ከውጭ የሚመጡ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ለዘርፉ በገንዘብ አቅርቦት የቅድሚያ ቅድሚያ መሰጠቱን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህ የተገለጸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራልና ከክልል ፀጥታ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም ዘርፉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የደንብ ልብስና ተያያዥ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት፣ አቅም መፍጠር በሚያስችል ፕሮጀክት ላይ ማክሰኞ የካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም ከተጀመረው የተማሪዎች ጫማና ቦርሳን በአገር ውስጥ የማምረት ፕሮጀክት ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን፣ በፀጥታ ኃይሎች የደንብ ልብስ በኩልም ከፍተኛ የገበያ ዕድል በመኖሩ ትኩረት መደረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገልጸዋል።
በተለይ የፀጥታ ኃይሎች አልባሳትና ጫማዎች የደኅንነት ሥጋት እንዳይኖርባቸው፣ በአገር ውስጥ እንዲመረቱ የሚያስችል እንደሆነም አቶ መላኩ አክለዋል። ካለው አቅም አንፃር ከአገር ውስጥ አልፎ ለጎረቤት አገሮች መላክን ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በተጀመረው የተማሪዎች ጫማና ቦርሳን በአገር ውስጥ የመተካት ፕሮጀክት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ718 ሺሕ በላይ ጥንድ ጫማዎች መቅረቡን ገልጸው፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ጫማዎች ደግሞ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለፌዴራል ፖሊስና ለክልል ፖሊሶች ከአገር ውስጥ አምራቾች ቀርበዋል ብለዋል።
የአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የሽያጭ ክፍል ኃላፊ አቶ አብዱራህማን ከማል፣ ዘርፉ ከፍተኛ ካፒታልና የሥራ ማስኬጃ የሚፈልግ በመሆኑ በተለይ የገንዘብ አቅርቦት ከፍተኛ ችግር እንደሆነ ገልጸዋል። ዘርፉ ካለው አቅም አንፃር ዕድገቱ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ መንግሥት የገበያ ትስስርን በመፍጠር ድጋፍ ሊያደር ይገባል ብለዋል።
ፋብሪካዎች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከአቅማቸው በታች እያመረቱ የሚገኙት በውጭ ምንዛሪ እጥረትና በብድር አቅርቦት ችግር መሆኑን ገልጸው፣ በተለይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትኩረት ሰጥተው ለመሥራት መስማማታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ማኅበር የቦርድ አባልና የዕድገት ጋርመንት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ደገፉ ደግሞ ለአምራቾቹ የሚሰጡ ጥቅማ ጥቅሞቹ ከውጭ ከሚመጡ ኢንቨስተሮች ያነሰ በመሆኑ፣ ተወዳዳሪ መሆን አለመቻሉን ይገልጻሉ። የምርቶቹ የጥራት ችግር በጥሬ ዕቃ እጥረት የሚከሰት በመሆኑ የገንዘብ አቅርቦቱን በማሻሻል፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እንዲመረት ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
ዘርፉ ከአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ ከሌሎች አገር ድርጅቶች ጋር የሚወዳደር ስለሆነ የተለየ ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸው፣ ለዚህም ካለው ውስን ሀብት ላይ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጠው ፕሮጀክቱ እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን የጥራት ችግር በተለይ በጨርቃ ጨርቅ በኩል በቀለም፣ በጨርቅ ዓይነትና በመሰል የጥሬ ዕቃ ችግሮች፣ እንዲሁም በጫማ ላይ ደግሞ በሶልና በማስቲሽ ጥራት ችግሮች የሚከሰት በመሆኑ ፕሮጀክቱ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።
በአጠቃላይ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ በዓመት ወደ ውጭ የሚላከው ምርት በአማካይ 114 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን፣ ከውጭ የሚመጣው ዓመታዊ አማካይ ምርት ደግሞ 545 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን አቶ መላኩ ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከ1‚700 በላይ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ፣ እንዲሁም ከ200 በላይ ከፍተኛ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩም፣ በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ ባለመሆናቸው በገቢና በወጪ ምርት መካከል ልዩነቱ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።