- የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽንን የማቋቋም ሒደት እንዲቆም ተጠየቀ ነው ያልከው?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር።
- ጥያቄውን ያቀረበው ማነው?
- የጋራ ኮሚቴ እንደሆነ ነው የሰማሁት።
- የጋራ ኮሚቴ ከሆነማ እኛም አለንበት ማለት ነው።
- እንዴት?
- አብዛኞቹ ኮሚቴዎች ላይ እየተሳተፍን ስለሆነ ብዬ ነው።
- እንደዚያ ቢሆን ቀድመን እንሰማ ነበር፣ ወይም ደግሞ ሆነ ብለው እኛን ሳያሳትፉ የወሰኑት ይሆናል።
- ሊሆን ይችላል፣ ለመሆኑ የምክክር ኮሚሽኑን የማቋቋም ሒደቱ እንዲቆም የጠየቁት ለምንድነው?
- ዋና ምክንያት ሆኖ የቀረበው ሒደቱ ግልጽነት የጎደለው ነው የሚል ነው።
- እንዴት? ከረቂቅ አዋጁ ጀምሮ ምክክር ሲደረግበት አልነበረም እንዴ?
- ሒደቱ ገለልኛ አይደለም ያሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረዋል ክቡር ሚኒስትር።
- ምን ምክንያት አቀረቡ?
- በዋናነት ያነሱት ዕጩ ኮሚሽነሮች ሆነው የቀረቡት 42 ሰዎች መሥፈርቱን አያሟሉም የሚል ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ…
- ቆይ… ቆይ… ለኮሚሽነርነት የቀረቡ ዕጩዎች አሉ እንዴ?
- ምን ማለትዎ ነው ክቡር ሚኒስትር? ፓርላማው ሰሞኑን 42 ሰዎችን በዕጩነት ይፋ አድርጎ የለም እንዴ?
- አላቀረበም፣ ዕጩ አይደለም ያቀረበው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን እኮ የ42 ሰዎች ስም ዝርዝር ይፋ ተደርጓል።
- ፓርላማው ይፋ ያደረገው ከሕዝብ ከተቀበለው በርካታ ጥቆማ ውስጥ ለመሥፈርቱ ይቀርባሉ ብሎ የለያቸውን 42 ሰዎች ማንነት እንጂ ዕጩዎች አይደሉም፣ በአዋጁ መሠረት 42 ሰዎች በዕጩነት ሊቀርቡ አይችሉም።
- ስንት ሰው ነው በዕጩነት የሚቀርበው?
- አዋጁ የሚለው 14 ሰዎች በዕጩነት ከቀረቡ በኋላ፣ ከእነሱ ውስጥ ሁሉን በሚያሳትፍ ወይይት 11 ሰዎች ለሹመት ይቀርባሉ ነው።
- እንደዚያ ነው?
- አዎ፣ የተጠቆሙት 42 ሰዎች ከተመዘኑ በኋላ ለመጨረሻ ምዘና ከሚቀርቡት 14 ዕጩዎች መካከል ለኮሚሽነርነት ብቁ የሚሆኑ 11 ሰዎች ማግኘት ካልተቻለም ተጨማሪ ሒደት ይኖራል።
- እህ…
- በዚህ ሒደት ውስጥ ኮሚቴዎችም፣ ፓርቲዎችም፣ የማኅበረሰብ ተወካዮችም ያገባናል የሚሉ ሁሉ እንደሚሳተፉ በአዋጁ ተደንግጓል።
- ታዲያ ጩኸቱ የበረከተው ለምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
- ጩኸቱን የሚያቀናብሩ ሊኖሩ ይችላሉ፣ እሱን እናቆየውና የጋራ ኮሚቴው ያቀረበው ተጨማሪ ምክንያት ምንድነው?
- ሌላ ያነሱት ምን ነበር? አዎ… ሒደቱ አካታች አይደለም ብለዋል።
- ምን ማለታቸው ነው?
- የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎና ውክልና አነስተኛ በመሆኑ ሒደቱ ይቁም ነው የሚሉት።
- ተሳትፎና ውክልና ነው ያልከው?
- እኔ አይደለሁም፣ እነሱ ያሉትን ነው የገለጽኩት፡፡
- ምን ላይ ነው ሴቶችና ወጣቶች ያልተወከሉት?
- ይፋ የተደረጉት ዕጩዎች ውስጥ።
- ይፋ የተደረገ ዕጩ የለም አልኩህ እኮ?
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፣ እነሱ ያሉትን ማለቴ ነው፡፡
- ዕጩ ባልቀረበበት እንዴት እንደዚያ ይላሉ? ወደፊት ከሚቀርቡት 14 ዕጩዎች መካከል ሴቶችና ወጣቶች ሳይወከሉ ቢቀርና ቅሬታውን ቢያነሱ ጥሩ ነው፣ ዕጩ ባልቀረበበት?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ነገሩ ሊገባኝ አልቻለም፣ ብቻ ሒደቱ አካታች አይደለም ገለልተኛ አይደለም በማለት ነው ሒደቱ እንዲቆም የጠየቁት።
- አልገባቸውም ማለት ነው?
- ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- ሒደቱ፡፡
- ምን የሆነው?
- ቅሬታ ለማቅረብ ተሸቀዳደሙ እንጂ፣ ሒደቱን አልተረዱትም ማለቴ ነው።
- ልክ ነው፣ ዕጩ ባልቀረበበት የቀረቡት ዕጩዎች ገለልተኛ አይደሉም ብለው ሒደቱን ለመቃወም መግለጫ ያወጡት ባይገባቸው ነው።
- በእርግጥ ሆነ ብለውም ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡
- ለምን ብለው? እህ… ገባኝ… ገባኝ… እንደዚያ ሊሆን ይችላል፡፡
- ምን?
- ጭር ሲል አልወድም፡፡
- እንደዚያ ማለት ፈልገው ነው አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አይ እኔ እንኳን እንደዚያ ለማለት አልነበረም።
- ምን ሊሉ ነበር?
- መልዕክት ተቀብለው ይሆናል ብዬ አስቤ ነው።
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር? መልዕክት ተቀብለው ይሆናል ነው ያሉት?
- አዎ።
- ከማን?
- ከልዩ መልዕክተኛው!
[ክቡር ሚኒስትሩ የምክክር ኮሚሽን የማቋቋም ሒደት ላይ እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎችን የተመለከተ ማብራሪያ እንዲያቀርቡ በታዘዙት መሠረት በአለቃቸው ቢሮ ተገኝተዋል]
- እንግዳውን የምቀበልበት ሰዓት እየደረሰ በመሆኑ ማብራሪያውን አጠር አድርገህ አቅርብ፡፡
- እንግዳ አለብዎት እንዴ? የአገር ውስጥ እንግዳ ነው?
- ደጋግመው ከመምጣቸው የተነሳ እንግዳ ከምንላቸው ቢሮ ብንሰጣቸው ሳይሻል ይቀራል ብለህ ነው?
- ኦ… መልዕክተኛው ገብተዋል እንዴ?
- አዎ። እስኪ ማብራሪያውን አፍጥነው እባክህ፣ ምን የተለየ ነገር አለ?
- ክቡር ሚኒስትር የምክክር ኮሚሽን የማቋቋም ሒደት ላይ ቅሬታ ቢነሳ ችግር የለውም፣ እንደዚህ ዓይነት ትልቅ አጀንዳ ሒደቱ ላይ ቅሬታ ቢገጥመው እንደ ችግር መታየት የለበትም፣ መታየት ያለበት ዋናው ነገር የሚቀርበው ቅሬታ አመክንዮና ተገቢነት ነው።
- ልክ ነህ፣ ትኩረት መደረግ ያለበት እሱ ላይ ነው።
- ስለዚህ እየቀረቡ ያሉትን ቅሬታዎች በኮሚቴ ደረጃ የተመለከትነው ከዚህ አኳያ ሲሆን፣ በተጨማሪም ከደኅንነትና ከሌሎች ምንጮች የተሰበሰቡ መረጃዎችን በግብዓትነት በመጠቀም ትንታኔ ተሰጥቶበታል።
- ጥሩ፣ ምን ዓይነት ድምዳሜ ላይ ደረሳችሁ?
- እየቀረቡ ካሉት ቅሬታዎች አመዛኞቹ ምክንያትን መሠረት ያደረጉ አይደሉም። ከዚያ ይልቅ የምክክር ሒደቱ የገለልኝነት ጥያቄ እንዲነሳበት ዓላማና ግብ ተይዞ እየተሠራ እንደሆነ ነው የተረዳነው።
- ጥሩ፣ ፍላጎትና ዓላማው ምን እንደሆነ በማስረጃ መተንተን ችላችኋል?
- በሚገባ… የገለልተኝነት ጥያቄው ተቀባይነት እንዲያገኝ በኤንጂኦዎችም ሆነ በፓርቲዎችና በሚዲያ አካላት ደጋግሞ በማስተጋባት ማሳካት የሚፈለጉት ግቦች ሁለት ናቸው።
- ምንድናቸው?
- ዋነኛ ግቡ አገራዊ ምክክሩን የሚመራና የምክክር ውጤቱን የሚተገብር የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ ነው።
- ሌላውስ?
- ይህ ካልተሳካ ደግሞ የምክክር ሒደቱ ገለልተኛ በሆነ የውጭ አካል እንዲመራ ማድረግ ነው፣ ይህ አማራጭ ከመጀመሪያው ጋር የተሳሰረ ነው።
- እንዴት?
- በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የውጭ አካልን ማሳተፍ ያልተለመደ በመሆኑ፣ የመጀመሪያው ተቀባይነት ይኖረዋል የሚል ዕሳቤን ይዟል።
- ጥሩ፣ መልዕክተኛው ደርሰዋል እየተባለ ስለሆነ ቀሪውን በቀጣይ እንመክርበታለን።
- እስካሁን ያቀረብኩት ለእሳቸው የሚበቃ ይመስለኛል፡፡
- ለማን?
- ለመልዕክተኛው!