Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአቢሲኒያ ባንክ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ለነበሩት አቶ ዱባለ ጃሌ የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በመሆን ሲያገለግሉ ለነበሩትና በአሁኑ ወቅት በሕመም ምክንያት ችግር ውስጥ ለገቡት አቶ ዱባለ ጃሌ የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ፡፡

በጤና እክል በአሁኑ ወቅት መታከሚያ በማጣት ጭምር ተቸግረው ለነበሩት ለአቶ ዱባለ ጃሌ የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ የሰጠው አቢሲኒያ ባንክ ነው፡፡ አቶ ዱባለ ከፍተኛ በሆነ የኩላሊት ሕመም ለዓመታት ሲቸገሩ እንደነበር ታውቋል፡፡ አስታዋሽ አጥተው ነበር ለተባሉትና የአገሪቱን ከፍተኛ የፋይናንስ ተቋም ሲመሩ የነበሩት አቶ ዱባለ የአቢሲኒያ ባንክ የሰጣቸውን የገንዘብ ድጋፍ የተረከቡት በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆነው ነበር፡፡

የካቲት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. የአቢሲኒያ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በቃ ዘለቀ ድጋፉን ለአቶ ዱባለ አስረክበዋል፡፡

በዕለቱ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው አቶ ዱባለ ስሜታቸውን ለመግለጽ ንግግር እንዲያደርጉ ዕድል የተሰጣቸው ቢሆንም መናገር እንኳን ባለመቻላቸው ሐሳባቸውን መስማት አልተቻለም ነበር፡፡

አቢሲኒያ ባንክ በዕለቱ ለአቶ ዱባለና በተያያዥነትም ለዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የሰጠውን ድጋፍ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የራሳቸው የሆነ ደማቅ አሻራ ያሳረፉት እኝህ አንጋፋ ሰው ከፍተኛ በሆነ የኩላሊት ሕመም እየተቸገሩ እንዳለ ተረድቶ ያደረገው ድጋፍ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

‹‹በእኝህ አንጋፋ የአገር ባለውለታ የገጠማቸው ከፍተኛ የጤና እክል ከግምት በማስገባት ለሕክምና ወጪያቸው ይረዳቸው ዘንድ የገንዘብ ድጋፉን አድርጓል፤›› በማለት ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ባላቸው ገዥዎች መመራት ከጀመረበት እ.ኤ.አ. ከ1959 ጀምሮ ዘጠኝ ገዥዎች ባንኩን መርተዋል፡፡ ከነዚህ መካከል ሰባተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ዱባሌ ጃሌ ሲሆኑ እ.ኤ.አ. ከ1995 እስከ 2006 ለ11 ዓመታት ባንኩንና የባንኩን ኢንዱስትሪ ማገልገላቸውንም አቢሲኒያ ባንክ ያወጣው ያሳያል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያውያን መመራት ከመጀመሩ በፊት እ.ኤ.አ. ከ1913 እስከ 1959 ድረስ ስድስት የውጭ ዜጎች በገዥነት ባንኩን መርተውታል፡፡ ከ1959 በኋላ ግን ባንኩ በኢትዮጵያውያን መመራት የጀመረ ሲሆን፣  እ.ኤ.አ. 1959 የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የባንክ ገዥ የሆኑት አቶ ምናሴ ለማ ነበሩ፡፡ ከእሳቸው በኋላ አቶ ተፈራ ደግፌ፣ አቶ ለገሠ ጥቀሔር፣ አቶ ታደሰ ገብረ ኪዳን፣ አቶ በቀለ ታምራት፣ አቶ ለይኩን ብርሃኑ በተከታታይ የባንኩ ገዥ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ከ1983 ዓ.ም. በኋላ አቶ ለይኩን ኃላፊነታቸውን ሲለቁ እሳቸውን የተኩት አቶ ዱባለ ጃሌ ነበሩ፡፡ አቶ ዱባለን ተክተው የባንኩ ገዥ የሆኑት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ሲሆኑ፣ አሁን ላይ ደግሞ የባንኩ ገዥ በመሆን እያገለገሉ ያሉት ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅዳሜው የአቢሲኒያ ባንክ ፕሮግራም ላይ ባንኩ ለዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል የዳያሊስስ የሕክምና ማዕከል ሁለት የኩላሊት እጥበት ማሽኖች ከአራት ተያያዥ ሕክምና መስጫ መሣሪያዎች ጋር ገዝቶ ማስረከቡ ተገልጿል፡፡ ይህ ለዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ከባንኩ የተሰጠው መሣሪያ ዋጋው 2.7 ሚሊዮን እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

 ባንኩ በአንድ ዓመት ብቻ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለተለያዩ የድጋፍ ጥያቄዎች ከ66 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ሰጥቷል፡፡

በኩባንያው ደረጃ ከሚሰጠው ድጋፍ ባሻገር የአቢሲኒያ ባንክ ሠራተኞች ከወርኃዊ ደመወዛቸው በቋሚነት ተቀናሽ በማድረግ ለኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ለኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከልና ለኢትዮጵየ ቀይ መስቀል ማኅበር ወርኃዊ ድጋፍ እያረጉ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ በአሁኑ ወቅት ከቀዳሚዎች የግል ባንኮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፉ መገለጹ አይዘነጋም፡፡

በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ረዥሙ የሚባለውን ባለ 60 ወለል ፎቅ ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባንኩ በመላ አገሪቱ 683 ቅርንጫፎች ከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች