ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው የወጪ ንግድ ምርቶች መካከል አንዱ የሆነው የአበባ ምርት በዘንድሮ የፍቅረኛሞች ቀን (ቫላንታይን ዴይ) በዋጋም ሆነ በመጠን ከቀዳሚዎቹ ዓመታት ብልጫ ያለው ገቢ እንደተገኘበት ተገለጸ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአበባ ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ ገበያ በሚደራበት የፍቅረኛሞች ቀን ሰሞን ኢትዮጵያ በአበባ ሽያጭ ከፍተኛ መጠን ያለው አበባ ለመሸጥ የቻለችበት እንደሆነም የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ዘውዱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ቴዎድሮስ፣ እስከ ሰኞ የካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ከሦስት ሺሕ ቶን በላይ አበባ ወደ ተለያዩ አገሮች ተልኳል፡፡ ይህም በቀዳሚው ዓመት ከተላከው አንፃር ሲታይ የ30 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ያመለከቱት አቶ ቴዎድሮስ፣ በዋጋም ደረጃ ቢሆን በዘንድሮው የፍቅረኛሞች ቀን ከአሥር በመቶ እስከ 20 በመቶ የዋጋ ጭማሪ የታየበት በመሆኑ የተሻለ ገቢ የተገኘበት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
በዘንድሮ የፍቅረኛሞች ቀን ሰሞን የአበባ ገበያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው ከፍ ብሎ መገኘቱ ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ የገለጹ ሲሆን፣ ለዚህም ዋና ምክንያት የአውሮፓ አበባ አምራቾች ለምርቱ ግብዓት የሚጠቀሙበት የጋዝ ዋጋ ከፍ በማለቱና በበቂ ሁኔታ ባለማምረታቸው መሆኑን አክለዋል፡፡
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የካርጎ እጥረትም በዘንድሮው የፍቅረኛሞች ቀን የፍላጎቱን ያህል አበባ ማቅረብ ባለመቻሉ በዓለም አቀፉ ደረጃ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ሳምንታት ውስጥ የአበባ ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡
እንዲህ ያለው አጋጣሚ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የአበባ አምራች አገሮች ጥሩ ዕድል በመፍጠሩ፣ ከዚህ ቀደም በፍቅረኛሞች ቀን ሰሞን ይላክ ከነበረው የአበባ መጠን በላይ ሊላክ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በዘንድሮው የፍቅረኞች ሰሞን የአበባ ወጪ ንግድ ኢትዮጵያ በዘርፉ የተሻለ የሚባል ገቢ ከማግኘቷ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአበባ ንግድ ወሳኝ የሆነውን የማጓጓዝ ሥራም ኢትዮጵያ መሥራት መቻሏ በልዩ ሁኔታ መታየት ያለበት እንደሆነ አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡
ይህም ባለፈው ሁለት ሳምንታት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያን የአበባ ምርቶች ከማጓጓዝ ባለፈ የሌሎች አበባ አምራች አገሮችን ምርት በማጓጓዝ ቀዳሚ የሚባል አፈጻጸም ሊያሳይ ችሏል ብለዋል፡፡
ይህ ከዚህ ቀደም ብዙም ያልተለመደ እንደሆነ የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ በዘንድሮው የፍቅረኛሞች ቀን ሰሞን ብቻ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያን ጨምሮ የሌሎች አበባ አምራች አገሮችን አበባ በዘመናዊ የካርጎ አውሮፕላኖቹ ማጓጓዝ ችሏል ሲሉም አክለዋል፡፡
በሁለት ሳምንታት ውስጥ አየር መንገዱ ከኢትዮጵያና ከሌሎች አበባ አምራች አገሮች በ86 በረራዎች የአበባ ምርትን ለዓለም አቀፍ ገበያ እንዲቀርብ ማስቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለፍቅረኛሞች ቀን የሚውሉ አበቦችን ካጓጓዙበት 86 በራራዎች ውስጥ 48 የኢትዮጵያ አበባዎችን ያጓጓዘበት ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 36 በረራዎች ደግሞ የሌሎች አገሮች ምርቶችን ያጓጓዘበት ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎን በመጠቀም አበባ ምርታቸውን ካጓጓዙት አገሮች ኬንያ፣ ኢኳዶር፣ ኮሎምቢያና ዩናይትድ ስቴትስ ይገኙበታል፡፡ የእዚህን አገሮች ምርት ያጓጓዘው ዋነኛው የአበባ ገበያ ወደ ሚካሄድበት ከተሞች ነው፡፡
እንደ አቶ ቴዎድሮስ፣ ከ150 ሚሊዮን እስከ 200 ሚሊዮን የሚሆኑ የአበባ ዘንጎች በተለይ ለአውሮፓና ለአሜሪካ ገበያ ይቀርባሉ ተብሎ የሚታመን ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጓጓዘው የአበባ መጠን 110 ሚሊዮን ዘንግ በመሆኑ፣ የዘንድሮን የፍቅረኞች ቀን የአበባ ምርቶች ውስጥ አብዛኛው በኢትዮጵያ አየር መንገድ መጓጓዙን የሚያሳይ ነው፡፡ ዘንድሮ ኢትዮጵያ ከአበባ ንግዱ ብቻ ሳይሆን፣ ምርቱን በማጓጓዝም ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል መፈጠሩ ትልቅ ነገር ነውም ብለዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደምም የኬንያ አበባን ወደ አውሮፓ ያጓጓዘ ቢሆንም፣ እንደ ዘንድሮው ግን የአበባ ምርቶችን ያጓጓዘበት ጊዜ የለም፡፡
በአውሮፓ አንድ የተሰናዳ የአበባ ዘንግ በችርቻሮ መሸጫ ሱቆች በዩሮ እስከ 70 ሳንቲም ሲሸጥ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ዋጋ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ዋጋዎች ሁሉ ከፍተኛ የሚባል እንደሆነም ታውቋል፡፡
በዓለም አቀፍ የፍቅረኛሞች ሰሞን ውጭ ከሚሸጠው አበባ በተጨማሪ በአገር ውስጥም በተለይ በአዲስ አበባ እሑድና ሰኞ ዕለት ገበያው ደርቶ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ያነጋገርናቸው የአበባ መሸጫ መደብሮች ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡ በስጦታ ፕላቲክ የተጠቀለለ አንድ የሮዝ አበባ ዘንግ ከ15 ብር ጀምሮ ሲሸጥ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ቴዎድሮስም ለአገር ውስጥ የሚቀርበው ምርት በዚህ ወቅት የሚጨምር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የአበባ የወጪ ንግድ በኢትዮጵያ ከተጀመረ የ20 ዓመታት ዕድሜ ያለው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከሦስት ዋና ዋና የወጪ ንግድ ምርቶች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ የአበባ ላኪዎችን መረጃ የተመለከቱ ዓለም አቀፍ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ፣ ከዓለም ዓመታዊ የአበባ ገበያ ግማሽ ያህሉን የያዘችው ኔዘርላንድ ነች፡፡ ከኔዘርላንድ ቀጥሎ ኮሎምቢያ፣ ኢኳዶር፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ ከሁለት እስከ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከ120 በላይ አባላት ካሉት ከኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ2014 ዓ.ም. በስድስት ወራት ውስጥ ከአበባ ምርት ብቻ 246.46 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህ ገቢ የተገኘው 54,184 ቶን አበባ ተልኮ ነው፡፡ ይህ አፈጻጸም ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ16 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ የማኅበሩ መረጃ፣ በአሁኑ ወቅት በአበባ የወጪ ንግድ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አሥር አገሮች ኢትዮጵያ በአራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያ የአበባ ምርት በ1,600 ሔክታር መሬት ላይ እየተመረተ ሲሆን፣ በእነዚህ የእርሻ መሬቶች ላይ ከ200 ሺሕ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ሠራተኞች ውስጥ 80 በመቶው ሴቶች ናቸው፡፡