Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአርፋጆች

አርፋጆች

ቀን:

በአዲስ አበባ በሚገኙ በተለይ በመንግሥት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያረፈዱ ተማሪዎችን ትምህርት ቤት በር ላይ ማየቱ የተለመደ ነው፡፡ አርፍደው ከትምህርት ቤታቸው ደጃፍ ከሚታዩት ባልተናነሰ ደግሞ የትምህርት መግቢያ ሰዓት ጠዋት 2፡30 ቢሆንም ለሦስት ሰዓት አምስትና አሥር ጉዳይ ድረስ ዩኒፎርም የለበሱ ተማሪዎች በእግራቸው ሲጓዙ ማየት አሊያም ትራንስፖርት የሚገኝበት ሥፍራ ቆመው ሲጠብቁ መመልከትም ተለምዷል፡፡

አብዛኛው ተማሪ በሰዓቱ ደርሶ ትምህርት ክፍሉ የሚገኝ ቢሆንም፣ አርፋጅ ተማሪዎች መኖራቸው በተማሪዎችና መምህራን ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅዕኖ አለ፡፡

ቀድመው ትምህርት የጀመሩ ተማሪዎችን ማወክ፣ የተማሪንና የአስተማሪን የመማር ማስተማር ስሜት ከመረበሽ ባለፈም በተለይ በተደጋጋሚ የሚያረፍዱ ተማሪዎች የትምህርት ቤት የሰዓት መመርያን ባለመተግበራቸው አለመተግበርና ዝቅተኛ የትምህርት ውጤት የሚያስመዘግቡ ይሆናል፡፡

የተለያዩ ጥናቶችም ማርፈድ ዓለም አቀፍ ችግር እንደሆነ ጠቅሰው፣ አብላጫ ምክንያቱን ደግሞ ከተማሪዎች ኃላፊነትን አለመወጣት ጋር ያያይዙታል፡፡ ይህም በትምህርት ቤቱ ሥርዓት መሠረት በተጠቀሰው ሰዓት መገኘትን እንደ ቁም ነገር ካለመቁጠር እንደሚመነጭም ይጠቁማል፡፡ ይህም ተማሪዎችን ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡

በአዲስ አበባ ሆነ በክልል በተለይ ሩቅ መንገድ ተጉዘው ትምህርት ቤት ለሚማሩት የትራንስፖርት ችግር እንደ አንድ ምክንያት ቢነሳም፣ ይህንን ተቋቁመው በሰዓታቸው የሚገኙ ተማሪዎች መኖራቸው የአርፋጆቹን ጥፋተኝነት ያጎላዋል፡፡

አርፍዶ ትምህርት ቤት ሳይገቡ በር ላይ መቆሙ ደግሞ የተማሪውን ብቻ ሳይሆን የትምህርት ቤቱን ቅቡልነትም የሚፈታተን ነው፡፡

በአዲስ አበባ የአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ላይ የሚስተዋለው  ማርፈድ፣ በዚሁ ሰበብ ከትምህርት ቤት መቅረትና ለተለያዩ ሱሶችና ፆታዊ ጥቃቶች መጋለጥ አሳሳቢ ችግር በመሆኑም ይህን ለመከላከል የአዲስ አበባ ትምህር ቢሮ ከትምህርት ቤቶችና ከወላጆች ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡

የተማሪዎች ማርፈድ ሁሌ የሚታይና የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮም ክትትል የሚያደርግበት ጉዳይ እንደሆነ በቢሮው የአጠቃላይ ትምህርት ሱፐርቪዥን ቡድን መሪ አቶ ፀጋዬ አሰፋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች ትምህርት ላይ እስካሉ ድረስ ማርፈድ መብት ባይሆንም፣ ተማሪዎች በተለያየ ምክንያት ስለሚያረፍዱ ማርፈድ ስህተት እንደሆነ በተደጋጋሚ ያስገነዝባል ብለዋል፡፡

ቢሮው ከወላጆች፣ ከተማሪዎችና ከትምህር ቤት አመራሮች ጋር በመሆን የተማሪዎችን ማርፈድ እንዴት መቀነስ ይቻላል? በሚል በየጊዜው ውይይት የሚያደርግ ሲሆን፣ አልፎ አልፎ በትንራስፖርት ችግር የሚያረፍዱ በመኖራቸው ተማሪዎች ደጅ እንዲቆሙ ሳይሆን ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ገብተው ቁጥጥር እየተደረገ ምክር እንዲሰጣቸው በቢሮው ደረጃ አቅጣጫ መቀመጡን ይናገራሉ፡፡

