Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የነዳጅ ዋጋ ንረትን ለመታደግ ታዳሽ ኃይልን የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ለገበያ ቀረቡ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በታዳሽ ኃይል ምንጮች ዘርፍ ላይ እየሠራ የሚገኘው ግሪን ቴክ ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ ገጣጥሞ ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ኩባንያውን ሥራውን በይፋ መጀመሩን በማስመልከት ሐሙስ ጥር 3 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ከአምስት ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ለማቅረብና ለትራንስፖርት አገልግሎት ለማዋል ስለመዘጋጀቱ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወጪ የምታወጣበትን የነዳጅ ምርትን ታሳቢ በማድረግ ኩባንያው የጀመረው እንቅስቃሴ አገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ጠቀሜታ የሚሰጥ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ‹‹እገጣጥማቸዋለሁ›› ብሎ ለዕይታ ያቀረባቸው የተለያዩ ሞዴል ያላቸው ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙት የኤሌክትሪክ ፍጆታ እጅግ አነስተኛ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

የግሪን ቴክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፍፁም ደሬሳ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ሊገጣጠሙና ለገበያ ሊቀርቡ የተዘጋጁት ተሽከርካሪዎች በአንድ ጊዜ የኤሌክትሪክ ቻርጅ እስከ 420 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችሉ ናቸው፡፡

እንዲህ ያሉ ተሽከርካሪዎች በተለይ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከፍተኛ ወጪ እየጠየቀ ያለውን ነዳጅ በመተካት በአነስተኛ የኤሌክትሪክ ዋጋ ማገልገል የሚያስችሉ መሆናቸው፣ ከአካባቢ ጥበቃ አንፃርም ምንም ብክለት የሌላቸው መሆኑ ሌላው ጠቀሜታቸው እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ተሽከርካሪዎቹ ገንዘብ ቆጣቢ ስለመሆናቸው ለማሳየትም በተወሰጠው ምሳሌ በአንድ ጊዜ ሙሉ ቻርጅ  320 ኪሎ ሜትር ለመጓዝ የሚያስችለው የኤሌክትሪክ ኃይል 80 ኪሎ ዋት መሆኑን ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ባለው የኤሌክትሪክ ታሪፍ መሠረት 80 ኪሎ ዋት ኃይል ለማግኘት የሚከፈለው  28 ብር ብቻ መሆኑንና ይህም ሥሌት የአንድ ኪሎ ዋት ዋጋ 0.35 ሳንቲም መሆኑ ነው፡፡ ይህም ተሽከርካሪው ድጋሚ ቻርጅ ማድረግ ሳያስፈልገው ሦስት አራት ቀን ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ካለው የነዳጅ ዋና አንፃር፣ ተሽከርካሪዎቹ እጅግ ጠቃሚና ከፍተኛ ወጪ ቀናሽ ሲሆን፣ በነዳጅ ተሽከርካሪ 320 ተሸርካሪ ኪሎ ሜትር ለመጓዝ ግን አንድ ሺሕ ብር በላይ ነዳጅ የሚጠይቅ በመሆኑ በኤሌክትሪክ የሚሠራው ተሽከርካሪ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ያሳያል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ በይበልጥ በከተማ የታክሲ አገልግሎት እንዲሰጡ ታስቦ የሚገጠሙ ናቸው፡፡

ተሽከርካሪዎቹን ለታክሲ አገልግሎት ለማዋልም ኩባንያው የራሱ የሆነ አሠራር ያዘጋጀ ስለመሆኑ የገለጹት የኩባንያው ኃላፊዎች፣ ለከተማ የታክሲ አገልግሎት የሚውሉትን ተሽከርካሪዎች ለሥራ ፈጠራ ለማዋል እንዲሁም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ቆጥበው የተሽከርካሪዎቹ ባለቤት ከሚሆኑ ደንበኞች ጋር 40/60 በሚል ስምምነት ኩባንያው የሚሠራ መሆኑን ነው፡፡

ይህም አንድ ተሽከርካሪውን ለመግዛት የሚፈልግ ተጠቃሚ 60 የባለቤትነት ድርሻ የሚኖረው ሲሆን 40 በመቶው ደግሞ የኩባንያው ድርሻ ሆኖ የተሰናዳ ነው፡፡

ከዚህ ውስጥ የመኪናው የ60 በመቶው ባለንብረት መኪናውን ለመረከብ ከመኪናው ዋጋ 30 በመቶውን ቀድሞ በመቆጠብ መኪናውን ተረክቦ እንዲሠራ ይደረጋል ተብሏል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ተሽከርካሪዎቹ በእጅ ሳይገቡ ደንበኞችን በመመዝገብ ብቻ ችግር እንዳይገጥማቸው የሚያደርግ ሲሆን፣ ኩባንያው 40 በመቶ ድርሻ መያዙም ለገዥው መተማመኛ እንዲሆን ያግዛል ተብሏል፡፡ የግሪን ቴክ አፍሪካ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሲትራ ዓሊ ደግሞ እንደተናገሩት፣ እንዲህ ያለውን አሠራር የቀረፁት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖች ለማገዝ ነው፡፡ ይህ አሠራር ተሽከርካሪዎቹን በማስተላለፍ ረገድ ምንም ችግር እንዳይገጥም የተደረገ ሲሆን፣ ከዚህ አሠራር የተሻለ ነገር ከመጣ መለወጥ ይቻላል ብለዋል፡፡ ዋናው እንደነዚህ ያሉ ተሽከርካሪዎች ጠቀሜታ ታውቆ ብዙኃን እንዲጠቀሙበት ማድረግ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ 

በኤሌክትሪክ የሚሠሩት ተሽከርካሪዎች አሁን ላይ በቀጥታ የገቡ ቢሆንም፣ ዋናው ዓላማ ግን ኩባንያው በድሬዳዋ ባለው የራሱ ቦታ ላይ መገጣጠሚያ ፋብሪካ በመገንባት፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹን ለመገጣጠም ያለመ ነው፡፡ በተመሳሳይ በአዲስ አበባም የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ለመገንባት የታቀደ ስለመሆኑ የኩባንያው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ አገልግሎቱ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ታክሲዎቹ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሞሉበት ስቴሽኖች በተለያዩ ቦታዎች እንዲተከሉ የሚደረግ ሲሆን፣ ራሱን የቻለ የተሽከርካሪዎች የጥገና ጋራጅ እንደሚኖረው ወ/ሮ ሲትራ ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው እነዚህን ምርቶች በ40/60 አሠራር የሚያስረክበውም ውለታ ከፈጸመው አፍሪካ ቪሌጅ ከተባለ ማክሮ ፋይናንስ ተቋም ጋር በመተባበር እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ አሁን ባለው ሁኔታ ጠቃሚ መሆናቸውን ለማስረዳት በተሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ ከነዳጅ ተሽከርካሪዎች አንፃር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሰርቪስ ወጪ የሌላቸው መሆኑ፣ የሞተር ዘይት የሞተር ዘይት በፊሊተር፣ የአየር ፊሊተር፣ ካንዴላና የመሳሰሉት ወጪዎች የሌላቸው መሆኑም ለአብነት ተጠቅሷል፡፡ የጥገና ወጪ የሌላቸው መሆኑም ሌላ መለያቸው ነው ተብሏል፡፡

እንደ ፍፁም (ኢንጂነር)  ገለጻ ተሽከርካሪዎቹ ቻርጅ የሚደረጉት በቤት ውስጥ ባለ ኤሌክትሪክ ጭምር በመሆኑ ሌላው የተመቻቸ ዕድል ነው ይላሉ፡፡ በመካከለኛ ፍጥነት ቻርጅ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጁ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡

ተሽከርካሪዎቹን ቻርጅ ለማድረግ ቻይ ቻርጅ በሚባለው የመካከለኛ ፍጥነት ቻርጅ ሙሉ ቻርጅ ለማድረግ ከ30 ደቂቃ እስከ ሦስት ሰዓት የሚፈጅ ሲሆን፣ ፋስት ቻርጅ በሚባለው ደግሞ ከሦስት ደቂቃ እስከ 30 ደቂቃ ይፈጃል ተብሏል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል በማይኖርበት ወቅት ሊያስተጓጉላቸው አይችልም ወይ? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ቢሆንም  ፍፁም (ኢንጂነር) ግን ‹‹ይህንን ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት ድርጅታችን ዝግጅት አድርጓል›› ብለዋል፡፡

በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ፋስት ቻርጅ ስቴሽኖችን መገንባት እንደሚያስፈልግ ታምኖበት ይህንኑ ለማድረግ ለስቴሽኖቹ የሚሆኑ ቦታዎችን ለማግኘት ለአዲስ አበባ አስተዳደር ጥያቄ እዳቀረበ አመልክተዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮና ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በጥምር እየተሠራበት መሆኑንና አሁን ላይ ግን የኩባንያው ዋና መሥሪያ በሆነበት ቦታ ላይ አንድ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ ስቴሽን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የኃይል ማሙያ ጣቢያው ከሶላር ያገኘውን ኃይል ወደ ኤሌክትሪክ በመቀየር ተሽከርካሪዎቹን የሚሞላ እንደሆነም የተገለጸ ሲሆን፣ አመቺ በሆኑ ቦታዎች እንደሚከተሉም የኃይል መሙያ ጣቢያዎች

ተሽከርካሪዎቹን ለምን በኤሌክትሪክና በነዳጅ የሚሠሩ ማድረግ ተመራጭ አይሆንም? ለሚለው ጥያቄ ፍፁም (ኢንጂነር) እንደገለጹት ይህ ድርጅታቸው ታዳሽ ኃይልን ለማስፋፋት ከያዘው ውጥን አንፃር የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በኤሌክትሪክ ብቻ እንዲሠሩ ስለተፈለገ እንጂ በሁለቱም ሊሠሩ የሚችሉ ተሽከርካሪዎችን ማስገባት ወይም መገጣጠም ይቻላል፡፡ ነገር ግን የተሻለው በኤሌክትሪክ ብቻ የሚሠራ ስለመሆኑ ይህንኑ ለመተግበር ተፈልጎ ነው፡፡ በኤሌክትሪክ ችግር ተሽከርካሪዎቹ እንዳይስተጓጎሉም የተለያዩ አማራጮች ሰለሚቀርቡ ችግር እንደማይኖርም ጠቅሰዋል፡፡

አንዳንድ ሊገጣጠሙ የታሰቡ ተሽከርካሪዎችም የሚፈልጉትን የኤሌክትሪክ ኃይል በሶላር ኢነርጂ እንዲሠሩ ዲዛይን የተደረጉ ናቸው፡፡ በዚህ መንገድ የሚሠሩ የሁለት ተሽከርካሪዎች ሞዴልም መግባታቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንደ ኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ በኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባው የተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ እስኪገነባ ድረስ ኩባንያው በዓለም ላይ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራችነታቸው ከሚታወቁ አራት የቻይና አምራቾች ጋር በመሆን አምስት ሺሕ ተሽከርካሪዎችን ወደ ገበያ የሚያስገባ ሲሆን፣ ከሰባት ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎችን ደግሞ በግሪን ቴክ የኤሌክትሪካል መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በመገጣጠም ለገበያ የሚያቀርብ መሆኑን ገልጿል፡፡

ግሪን ቴክ አፍሪካ ከስድስት ዓመታት በፊት በታዳሽ ኃይል ዙሪያ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ለመሰማራት በአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ኩባንያ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች