Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቁልፍ እያለ በር መስበር?

ሰላም! ሰላም! ፖለቲካ ዓናይም አንሰማም ብለን ወደ አፍሪካ ዋንጫ መንደር ብንሰደድ እሱም ፖለቲካ ሆኖ አረፈው። ‹‹እግር ኳሳችን በእነ ሴኔጋል፣ ግብፅ፣ ካሜሩንና መሰል ተፋላሚዎች ተርታ ያልተሠለፈበት ምክንያት ምን ይሆን?›› ብሎ አንዱ ገራገር ጥያቄ ሲያነሳ፣ ‹‹የምንከተለው ፌዴራሊዝም ሥርዓት ብቃትን ሳይሆን ኮታን ሙጭጭ በማለቱ ምክንያት ነው…›› ብሎ ሌላው ነገረኛ ይመልስለታል፡፡ በአኅጉረ አፍሪካ ከማንም በፊት ቀድማ ካፍ እንዲመሠረት ትልቅ ሚና የነበራት አገር፣ በስንት መከራ ለተሳትፎ ያህል አልፋ በአንደኛው ዙር ስትሰናበት ሰበብ አለማጣታችን ድንቅ ይለኛል። ‹‹ስንፍናችን ጣሪያ ነክቶ ለዘመናት እንዳላነጋገረን ሁሉንም ነገር ከፖለቲካ ጋር አቆራኝተነው ይቻላል ወይ…›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ‹‹ሰነፍ ሰው ለሰበብ ቅርብ ነው፡፡ ከሌሎች ስኬት ወይም ውድቀት ተምሮ የተሻለ ውጤት ከሚያገኝ ይልቅ፣ የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ዓይነት ምክንያት መደርደር ይቀለዋል፡፡ እንኳንስ ኳሳችን ኑሮአችን ፈቅ የማይለው ጠንክረን ከመሥራት ይልቅ፣ ተኝተን ውለን እያደርን ሰበብ ለመደርደር ማንም ስለማይቀድመን ነው…›› ሲለኝ ራሴን ጭምር መታዘብ እጀምራለሁ፡፡ እውነቴን ነው!

    ለነገሩ ይህንን አሁን ያነሳነውን ጉዳይ ሰፋና ጠለቅ አድርገን ወደ ሕይወታችን ስንመልሰው ብዙ ነገሮች ያስነሳናል። ታዲያ አንድ አውቃለሁ ባይ ደላላ ወዳጄ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው፣ ‹‹አንተ ለካ ፈረንጅም ይኮምካል…›› አለኝ። ‹‹ምን ይላል ታዲያ…›› እለዋለሁ፣ ‹‹የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ዜጎችን በቀን ሦስቴ ከመመገብ አልፎ እንዴት እያዝረጠረጣቸው እንደሆነ አንድ ፈረንጅ ከዓመታት በፊት የጻፈችውን አንድ ምሁር ሲያስነብበኝ እንዳላለቅስ አፈርኩ፣ እንዳልስቅ ፈራሁ። ማርያምን ካላመንከኝ ሊንኩን እልክልሃለሁ…›› ሲለኝ፣ ይኼ ሰውዬ የምን ሊንክ ነው የሚልክልኝ ብየ ባልሰማ ከአጠገቡ መፈትለኬን አረሳውም፡፡ እና ምን ለማለት ነው፣ እኛ በሠራነውም ሆነ ባልሠራነው የሚያሾፈው የሚበዛው በራሳችን ስንፍና መሆኑን ለመናገር ያህል ነው፡፡ ምንም እንኳ ከምሁራን ተርታ ለመሠለፍ የተራራ ያህል ቢከብደኝም፣ የሰበብ ደርዳሪነታችን ምንጩ ጥራት የጎደለው ትምህርታችን ሊሆን ይችላል ብል ትስቁብኛላችሁ ወይስ ታዝኑብኛላችሁ ብዬ የምጨነቅ አይመስለኝም፡፡ ቀልቤ ይነግረኛላ!

እና እላችኋለሁ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ተጠናቆ አረፍ ስንል ኳሱን ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላዩን ሁኔታችንን ብንገመግመው መልካም ሳይሆን አይቀርም። ማንጠግቦሽማ የአፍሪካውያን ተጫዋቾችን ወኔ ካየች በኋላ፣ ‹‹አንበርብር በል በኳሱ ባይሳካልህ ለሚቀጥለው ኦሎምፒክ በረዥም ሩጫ የምትወዳደርበትን ርቀት ምረጥ…›› እያለች ታነቃቃኝ ጀምራለች። ‹‹ዝም ተብሎ ስፖርተኛ ይኮናል እንዴ? ዕድሜ፣ ብርታት፣ ጥንካሬ፣ ትንፋሽ፣ ወጥ አቋም፣ ሚኒማ፣ ወዘተ የሚባል ነገር እኮ አለ…›› ብዬ ሳልጨርስ፣ ‹‹ግዴለም ለእሱ አታስብ። ሁሉን እንደሚሆን ታደርገዋለህ። ዋናው ዘመድ ነው…›› አትለኝ መሰላችሁ። ምን ማለትሽ ነው ብዬ ልቆጣት ስል ከዜግነት ትስስር በስተቀር ዘንድሮ ሁሉም ነገር በትውውቅና በዝምድና መሆኑ ትዝ ብሎኝ ዝም አልኩ። ትዝታዬ ትዝታ ሲቆሰቁስ ደግሞ ልጆች እያለን በአቅራቢያችን ያለ ወንዝ እየሄድን የምንዋኘው ትዝ አለኝ። የምንዋኘው ስል መቼም ይገባችኋል። የዛሬን አያድርገውና መዋኘት እንዲህ ቀላል ነገር አልነበረም። ሲጀመር ከቤት የሚያስወጣ ሰው ሲኖር ነው። የዛሬን ባላውቅም የእኛ ወላጆች ልጆቻቸውን ከውኃ ዋናና ከሰው ዓይን ሰውረው በማሳደግ የሚያምኑ ነበሩ። አንዳንዴ ሳስበው እየተፈራረቀ የምናየው ጭቆናና አፈና ምንጩ እዚያ ይመስለኛል፣ ቤታችን፡፡ አይመስላችሁም!

ታዲያ እንደ ምንም ተሽሎክሉከን አንዴ ከቤት እንወጣ አይደል? ምናልባት ካደግን በኋላ የሚታይብን ተሽሎክልኮ ከአገር የመውጣት አባዜም ጥንስሱ እዚያው ዕድገታችን ሠፈር ይሆናል። እንደ ልጅነታችን ራቁታችንን ወንዝ ለወንዝ ስንቦጫረቅ ውለን ስንመለስ ቀጥታ ወደ ፓስቲ ቤት ነው። ከውኃ የወጣ ሰው የረሃብ ስሜት ስለሚሰማው አይመስላችሁም ፓስቲ ቤት የምንሮጠው። በዘይቱ ታብሰን ለመውዛት እንጂ ጠርሰቅ አድርገን በልተን ስብ ለማቃጠል እንዳልሆነ ይገባችኋል። ምናልባት አንድ ሰው ተጠራጥሮ ደረታችንን ሲያሻሸው አመዳችን ቡን ካለ ወንዝ እንደ ወረድን ይታወቅብናንና ዋጋችን ይሰጠናል። ስለዚህ መፍትሔው የፓስቲ ዘይት መለቅለቅ ነበር እንጂ፣ እንደ ዛሬው ከዋና በኋላ ሻወር ወስዶ ለጋዜጣዊ መግለጫ መዘጋጀት በምን ዕድላችን፡፡ ይህንን ጉዳይ ያነሳሁት ለምን መሰላችሁ? እኛ ከአርባ ምናምን ዓመታት በኋላ ወንዝ ሄደን የዋኘንበት የታሪክ ምዕራፍ ተዘግቶ፣ ስንትና ስንት ታላላቅ ሆቴሎች ዘመናዊ የኦሊምፒክ መዋኛዎች ውስጥ የሚዋኙ ምነው ለውድድር መብቃት አቃታቸው ለማለት ያህል ነው፡፡ አገር ምድሩ ስታዲየም በስታዲየም እየሆነ ሌላው ቢቀር በአራት ዓመት አንዴ ለአፍሪካ ዋንጫ እያለፍን፣ ግማሽና ሩብ ፍጻሜ መድረስ ያቅተናል ለማለት ጭምርም ነው፡፡ ቆይ… ቆይ… ለመሆኑ ረሃብና ጠኔን በማስወገድ ጠግቦ ማደር ለምን ብርቅ ይሆንብናል፡፡ ይመራል እኮ!

መቼም ውይይትን የመሰለ የበሳል ሕዝብ መገለጫ ነገር የለም። የእኛ ነገር አልመች እያለ ከልማቱ ይልቅ ዳንሱ፣ ጭፈራውና ሆታው መብዛቱ፣ ባልበሰለ ፖለቲካዊ ቅኝት በማይረቡ ጉዳዮች መነታረክ ባህል መሆኑና በአጠቃላይ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰከነ መንገድ መነጋገር እያቃተን ይኸው እንደምታዩት ብዙ ያልተዘጉ የጭቅጭቅ ፋይሎች አሉን። ሰሞኑን በኢትዮጵያ ምድር ብሔራዊ ውይይት ለማድረጉን መታቀዱ ያስደሰታቸው አዛውንቱ ባሻዬ፣ ወዲያው የመንደሩን ወጣቶች ሰበሰቡና በምን ጉዳይ ላይ መነጋገር መልካም እንደሚሆን አሳሰቡ። በኋላ ለምን ቅድመ ስብሰባ እንዳሰቡ ስጠይቃቸው፣ ‹‹ኋላ ደግሞ የማይሆን ጥያቄ አንስተው ጀርባቸው ይጠና ቢባል መድረሻ ልጣ…›› ነበር ያሉኝ። ወጣቶቹም የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምን ምን እንደሆኑ ሊገመግሙ ቁጭ አሉ። ጥያቄዎች መቅረብ ሲጀምሩ ባሻዬ መከርከምና ማረም ጀመሩ። አንዱ ተነስቶ፣ ‹‹እኔ የማነሳው ጤናማና የተስተካከለ አቋም ያለው ብቁ ተወዳዳሪ ዜጋ ማፍራት እንደሚቻል ነው። እንደሚታወቀው አገራችን ታስመዘግባለች በሚባለው ፈጣን ዕድገት ሳቢያ ወጣቱ ወገቡ አልታጠፍ፣ ክንዱ አልዘረጋ እስከ ሚል በምቾት ተንገላቷል። ቦርጭ በዝቶ መጫወቻ አድርጎናል። ጫት፣ ሲጋራና አልኮል በስትሮክ ሊጨርሰን ነው። ኳስ ማንከባለል ሲያምረን የምንገኘው ዲኤስ ቲቪ ያለበት ሆቴል ነው። ሌላው ቀርቶ በየአካባቢው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ሳይዘጋጅ አገራችን በዓለም አቀፍ ስፖርታዊ የውድድር መድረኮች ለማግኘት ያሰበቻቸውን ሜዳሊያዎች ታሳድጋለች። ለምን? እስከ መቼ?›› ሲል አዳራሹ በጭብጨባ ደመቀ። ‹‹ራሳችን ለራሳችን እናጨብጭብ እንጂ ሌላውማ እየሳቀብን ነው…›› ብለው ባሻዬ ስብሰባውን በተኑት፡፡ ምን ያድርጉ ታዲያ!

እናላችሁ በእስተርጅና የተቀላቀልኩት ፌስቡክ የሚባል ዘመናዊ ሥራ አስፈቺ ሥራዬን እያስረሳኝ ተቸግሬያለሁ። አንዳንድ ወዳጆቼ ሁኔታዬን እያዩ የማይዳሰሰው ገጻቸው ላይ ሲያሙኝ ተደብቄ ዓያለሁ።  አንበርብር እንዲህ 24 ሰዓት ኢንተርኔት ላይ ተሰጥቶ መዋል የጀመረው በገዥው ፓርቲ ልዩ ቅናሽ የኢንተርኔት መስመር ስለተቀጠለለት ነው ይሉኛል። እኔ ደግሞ ከታማሁ አይቀር በማለት፣ ‹‹ሕገ መንግሥታችን ባጎናፀፈን የእኩልነት፣ የመናገርና የመጻፍ መብት ዛሬ ገበሬው ቀርቶ ፌስቡከሩ ሳይቀር ምርትና ግርዱን በነፃነት እያጨደ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው…›› እላለሁ። ነገረኞች ሊያስበሉኝ ነው መሰል፣ ‹‹አንበርብር በሾርኒ መንግሥትን እየቀለደበት ነው…›› እያሉ ያላግጣሉ፡፡ እንዲህ ስጃጃል ለካ በላዬ ላይ ስንት ቤት ተለቀቀ… ስንቱ ተከራየ.. አትጠይቁኝ። የዕውር ድንብሬን ተነስቼ አንድ እጄ ላይ የነበረ የነዳጁ ቦቴ ላሻሽጥ ከቤቴ ወጣሁ። ተፍ… ተፍ… ብዬ አስማምቼ ለፍጻሜ በነጋታው ቀጠሮ ይዤ ስመለስ አንዲት የድንች ጥብስ ሻጭ ምድጃዋን ስትለኩስ ዓይኔ ገባች። ዓለም በስላቅ፣ በሥጋትና በተስፋ በሚያያት ውዲቷ አገሬ ድንች ፋብሪካ ውስጥ ተጠብሶ ኤክስፖርት የሚደረግበት ጊዜ ናፈቀኝ፡፡ የእኛ ሰው ከአገሩ በስደት ወጥቶ አሜሪካና አውሮፓ ውስጥ ድንች እርሻ ውስጥ ከሚታይ ይልቅ፣ አገሩ ውስጥ በትራክተር እያረሰ ለአፍሪካ ገበያ መትረፍ ቢችል እኮ ድህነት ደህና ሰንብት ይባል ነበር፡፡ ምኞት አይከፋም!

በሉ እንሰነባበት። ነገር ስለበዛ ብቻ አያነጋግርም። አዕምሮ ያለው ሁሉ ያስባል ማለት አይደለም። አፍ ያለው ሁሉ የሚናገረው ትክክል ነው ማለት አልነበረም። ግን እንደምታዩት ዘመኑ ሁሉን ሸጋ፣ ሁሉን ትክክል፣ ሁሉን አዋቂ አድርጎታል። ነገር ሁሉ ሲያታክታችሁ እናንተ የምታደርጉትን ራሳችሁ ታውቃላችሁ። በበኩሌ እኔ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ወደ የምናዘወትራት ግሮሰሪያችን እናመራለን። ‹‹ወይን ያስተፈስህ ልበ ሰብ›› እንዲሉ፡፡ እሱ ደግሞ እንደምታውቁት በምሁራዊ አንደበቱ፣ በዕውቀት በተገራ የማሰብ ክህሎቱ፣ ሕግጋትን በተከተለ ጤናማ ማብራሪያው የፈረሰብኝን ሲገነባልኝ፣ የተዛባብኝ ሲያስተካክልኝ ያመሻል። አንዳንዴ ይህንን መልካም ወዳጅነቱን እያየሁ ምነው ሰው ስለፀጉር አስተካካዩ ብቻ ይጨነቃል። ለምን አስተሳሰቡን የሚከረክምለት፣ የሚያስተምረውና የሚያንፀው ሰው አያፈላልግም እላለሁ፡፡ ታዲያ እንዲህ እየተባባልንና ወቅታዊ ጉዳዮችን እያነሳን ስንጫወት ቆይተን አንድ ጥያቄ አነሳሁለት። መወያየት መልካም ነው!

ጥያቄዬን ያቀረብኩት የብዙዎችን ስሜት ይጋራል በማለት ነው፡፡ ‹‹አንተ ፌስቡክን ጨምሮ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ እንዲህ የቀለጠ ሕዝባዊ መንደር ነው እንዴ?›› ስለው፣ ‹‹ነበር ባይሰበር፣ ግን መጣ መጣና እኛ ጋ ሲደርስ ሳተ…›› አለኝ። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹በአጠቃላይ ይህ ቴክኖሎጂ አመጣሽ የሐሳብ ማሳለጫ መሣሪያ እኛ ዘንድ ከሽፏል አንበርብር። ነጥብ በነጥብ አንነጋገርበትም፣ ሐሳብ ለሐሳብ አናወዳድርበትም። እዚያ ውስጥ የመሸጉ ጉዳች ትናንት ላይ ቆመው ዛሬን ይመዝኑበታል። ያልኖሩበትን ሕይወት እያለቃቀሱበት መንደሩን የለቅሶ ድንኳን ያደርጉታል፡፡ ዛሬ ከ115 ሚሊዮን በላይ ሆነን ምግብና ሌሎቸ መሠረታዊ አቅርቦቶች እንደ ሰማይ ርቀውን፣ ችግር ፈቺ ሳይሆን ችግር አባባሽ አጀንዳ ይመዙብናል፡፡ የሆነ አዙሪት ውስጥማ ገብተናል። እና ታዲያ ምን ይሻላል ሲባል አዋቂ ተብዬዎቹ ይብሳሉ። እንደ አዕዋፍ እንቁላሉን ሰብረን መውጣት አለብን ይሉናል። የሰው ልጅ ከአጥቢ እንስሳት የሚመደብ ነው። ተምጦ ተወልዶ፣ አምጦ ነው የሚወልደው። ያ ማለት ኑሮው በጥረት፣ በትጋት፣ በመከራና አልፎ ካሳለፈው ውጣ ውረድ በመማር የሚመራ ፍጡር ነው ማለት ነው እንጂ፣ በስሜትና በጉልበት እየተመራ ደመነፍሳዊ ሕይወት መምራት የለበትም። ታዲያ ለምንድነው ቁልፉን ፈልገን እናግኘው አናግኘው ሳይታወቅ በር ስለመስበር የሚወራው? ከሐሳብ በፊት ለምን ስሜታዊነት አበረታች ምክር ይቀድማል?›› ሲለኝ ደንዝዤ አዳምጠው ነበር። ለኢትዮጵያ አገራችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሔ የሚሆነወው በር መስበር ሳይሆን፣ አሁንም ነገም ከነገ ወዲያም ቁልፉን ማግኘት ላይ ነው ብሏል ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ብላችሁ አደራ ዩቲዩባችሁና ፌስቡካችሁ ላይ ሼር አርጉልኝ። ሰላም ተመኘሁ። መልካም ሰንብት! 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት