ ነው›› እንል ይሆን?

አፄ ዮሐንስ ሙስሊምን ጨፍጭፈዋል ለተባለበት ክስ (ሙስሊሙ መሞቱ ችግር የለውም ከሚል ዕሳቤ የመነጨ እንዳልሆነ ይገነዘበዋል) ከአፄ ዮሐንስ በኋላም ከነገሡት አፄ ምኒልክና በዚሁ ዘመን ከነበሩት ከወለኔ ጉራጌ አባትና ከእነሞር ጉራጌ እናት የሚወለዱት፣ ጉራጌንና አንዳንድ የሐዲያ አካባቢዎችን ገዥ ከነበሩት ሐሰን ኢንጃሞ አንፃር ምን ልዩነት አለው? በሚል ስናነፃፅረው፣ ከአፄ ምኒልክ አኳያ ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ‹‹አጤ ምኒልክ ለሐረሩ ገዥ ኢሚር አብዱላሂ ግባልኝ (ለማዕከላዊ መንግሥት ገብር) ለሚለው ደብዳቤ መልስ ያለመምጣቱን እንዳዩ ድጋሚ ‹ብትገባ ይሻልሃል› የሚል ሁለተኛ ደብዳቤ ላኩለት። አሚር አብዱላሂ ደብዳቤውን ሲያይ ሳቀ። መልስ ሲመልስም፣ ‹በእስልምና ሃይማኖት ገብተህ የሰለምክ እንደሆነ ጌትነትህን እቀበላለሁ› ብሎ እስላሞች የሚያሸርጡትን ሽርጥ፣ በራሳቸው ላይ የሚጠመጥሙት ጥምጣምና መስገጃ ምንጣፍ ላከላቸው። አፄ ምኒልክ ምላሹን ሲያነቡ ‹‹ወደ ሐረር እመጣለሁ። በዚያ ያለውን መስጊድም ወደ ቤተ ክርስቲያንነት እለውጠዋለሁ። ጠብቀኝ የሚል ደብዳቤ ላኩለት፤›› ይላል።

ከሐሰን ኢንጃሞ አንፃር ስናየው፣ ሰዋስው የማኅበራዊ ድረ ገጽ ከዓመት በፊት ስለሐሰን ኢንጃሞ ታሪክ በሠራው ዝግጅት፣ ‹‹1867 ዓ.ም. ዑመር ቤኬሳ ለሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ለመገበር ተስማማ። ‹ለሸዋው ንጉሥ ለመገበር መስማማት ኢስላምን መካድ ነው› ብሎ የሚያስበው ሐሰን ኢንጃሞን አስቆጣ። . . .ከዚህ በኋላ የሐሰን ኢንጃሞ እንቅስቃሴ የነበረው በዑመር ቤኬሳ ዘመን ተበርዟል ያለውን እስልምና ማጽናትና ለሸዋው ንጉሥ በገበሩ ጎረቤት መንግሥታት ላይ ጦርነት መክፈት ነበር። ሐሰንን ለማግባባት የዲፕሎማሲ ሙከራ አድርጎ ያልተሳካለት የሸዋ መንግሥትም የሐሰን ኢንጃሞን ጦር ለማንበርከክ በቀኛዝማች ውቤ አርጃኖ፣ ደጃዝማች ወልዴ አሻጋሪና በባሻ ሀብተ ሥላሴ የተመራ ጦር አዘመተ። ሐሰን ግን ድል በመንሳት ሰባት ቤት ጉራጌንና አክሊልን ተቆጣጥሮ ዑመር ቤኬሳን ማረከ። ሐሰን ከዚያ በመቀጠል በሰባት ቤት ጉራጌ እስልምና እንዲስፋፋ ሲያደርግ፣ ባህላዊ አምልኮዎችንና የአምልኮ ሥፍራዎችን እንዲወድሙ አደረገ። በዚህ ጊዜ እስልምናን ተቀብዬ የአባቶቼን ባህላዊ የአምልኮ (ዋቅ) ሥርዓት አልተውም ብሎ ያመፀው ሳሞራ ጋቼኖ በያበዜ ሕዝብ ፊት እንዲገደል ሲያደርግ፣ ክርስቲያኖች፣ ሙኸሮች፣ በእቸኔና በያሚናን ደም አፋሳሽ ውጊያ አደረጉ። ድሉ ግን የሐሰን ኢንጃሞ ነበር፤›› በሚል አስነብቦ ነበር።

ይህ እንዴት ይታያል? አሁንም ‹‹የሟች ቁጥሩ ከአፄ ዮሐንስ ጋር አይነፃፀርም›› እስካላልን ድረስ በዘመኑ ግዛታቸውን በራሳቸው ሃይማኖታዊ መነጽር ብቻ የማየቱ አዝማሚያ የነገሥታቱ ብቻ ሳይሆን፣ የመሳፍንቱስ አልነበረም? የአፄ ዮሐንስ ብቻ ሳይሆን የተተኪያቸው የምኒልክም አልነበር? የክርስቲያን ንጉሡ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሙስሊም መሳፍንቱም ጭምር አልነበረም? ድርጊቱ ከዘመኑ መንፈስ ጋር ተያይዞ ሊታይ አይችልም?

በመጨረሻም በአሚኮ ወቅታዊ ዝግጅት በአፄ ዮሐንስ ላይ የተነሳው ክስ በወቅቱ በሥፍራው ሕወሓት ባደረሰው ጥፋት ጫና ውስጥ በመሆን ሁሉንም በዚያ ዓይን ለማየት ከመገደድ የመነጨ ይሆናል? የሚል ግምት አለኝ። ከሆነም ሕወሓት ከአፄ ዮሐንስ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጋር ተነፃፃሪ የሚሆንበት አግባብ ስሜት ይሰጣል? በተለይ አፄ ዮሐንስ የተሰዉለት ሐሳብ ኢትዮጵያዊነት፣ የተሰዉበትም ሥፍራ ከትውልድ ሥፍራቸው ተሻግረው አማራ መሬት ላይ ከመሆኑ አንፃር እንዴትስ ይታያል?

የዘመናዊ ኢትዮጵያ ግንባታ ወቅት በሚባለው ዘመን የነገሡት ነገሥታት አጠፉት ለሚባለው ጥፋት ጥያቄ ለማንሳት ያህል እንጂ፣ ጠበቃ ሆኖ መገኘት የዚህ አንቀጽ ጸሐፊ ፍላጎት አይደለም። የሆነው ሆኖ የአፄ ምኒልክ የዓድዋ ጀግንነታቸውን፣ የአፄ ቴዎድሮስ እስከ ሞት ያደረሳቸውን አሻፈረኝ ባይነትና በብሔርና በክልል ሳይገደብ አንዱ ለአንዱ ከመኖር እስከ መሞት መስዋዕትነት ይከፈልበት የነበረውን፣ ቀደምት ኢትዮጵያዊ አኗኗራችንን በሚያስታውሰን መልኩ አፄ ዮሐንስ ከትውልድ ሥፍራቸው ተነስተው ጎንደር ላይ የሕይወት ዋጋ የከፈሉበትን ሒደት ዓላማ ተገናዝቦ ነገሥታቱን ወደ መንደር አውርዶ ማየትም ይሁን፣ ስማቸውን በክፉ በማንሳት የሚገኝ የፖለቲካ ጥቅም ቢቀርብንስ? የሚል ጥያቄ አንስቼ ጽሑፌን አጠቃልላለሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles