Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የምጥ ማስታገሻ ሕክምና እና መንገዱ

የእናቶችንና የሕፃናትን ጤና ለማሻሻል በተለይም መከላከል በሚቻሉ ምክንያቶች የሚደርሰውን ሕመምና ሞት ለመታደግ በየዓመቱ ጥር ወርን ‹የጤናማ እናትነት ወር› በሚል ተሰይሞ ወሩን በሙሉ በተለያዩ ዝግጅቶች ተካሂዷል፡፡ ‹‹በማንኛውም ሁኔታ ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶችን ሞት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንግታ›› በሚል መሪ ቃል ወሩን በተለያዩ ዝግጅቶች አሳልፏል፡፡ የጤናማ እናትነት ወር ዝግጅቶችን ካሰናዱት አንዱ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ነው፡፡ በእናቶች ጤና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በሆስፒታሉም ሆነ በኮሌጁ ስላሉት ተግባራት የማኅፀንና የጽንስ ስፔሻሊስትና ኮሌጁ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር ማርያማዊት አስፋው (ዶ/ር)ን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በሆስፒታሉ የሚሰጠው የምጥ ማስታገሻ ሕክምናን ቢገልጹልን?

ዶ/ር ማርያማዊት፡- ብዙ ዓይነት ናቸው፡፡ ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል በመርፌ እየታገዘ በጀርባ፣ በጡንቻና በደም ሥር የሚሰጥ የምጥ ማስታገሻ ሕክምና ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል በጀርባ በኩል የሚሰጠው የምጥ ማስታገሻ የሚውለው ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸው እናቶች ብቻ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው በጀርባ በኩል እንደ ቀጭን መርፌ ወይም ቲተር የመሰለ ቲዩብ እንዲገባ ይደረጋል፡፡ በዚህም ቲዩብ ውስጥ የማስታገሻ መድኃኒቱ በተወሰነ ሰዓትና እንደ ሕመሙ ልክ እየታየ ይሰጣል፡፡ የተቀሩት መድኃኒቶች ግን ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ችግር ለሌለባቸው እናቶች ይሰጣሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት መድኃኒቶች ግን በምጥ ጊዜ የሚከሰተውን ሕመም የማስታገስ አቅማቸው አነስተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጀርባ የሚሰጠው የምጥ ማስታገሻ ተጓዳኝ በሽታ ለሌለባቸው እናቶች ለምን አይሰጥም?

ዶ/ር ማርያማዊት፡- በጀርባ የሚሰጡት መድኃኒቶች ተጓዳኝ በሽታ ለሌለባቸውም እናቶች እስካሁን ድረስ ያልተሰጠው በኮሌጁ አቅም ማነስ፣ በባለሙያዎች ዕጦትና ለሕክምናው የሚውሉ ፋሲሊቲዎችና ግብዓቶች አለመኖር ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን በእናቶችና ሕፃናት ሕክምና ማዕከል የጽንስ እና ማኅፀን የሰመመን ሕክምና ክፍሎች የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችም የተጠቀሱትን ችግሮች በመፍታትና የጎደሉትንም በማሟላት ሕክምናውን እስካሁን ላላገኙ እንዲዳረስ ለማድረግ የሚያስችል ተነሳሽነት (ኢኒሼቲቭ) አዘጋጅተው ለተግባራዊነቱም ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በማከናወን ላይ ናቸው፡፡   

ሪፖርተር፡- የተጠቀሰው እንቅስቃሴ እስካሁን ያስገኛቸው ውጤት አሉ?

ዶ/ር ማርያማዊት፡- እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ ከተገኙትም ውጤቶች መካከል ከሁለቱም ክፍሎች የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ተሳታፊ የሆኑበትና አፈጻጸሙን የሚከታተልና ሁኔታዎችን የሚያመቻች ግብረ ኃይል ለማቋቋም ተችሏል፡፡ ግብረ ኃይሉም በኢኒሼቲቩ ዙሪያ ከኮሌጁ ማኔጅመንት ጋር ተወያቶ አመርቂ ውጤት ላይ ይደርሳል፡፡ ከዚህም ሌላ ሕክምናውን መስጠት የሚያስችል መመርያና የማሠልጠኛ ፓኬጆች ለማዘጋጀት ተችሏል፡፡ ወደ 50 የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች በምጥ ጊዜ የሚከሰተውን ሕመም ለማስታገስ በሚያስችል ላይ ያተኮረ ሥልጠና ተከታትለዋል፡፡ ለሕክምናው የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ ግብዓቶችም በመቅረብ ላይ ናቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- እንደነገሩን ከሆነ አብዛኛው ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ ይህ ከሆነ ታዲያ ተጓዳኝ በሽታ ለሌለባቸው እናቶች በጀርባ በኩል የሚሰጠው የምጥ ማስታገሻ መቼ ይጀመራል?

ዶ/ር ማርያማዊት፡- ከአንድ ወር በኋላ ይጀመራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ አንዱ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸውም ሆነ ለሌለባቸው እናቶች በጀርባ በኩል የምጥ ማስታገሻ ሕክምና በአንዳንድ የግል ጤና ተቋማት ብቻ እንደሚሰጥ ነው፡፡ ኮሌጁ ከአንድ ወር በኋላ የሚጀምረው ይህ ዓይነቱ የሕክምና አገልግሎት ከመንግሥት የጤና ተቋማት ብቸኛውና የመጀመርያው ያደርገዋል፡፡   

ሪፖርተር፡- ምጥ የሚፀናባቸው እናቶች አሉ?

ዶ/ር ማርያማዊት፡- ይለያያል፡፡ ለትንሽ ሰዓት የሚያምጡ አሉ፡፡ የሚቆይባቸውም አይታጡም፣ ወዲያው አምጠው የሚወልዱም አሉ፡፡ ሆስፒታሉ ግን ወቅቱ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የማዋለጃ ክፍል አለው፡፡ በወር እስከ 1,000 ለሚደርሱ እናቶች አገልግሎት ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ሆስፒታላችሁ ለእናቶች ጤና አገልግሎት ሲሰጥ ብዙ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ከዚህ አኳያ ምን ዓይነት ዕድገት አሳይቷል ይላሉ?

ዶ/ር ማርያማዊት፡- ለጥያቄህ መልስ ከመስጠቴ በፊት በሆስፒታል ውስጥ የሚተገበር አንድ ተነሳሽነት (ኢኒሼቲቭ) አለ፡፡ እሱም ‹‹ሆስፒታል ከሕመም ነፃ መሆን አለበት›› የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት ምንም ዓይነት በሽታ/ሕመም አይኖርም ማለት አይደለም፡፡ ለሕመሙ የሚሆን ጥራቱን የጠበቀና ፍትሐዊነትን የተላበሰ ሕክምና በቶሎ መስጠትን የሚያመላክት፣ የሚያነሳሳ ኢንሼቲቭ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ኢኒሼቲቭ ከእናቶች ጤና ጋር ሲያያዝ ደግሞ የሕክምና አገልግሎቱ መጠናከር ብቻ ሳይሆን እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ኮሌጁ በሆስፒታሉ ውስጥ የሚሰጠው የወሊድ አገልግሎት ኮሌጁ በሚያስተዳድራቸው ጤና ጣቢያዎች ጭምር እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በየትኞቹ ጤና ጣቢያዎች ነው እንዲስፋፋ የተደረገው?

ዶ/ር ማርያማዊት፡- የነፍሰ ጡር ወይም የወሊድ እናቶችን ጤናን መጠበቅ አምራችና ጤናማ ትውልድን መፍጠር ማለት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ለእናቶች የሚደረግ ሕክምናና እንክብካቤ መጠናከርና መስፋፋት ይገባዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ኮሌጁ ይህንን አገልግሎት እናቶች ወዳሉበት አካባቢ የማስፋፋት ሥራ አከናውኗል፡፡ አገልግሎቱም የተስፋፋው በኮሌጁ ሥር በሚተዳደሩ በኮልፌና ፈለገ መለስ ጤና ጣቢያዎች ነው፡፡ ጤና ጣቢያዎቹ ከአቅማቸው በላይ የሆነውን ሕክምና ወደ ሕክምና ኮሌጁ ሪፈር ያደርጉታል፡፡

ሪፖርተር፡- በእነዚህ ጤና ጣቢያዎች በቀዶ ሕክምና የማዋለድ አገልግሎት እየተሰጠ ነው ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ማርያማዊት፡- በቀዶ ሕክምና የማዋለዱ ሥራ በሙከራ ደረጃ ተጀምሯል፡፡ በጤና ጣቢያ ደረጃ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ማስጀመሩን ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅን ቀዳሚ ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሾተላይ ሲባል እንሰማለን፡፡ ለመሆኑ ሾተላይ ምን ማለት ነው? በዚህ ላይ ያተኮረ የሕክምና አገልግሎቶች ትሰጣላችሁ?

ዶ/ር ማርያማዊ፡- ሾተላይ ማለት የእናትና የሕፃኑ ደም ካለመመጣጠኑ የተነሳ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱም ችግር ሕፃኑን እስከ ሞት ሊያደርሰው ይችላል፡፡ ካከናወንናቸው ትልልቅ ሥራዎች መካከል ችግሩን ለማከም የሚያስችል አገልግሎት መጀመራችን ነው፡፡ ይህም አገልግሎት በኮሌጁ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀርም በሁሉም ሆስፒታሎች እንዲስፋፋ ለማድረግ ባለን ፅኑ ፍላጎት መሠረት፣ ከተለያዩ ጤና ተቋማት ለመጡ ሐኪሞች በሕክምናው ላይ ትኩረት ያደረገ ትምህርት ኮሌጁ እየሰጠ ነው፡፡     

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...

በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን የሰላም ንግግር አሜሪካንን ጨምሮ ተመድና ኢጋድ እየታዘቡ ነው

ለሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት...