የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 80ኛ ዓመት ክብረ በዓልና የዋና መሥሪያ ቤቱ ግዙፍ ሕንፃ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ንግድ ባንክም ሆነ ሁሉም የኢትዮጵያ ባንኮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ለበርካታ ዓመታት ከለላ ተደርጎለት የውጭ ባንኮች እንዳይገቡ መደረጉን አስታውሰው፣ ከዚህ በኋላ ግን በዚህ ሁኔታ ስለማይቀጠል ባንኮች በአገልግሎት አሰጣጣቸውም ሆነ በሌሎች መስኮች ራሳቸውን በማዘመን ለፉክክር መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ስለሆነ፣ ለዘመናዊ አገልግሎቶች ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ በቴሌኮም ዘርፍ የተጀመረው የሊበራላይዜሽን እንቅስቃሴ ወደ ፋይናንስ ዘርፉ መግባት ሲጀምር መደነጋገር እንዳይፈጠር፣ በተለይ የግል ባንኮች ከወዲሁ ለውድድር ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ተዘግቶ አይቀጥልምና፡፡ በቀጥታ ኢንቨስትመንትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ ኩባንያዎች፣ በኢትዮጵያ መሰማራት የሚችሉት ብቁና ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች ሲኖሩ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ግን በፋይናንስ ዘርፉ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ዘርፎች መዘመን እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡
ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በኋላ ኢትዮጵያ ዘመናዊውን የዕድገት መንገድ ከያዘችበት ጊዜ ጀምሮ ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የአውራ ጎዳና ባለሥልጣን (አሁን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር)፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን (አሁን ኢትዮ ቴሌኮም)፣ የኤሌክትሪክና ኃይል ባለሥልጣን (አሁን የኤሌክትሪክ አገልግሎት/ኃይል)፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መሰል ውስን ተቋማት ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ በቁጥር አነስተኛ ተቋማት ውጪ ብዙዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር ቀርቶ፣ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች አቻዎቻቸው ጋር ሲነፃፀሩ እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡ በተማረ የሰው ኃይል፣ ብቃት ባለው አመራርና ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመታጠቅ ረገድ ብዙ ርቀት ወደ ኋላ የቀሩ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ሥራ በአስቸጋሪነት ከሚታወቁ አገሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡ በተለይ ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ አለመደራጀታቸው አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ለረዥም ጊዜያት ለተቋማት ግንባታ ትኩረት በመነፈጉ፣ ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ከዘመኑ ጋር እኩል መራመድ የማይችሉ ናቸው፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ራሳቸውን በሰው ኃይል፣ ብቃት ባለው አመራርና በዲጂታል ቴክኖሎጂ እያዘመኑ የአገልግሎታቸውን ተደራሽነትና ጥራት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ባንኮች ብቁ ተወዳዳሪ ሆነው ህልውናቸውን ለማስጠበቅ የሚችሉት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለፉክክር የሚያበቃቸውን መሠረት ሲጥሉ ነው፡፡ ለዚህም እጅግ በጣም ዘመናዊና ቀልጣፋ አሠራሮችን በማስፈን፣ ለደንበኞቻቸውም አመርቂ የቁጠባና የወለድ ማዕቀፎችን ተግባራዊ ማድረግና ደንበኞችን የሚያሸሹ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ማስወገድ አለባቸው፡፡ የልማዳዊ አሠራር እስረኛ ከመሆን መላቀቅም አለባቸው፡፡ ደንበኞችን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ አጓጊ ፓኬጆችን ማቅረብ ላይ ማተኮር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በየጎዳናው ዳርቻ ድንኳን እየተከሉ ደንበኞች ለማፍራት የሚደረገው ኋላቀር ድርጊት አያዋጣም፣ ከዘመኑ ጋርም አይሄድም፡፡ ሌላው ሊተኮርበት የሚገባው በመያዥ ላይ የመተሠረተው ብድር (Collateral Based Loan) ጉዳይ ነው፡፡ ባንኮች በሚገባ ከተንቀሳቀሱና ከሠሩበት በተለያዩ ቴክኖሎጂዎችና አዋጭ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎችንና ክህሎት ያላቸውን ወጣቶች በብድር በመደገፍ፣ አብሮ በመሥራትና የትርፍ ሸሪክ በመሆን ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ፡፡ በተለመደው አሠራር መቀጠል ግን ፋይዳ አይኖረውም፡፡