ሆኖም የአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በራሳቸው ደጅ መቆም ይፈልጋሉ፣ ደጅ መቆምንም ባህሪ ያደርጋሉ፣ በተለይ ጠዋት የሕዝብ መዝሙር እስኪያልቅ ደጅ ሆነው መምህራን በተግሳጽ እንዲያስገቧቸው የሚፈልጉም አሉ ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ትምህርት ቢሮው ከትምህርት ቤት አመራሮች ጋር ባደረገው ውይይት ተማሪዎች ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብተው እንዲቆዩ የተወሰነ ሲሆን፣ የተለየ የትራንስፖርት ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ደግሞ ተለይተው ስለሚታወቁና ልዩ መታወቂያ/መግቢያ ስላላቸው ትምህርቱ እንዳያልፋቸው አርፍደው ቢመጡም ክፍል እንዲገቡ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡ አልፎ አልፎ ግን የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ተማሪዎች መጥተውም ደጅ መቆም እንደሚፈልጉ ከእነዚህ ጋር እልህ አስጨራሽ ትግልና ክትትል እንደሚደረግና አብዛኛው ተማሪ ግን በሰዓት የሚገባ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አልፎ አልፎ ርዕሰ መምህራን ሲቀያየሩ አሠራሩን እስኪለምዱት ድረስ ‹ያረፈደ ተማሪ አይገባም› ብለው በር የሚዘጉ መኖራቸውን ይህም በውይይት እንደሚፈታ አክለዋል፡፡

የአርፋጅ ተማሪዎች ክትትልና ምክር በየደረጃው እንዳለ፣ ሴቶች ከሆኑ በልጃገረዶች ክበባት በኩል ለምን እንዳረፈዱና ጾታዊ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ከሆነም ውይይት እንደሚረግ፣ በምክርና በክትትል ተማሪዎችን ለማስረዳት እንደሚሞከርና በሕግና ሕግ ተከትሎ ብቻ ውጤት እንደማይመጣ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሪፖርተር ጋር በነበረው ቃለ መጠይቅ ተማሪዎች ሲያረፍዱ ደጅ እንዳይቀመጡ፣ ግቢ እንዲገቡና የመጀመርያው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሲያልቅ ክፍል እንዲገቡ ከትምህርት ቤቶች ጋር በነበረው ውይይት ከስምምነት ተደርሶ ጥሩ ውጤት እንደተገኘበት መናገሩን ያነሳንላቸው አቶ ፀጋዬ፣ ይህ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን፣ ተማሪዎች አርፍደው ሲመጡ ግቢ ገብተው ምክር እንዲያገኙ እንደሚደረግ ነግረውናል፡፡ በተደጋጋሚ የሚያረፍዱ ላይ ቁጥጥርና ቁጣም እንዳለ፣ መግቢያ መታወቂያቸው ተይዞ ወላጅ እንዲያመጡ እንደሚደረግና ከፖሊስ ጋር ተግባብተው የሚሠሩበት አካሄድ እንዳለ ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቢሮው ተማሪዎች ደጅ እንዲቆሙ እንደማያበረታታ፣ ደጅ ይሁኑ የሚል አሠራርም እንደሌሌ ነገር ግን ቢሮው ክትትል ሲያደርግ ተማሪዎች ደጅ ሆነው እንደሚያጋጥሙ አስረድተዋል፡፡

ለምሳሌ የዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህርት ቤት አንዳንድ ተማሪዎች ትምህርት ቤቱ በር ጋር ብቻ ሳይሆን መንገድ ተሻግረው እንደሚቆሙ መታዘባቸውን፣ መምህራን እነዚህን ተማሪዎች ለማስገባት ያለባቸውን ፈተናና ችግሩ የተማሪ ሥነ ምግባር ጉድለት ጭምር እንደሆነ አክለዋል፡፡

አንዳንዴ ተማሪ ያልሆኑ ሁሉ ዩኒፎርም ለብሰው እንደሚቆሙ፣ ትምህርት ቤት ግቡ ሲባል ደብተርም ሆነ መታወቂያ ሳይኖራቸው እንደሚገኙ፣ ተማሪ ያልሆነ ነገር ግን ዩኒፎርም ለብሶ የሚመጣ በመኖሩ ቢፈተሽ መልካም ነው የሚሉት አቶ ፀጋዬ፣ ቢሮው ባጋጠመንው ጊዜ ለፖሊስ እንደሚነግር ገልጸዋል፡፡

ግቡ ሲባሉ እሺ ብለው ከማይገቡ ልጆች ጋር ደጅ ላይ ግብ ግብ መፍጠሩ ዋጋ እንደሌለው፣ በማርፈድ ሰበብ ከትምህርት የሚቀሩ ተማሪዎች ሲኖሩ ግን የሁሉም ተማሪ የወላጅ መረጃና መታወቂያ ስላለ ትምህርት ቤቱ ለወላጅ እንደሚያሳውቅ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ፀጋዬ፣ ይህም ሆኖ ችግሩ መፈጠሩ አልቀረም፡፡ እንደ ምኒልክ ባሉ መሀል ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥም ተማሪዎች ከሥነ ምግባር ሲወጡና ለሱስ ተጋላጭ ሲሆኑ  ይስተዋላል፡፡ ችግሩም በጣም ከባድ ነው፡፡

‹‹እኛ ያለንበት ፈተና ቀላል እንዳይመስላችሁ፡፡ ሰው ሲናገር እንደ ቀላል ያየዋል፡፡ እኛ የጦርነት ያህል ነው ልጆቹን ከሱስ ለማስጣል የምንታገለው፤›› ብለዋል፡፡

ተማሪዎች ወደ ሱስ እንዳይገቡ ለማድረግ ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት ያለ ሲሆን፣ እስከ ታች ትምህርት ቤት ድረስ ገብቶ ይከታተላል፡፡ ብዙ ተማሪዎችም በችግሩ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ ትምህርት ቤት ከመጡ በኋላም ሾልከው ይወጣሉ፡፡ ሱስ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የገቡም አሉ፡፡ ችግሩም አሳሳቢ ስለሆነ በከተማ ደረጃ ከትምህርት ቤቶች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡

ከዚህ ባለፈ ሌብነትና ቅሚያ ድረስ የደረሱ እንዳሉ፣ ትምህርት ቤት ውስጥ የመምህር ሞባይል ቀምቶ የሚወጣ መኖሩን ነገር ግን በሚደረገው ክትትል ችግሩ እየቀነሰ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ትምህርት ቢሮው ብቻ ሳይሆን ወላጅ፣ ትምህርት ቤቶችና ሁሉም ኅብረተሰብ እንዲሠራ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ፀጋዬ፣ ችግሩ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በግሎቹም እንደሚበዛ ለዚህም ሱስ አማጭ ነገሮችን ለማግኘት ከመንግሥት ተማሪዎች ይልቅ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተሻለ ዕድል ስላላቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ተማሪዎች ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን ሠፈርም ስለሚገናኙ የሀሺሽ ሱስ ውስጥ እንዳይገቡ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ፀጋዬ፣ አሁን ላይ ጎረቤት ጭምር እያየ ዝም ማለቱና ኅብረተሰቡም እንዳላየ ሆኖ ማለፉ ችግሩን በትምህርት ቤት፣ በትምህርት ቢሮና በአስተማሪ  ለመቅረፍ አዳጋች እንዳደረገው ጠቁመዋል፡፡

ትውልድን የማጥፋት አጀንዳ ዓለም አቀፍና በገንዘብ የሚደገፍ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ፀጋዬ፣ በትምህርት ቢሮው በኩል የሚረገው የመከላከል ሥራ ካለው ግፊት ጋር ስለማይመጣጠን ማኅበረሰቡ ትውልድን ማጥፋት የጦርነት አንድ አካል መሆኑን ተገንዝቦ እንደ ጥንቱ ሁሉም እጁን አንስቶ ሊያስቆመው እንደሚገባ መክረዋል፡፡

በትምህርት ማኅበረሰብ በኩል ከሚሰጠው ምክር ይልቅ በየሚዲያው የሚተላለፈው በእጅጉ ስለሚበልጥ ይህንን ለማመጣጠን ሁሉም በኃላፊነት ሊረባረብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...