Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየሩሲያ ወታደሮች ከዩክሬን ድንበር ወደ ጦር ሠፈራቸው መመለስ ጀመሩ

የሩሲያ ወታደሮች ከዩክሬን ድንበር ወደ ጦር ሠፈራቸው መመለስ ጀመሩ

ቀን:

ዩክሬንና ሩሲያ ውጥረት ውስጥ ከገቡ ስምንት ዓመታት ያህል ቢቆጠሩም፣ ፍጥጫቸው ወደለየለት ጦርነት ሊያመራ ይችላል የተባለው ከወር በፊት ነው፡፡ ምዕራባውያን ‹‹ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ነው›› በማለት በሩሲያ ላይ ባበሩበትና ከዩክሬን ጎን በቆሙበት በሰሞነኛው ፍጥጫ፣ ዩክሬን የውክልና ጦርነት ሰለባ ትሆናለች የሚለው ሥጋት አይሏል፡፡

ሩሲያ ዩክሬንን የመውረር ፍላጎት እንደሌላት፣ ዩክሬንም የሩሲያ ወታደሮች ወደ ድንበሯ መጠጋት ሥጋት ቢሆንም ከቀደመው የተለየ ነገር እንደሌለ ብታሳውቅም፣ ሩሲያ ከማክሰኞ የካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በፊት ዩክሬንን ትወራለች ተብሎ ከወደ አሜሪካ የተሰማው ዜና የላቀ ሥጋት ፈጥሯል፡፡

የዩክሬንና የሩሲያ ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት ሁሉም ምዕራባውያን ቢያነሱም፣ በጎን ከሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጋር በመሆን ጦራቸውን እያጠናከሩ፣ ለዩክሬንም ድጋፍ እየሰጡ መሆኑ ከዲፕሎማሲው ይልቅ የጦርነቱ ሥጋት እንዲያይል አድርጎታል፡፡

- Advertisement -

ዩክሬንን የኔቶ አባል ለማድረግ ምዕራባውያኑ የሚያደርጉት ሩጫና፣ የሩሲያ ዩክሬን የኔቶ አባል መሆን የለባትም የሚለው አቋም የፈጠረው ልዩነትም ዩክሬንን በሩሲያና በአውሮፓውያኑ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ሆኗል፡፡

ሩሲያ ወደ ዩክሬን ድንበር 130,000 ወታደሮች አስጠግታለች፣ በማንኛውም ሰዓት ዩክሬንን ትወራለች በማለት፣ በተለይ በዩክሬን ምድር ከሩሲያ ጋር ጦርነት ለመግጠም ዝግጅት ባጠናቀቁበት ዋዜማ፣ ሩሲያ በዩክሬን ድንበር ልምምድ ሲያደርጉ ነበር ያለቻቸውን ወታደሮቿን ወደ ጦር ሠፈራቸው መመለስ ጀምራለች፡፡

በዩክሬንና በሩሲያ መካከል ላለው አለመግባባት መፍትሔው ጦርነት ሳይሆን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ወሳኝ ነው በማለት ስትወተውት የነበረችው ጀርመን ጉዳዩን በዲፕሎማሲ ለመጨረስ ማግባባቷን ቀጥላለች፡፡

gee

የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ትናንት ሞስኮ የገቡ ሲሆን፣ አውሮፓን ሊያተራምሳት፣ ዩክሬንን ሊያወድማት ይችላል ተብሎ የተሠጋውን የጦርነት ፍጥጫ የማስቀልበስ ግብ ይዘዋል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ኢንተርፋክስ የዜና ወኪል በበኩሉ፣ በዩክሬን ድንበር የጦር ልምምድ ሲያደርሱ የነበሩት የሩሲያ ወታደሮች ወደ ጦር መንደራቸው መመለስ መጀመራቸውን የሩሲያን መከላከያ ሚኒስቴር ጠቅሶ አስፍሯል፡፡ ይህም በሞስኮና በምዕራባውያኑ መካከል ወደጦርነት ሊያመራ የነበረውን ፍጥጫ ያረግበዋል ብሏል፡፡

ሩሲያ በባረንስት ባህር የጦር መርከቦች ልምምድ እያደረገች ሲሆን፣ በሩሲያና በኖርዌይ አማካይ ሥፍራ በአርክቲክ ባህር የሚደረግ ልምምድ ሞስኮ ዩክሬንን ልትወር ነው የሚል ፍርሃትን አንግሷል፡፡

ዩክሬንን የመውረር አቋም እንደሌላት በተደጋጋሚ ስትገልጽ የቆየችው ሩሲያ፣ በምዕራባውያኑ የተከፈተባትን የጦርነት ጉምታ ‹‹ምዕራባውያን ያለአንድም ተኩስ ተደምስሰዋል›› ስትል የምዕራባውያኑ ፕሮፓጋንዳ ሐሰት እንደነበር አስታውቃለች፡፡

‹‹ፊብሩዋሪ 15 (የካቲት 8) የምዕራባውያን ፕሮፓጋንዳ የወደቀበት›› ስትል የገለጸችው ሩሲያ፣ በዩክሬን ድንበር የነበራትን ወታደራዊ ልምምድ ጨርሳ ወታደሮቿን ወደጦር ሠፈራቸው መመለስ መጀመሯን አስታውቃለች፡፡

የሩሲያውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዘካሮቫ ይህን ያስታወቁት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ልታደርግ ሰዓታት ቀርተዋል ብለው የአሜሪካና የአውሮፓ ባለሥልጣናት ባስታወቁ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ነው፡፡

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴርም፣ የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን ድንበር በምትገኘው ቤላሩስ የነበራቸውን ልምምድ መጨረሳቸውንና ከሥፍራው እንደሚወጡም አሳውቋል፡፡ ምዕራባውያን ባለሥልጣናት ‹‹ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ነው›› ብለው በየሚዲያዎቻቸው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መክፈታቸው በአካባቢው ላይ ከባድ ውጥረት መፍጠሩን የዘገበው የሩሲያው ቴሌቪዥን አርቲ፣ ክሪምሊን ምንም ዓይነት ወረራ እንደማታደርግና፣ በእንግሊዝኛ የሚዘጋጁ መገናኛ ብዙኃን በሕዝቡ ላይ ፍርሃት እንዳነገሡበት ገልጿል፡፡

የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በበኩላቸው፣ ሞስኮ ለደኅንነቷ ዋስትና እንደምትፈልግና የኔቶን መስፋፋት እንደማትፈቅድ፣ ለዚህም ጉዳዩን በዲፕሎማሲ መፍታት እንደሚቻል ገልጸው፣ ‹‹ምዕራባውያን ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯ የማይቀር ነው›› ብለው የሚያስራጩት ሪፖርት ወደ መረጃ ሽብር አድጓል ብለዋል፡፡

(ጥንቅር በምሕረት ሞስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...