በሌሎች ዘርፎችም ከፍተኛ የሆነ ትራንስፎርሜሽን ያስፈልጋል፡፡ የአገሪቱ ግብርና ካልዘመነ ከድርቅና ከረሃብ መቼም ቢሆን መላቀቅ አይቻልም፡፡ ለብዙ ሺሕ ዓመታት በሞፈርና በቀንበር በሚታረስበት አገር እንዴት ሆኖ ነው አርሶ አደሩ ራሱን ችሎ አገር የሚመግበው? በሠለጠኑት አገሮች ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከአምስት በመቶ በታች የሆነው አርሶ አደር፣ ከአገሩ አልፎ ለኤክስፖርት የሚሆኑ ምርቶችን አምርቶ ነው የተሻለ ሕይወት የሚመራው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በመቶ የሚሆን ሕዝብ በግብርና ተሰማርቶ ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡ ዝናብ ሳይኖር ወይም ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ለረሃብ ይጋለጣሉ፡፡ በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ደግሞ ከአሥር አገሮች ተርታ በእንስሳት ሀብት በምትታወቅ አገር ሥጋ፣ ወተት፣ ቅቤ፣ እንቁላል፣ ዶሮና የመሳሰሉት የሰማይ ያህል የራቁ ናቸው፡፡ አርብቶ አደሩም ሆነ ሌላው ሕዝብ ከዚህ ሀብት እየተጠቀሙ አይደሉም፡፡ አሥራ ሁለት ተፋሰሶችና የተለያዩ የውኃ አካላት ባሏት ኢትዮጵያ፣ በዓሳ ሀብት ለመጠቀም የተደረገው ጥረት አናሳ ከመሆኑም በላይ ያለውንም በአግባቡ መያዝ አልተቻለም፡፡ በጋ ከክረምት ሊታረሱ የሚችሉ መሬቶች ፆም በማደራቸው ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳርና ሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ይገባሉ፡፡ ባስ ሲልም በምፅዋት መልክ በለጋሾች አማካይነት ይገኛሉ፡፡ ግብርናውን በማዘመን ለአፍሪካ ገበያ መትረፍ እየተቻለ፣ በተረጂነት ሥነ ልቦና መሰቃየት ያሳፍራል፡፡
የትምህርት ተቋማቶቻችን ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት የሚሰጠው ደረጃ ላይ ለመደረሱ ብዙ ማጣቀሻዎች ሳይቀርቡ፣ በቅርቡ ለፓርላማ በቀረበ የትምህርት ሚኒስቴር የግማሽ ዓመት ሪፖርት ላይ የሠፈሩ ነጥቦች ብዙ የሚናገሩት አላቸው፡፡ አንደኛው በ2014 ዓ.ም. ለጤና ትምህርት ክፍል ተማሪዎች የሚሰጠውን የሙያ ብቃት መለኪያ ፈተና ለመውሰድ ከተቀመጡት 7,818 ተማሪዎች ውስጥ፣ የመጀመርያውን ዙር ፈተና ለማለፍ የቻሉት 2,404 ያህሉ ወይም 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ይላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ 2,852 ተማሪዎች የመጀመሪያ ዙር የሕግ ትምህርት መውጫ ፈተና ወስደው፣ ከእነዚህ ውስጥ በመጀመርያው ዙር የተቀመጠውን የማለፊያ ነጥብ ያሟሉት 1,447 ተማሪዎች ወይም 50 በመቶ ያህሉ ናቸው ተብሏል፡፡ ሌላውና ሦስተኛው ጉዳይ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ፖለቲካዊ ገጽታ መላበሱ በሪፖርቱ በአፅንኦት መወሳቱ ነው፡፡ በትምህርት ዘርፍ የደረሰው የሞራል ክስረት ከፍተኛ መሆኑን፣ በተለይም ከፈተናዎች መሰረቅና ኩረጃ ጋር ያለው ጉዳይ ተቋማዊ ገጽታ መላበሱን፣ ‹‹የራሴን ክልል ሰዎች አሳልፋለሁ›› እስከ ማለት ተደረሰበት ችግር እንደሆነ ለፓርላማው ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ቀደም ሲልም የብቃት ምዘና ከተደረገላቸው መምህራን ያለፉት በጣም አነስተኛ መሆናቸው መነገሩ አይዘነጋም፡፡ በአጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይችል መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልገዋል ተብሏል፡፡
በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ለተቋማት መዘመን የተሰጠው ትኩረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በፌዴራል ደረጃ በተለይ በመንግሥት ሥር ያሉ ተቋማት እንዲዘምኑ ሙከራዎች ቢኖሩም፣ ብዙዎቹ የውጭ ገጽታ ለውጥ በማድረግ አጥሮቻቸውንና ሕንፃዎቻቸውን ቢያድሱም በባለሙያም ሆነ ብቃት ባለው አመራር ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩም ሆነ በክፍላተ ከተሞችና በወረዳዎች ያለው አሠራር የሚያመለክተው፣ ተቋማት ለውጫዊ ውበት እንጂ ዋነኛ ለሆነው አገልግሎት አሰጣጣቸው ትኩረት መንፈጋቸውን ነው፡፡ የክልሎች ሁኔታም ቢሆን ቢብስበት እንጂ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ የፋይናንስ ተቋማት ለመጪው ጊዜ ከባድ ፉክክር ከወዲሁ እንዲዘጋጁ ሲነገራቸው፣ ሌሎች ዘርፎችም በዚህ ደረጃ እንዲዘጋጁ ለማድረግ መንገዱን ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ ለጤናው ዘርፍ የንግድ ባንክ እንዳስገነባው ዓይነት እጅግ ዘመናዊ ሕንፃዎች ከተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች ጋር ማስገንባት ቢቻል፣ ኢትዮጵያ ሌላው ቢቀር የምሥራቅ አፍሪካ የጤና ማዕከል መሆን ትችላለች፡፡ የማዘጋጃ ቤት፣ የፍትሕ፣ የአስተዳደር፣ የገቢዎች፣ የጉምሩክ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የሌሎች ዘርፎች አገልግሎቶች እንዲዘምኑ ካልተደረገ ተወዳዳሪ መሆን አይቻልም፡፡ ስለዚህ ከፋይናንስ ዘርፉ በተጨማሪ የሌሎች ዘርፎችም ብቃት ይፈተሽ!