አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት እ.ኤ.አ. ከ1985 ወዲህ በእጅጉ የሻከረበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ከቀዝቀዛው ጦርነት በኋላና በፊት ሁለቱ አገሮች በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የሚናቆሩ ቢሆንም፣ አሜሪካ በ2016 ካደረገችው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በኋላ ነው ችግሮች እየጎሉ የመጡት፡፡
አሜሪካ በምርጫው ሩሲያ ጣልቃ ገብታለች፣ በ2020 ምርጫም ሙከራ አድርጋለች ስትል ሩሲያን ትኮንናለች፡፡ ክሪሚያ ወደ ሩሲያ መቀላቀሏ ሕጋዊ አይደለም የሚሉና የአሜሪካን ፍላጎት ይጋፋሉ በሚባሉ ጉዳዮች ሁሉ አሜሪካና ሩሲያ ሁሌም እንደተቃረኑ ነው፡፡
ሩሲያ በፀጥታው ምክር ቤት ያላት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብትና ይህም በርካታ የአሜሪካ ፍላጎቶችን ማክሸፍ፣ ሁለቱም ኑክሌር መታጠቃቸው፣ በወታደራዊ አቅም መፎካከራቸው፣ የቻይናና የሩሲያ ወዳጅነት አሜሪካ ከሩሲያ ጋር በቃላት ጦርነት እንድትፋለም ካደረጉ ጉዳዮች ይጠቀሳሉ፡፡
ሩሲያና አሜሪካ የኑክሌር ኃያለ መንግሥታት ሆነው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ትብብር መፍጠር ሲገባቸው፣ የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂ ሩሲያና ቻይና ቀዳሚ የአሜሪካ ደኅንነት ሥጋት ናቸው ብሎ ማስቀመጡ ይህ እንዳይሆን አድርጓል ሲሉ በአሜሪካና አውሮፓ የውጭ ፖሊሲ ተንታኝ አንጄላ ስቴንት ይገልጻሉ፡፡
በዓለም የኑክሌር፣ የባዮሎጂካልና ኬሚካል መሣሪያዎች እንዳይስፋፋ ሰላምን ማስጠበቅ የሚጠበቅባቸው አገሮቹ አሁን ላይ ጦርነት ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል፡፡
ስቴንት እንደሚሉት፣ ዓለም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሽብር፣ የኮቪድ-19 እና ሌሎችም ችግሮችን በጋራ መፍታት በሚጠይቅበት በአሁኑ ወቅት፣ የአሜሪካና ሩሲያ ግንኙነት እ.ኤ.አ. በ1985 ከነበረው በባሰ መሻከር ተግዳሮት ነው፡፡
አገሮቹ እርስ በርሳቸው ቀጥታ ጦርነት ውስጥ ባይገቡም በሶሪያ፣ በሊቢያና በየመን ጎራ ለይተው በውክልና ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ዩክሬንን እንደ ምክንያት በማስቀመጥ ፍጥጫ ውስጥ ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ. በ1922 የዛሬዎቹን ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ጆርጂያ፣ ቤላሩስ፣ አርመኒያ፣ አዘርባጃንን ጨምሮ 15 ግዛቶችን ይዞ የተመሠረተው ሶቪየት ኅብረት በ1991 ፈራርሶ 15 የተለያዩ አገሮች ቢፈጠሩም፣ ሁሉም በሚባል ደረጃ መረጋጋትን አላገኙም፡፡
የአርመኒያ ከአዘርባጃንና የሩሲያ ከዩክሬን ጋር ያላቸው ግጭት ደግሞ የጎላ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2014 በዩክሬንና በሩሲያ መካከል በተቀሰቀሰ ጦርነት ክሪሚያ ከዩክሬን ተገንጥላ ዳግም ወደ ሩሲያ መቀላቀሏ፣ በሩሲያና በዩክሬን መካከል የነበረውን የተሻለ ግንኙነት አሻክሯል፡፡ መሻከሩ ደግሞ በሁለቱ አገሮች ተወስኖ አልቀረም፡፡ አሜሪካና የተቀሩት ምዕራባውያንም ለዩክሬን ወግነው ሩሲያን እየኮነኑ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ የጦርነት ሥጋት ያጠላበት የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡
ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል፣ ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ነው በሚልም አሜሪካ 8,500 ወታደሮቿን በተጠንቀቅ ማዘጋጀቷን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ፣ አውሮፓና የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ም በአባል አገሮቹ መሪዎች በተደረገ ስምምነት ኅብረት መፍጠራቸው ተሰምቷል፡፡
‹‹ሩሲያ በዩክሬን ድንበር ጦሯን እየገነባችና እያስፋፋች ነው›› በሚል በሩሲያ ላይ ለመዝመት የተቀናጁት ምዕራባውያን፣ ሩሲያ በዩክሬን ድንበር 100 ሺሕ ወታደሮች ማስፈሯን ገልጸዋል፡፡
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት የመግባት ዕቅድ እንደሌላት በተደጋጋሚ ብታስታውቅም፣ አሜሪካ፣ ካናዳና እንግሊዝ ዜጎቻቸው ከዩክሬን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
‹‹ምዕራባውያን ሩሲያ በዩክሬን ድንበር ጦሯን እያበዛች ነው፣ ዩክሬንን ልትወር ነው›› የሚል አጀንዳ ይዘው ትብብር እየፈጠሩና ወታደሮች እያቀናጁ ቢሆንም፣ የጉዳዩ ባለቤት ዩክሬን፣ ‹‹ዩክሬን ድንበር ላይ ያለው የሩሲያ ወታደር ግንባታ የጎላ ጭማሪ አላሳየም›› ስትል አስታውቃለች፡፡
የዩክሬን ብሔራዊ ደኅንነትና የመከላከያ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ኦሌክሲ ዳኒሎቭ፣ ‹‹ሩሲያ በዩክሬን ድንበር ያላትን የወታደር ብዛት በጉልህ ደረጃ አልጨመረችም፤›› ማለታቸውን የዩክሬኑ ዩክሬንፎርም በድረ ገጹ አሥፍሯል፡፡
ዩክሬንፎርም እንዳሠፈረው፣ ምክር ቤቱ ሰኞ ጥር 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ በዩክሬን ድንበር ያሉ የሩሲያ ወታደሮች ብዛት አልተቀየረም፡፡
ዋና ጸሐፊው ዳኒሎቭ፣ ‹‹ሩሲያ በዩክሬን ድንበር 109 ሺሕ ወታደሮች አሏት፡፡ ድጋፍ ስጪ የሚባሉ ደግሞ ከ10 ሺሕ እስከ 11 ሺሕ ናቸው፡፡ ይህ ለዩክሬን አጋሮች [ምዕራባውያን] ትልቅ አጀንዳ ቢሆንም፣ ለዩክሬን ዜና አይደለም፡፡ የወታደር ቁጥሩ በሁለት ሺሕና በሦስት ሺሕ ቢጨምር ይህ ለዩክሬን ሥጋት አይደለም፡፡ ዩክሬንም ጉዳዩን ትከታተለዋለች፤›› ብለዋል፡፡
ዳኒሎቭ እንደሚሉት፣ አምና ቤላሩስ ወታደራዊ ልምምድ አድርጋ ነበር፡፡ ‹‹ይህንንም ዩክሬን ታውቃለች፡፡ እንዴት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነና ምን ሊሆን እንደሚችል ትገነዘባለች፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ውጥረቱ በዩክሬን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አለ የሚሉት ዳኒሎቭ፣ ‹‹ውጥረቱ በአሜሪካ አለ፡፡ አሜሪካና ሩሲያ ለየራሳቸው ባስቀመጡት መሥፈርት ውጥረት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በአውሮፓም ውጥረት አለ፡፡ አውሮፓ ዴሞክራሲን በማስፈን አቅሙ ላይ ውጥረት ውስጥ ገብቷል፤›› ብለዋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮልዲሜር ዜሌንስኪ በተገኙበት የተካሄደው የምክር ቤቱ ውይይት የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት ከውጭም ከውስጥም በመጠበቅ በኢኮኖሚ፣ በኢነርጂና በኮሮና ቫይረስ መከላከል ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
ኒውዴልሂ ቲቪ (ኤንዲቲቪ) በድረ ገጹ እንዳሠፈረው ደግሞ፣ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዜሊንስኪ ‹‹ምናልባት ሩሲያ ዩክሬንን ብትወር›› በሚል የአውሮፓ ኅብረት እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሜሪካ፣ እንግሊዝና የባልቲክ አባል አገሮች የዩክሬንን ጥሪ ተቀብለው ፀረ ታንክ፣ ፀረ ሚሳኤልና ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶች ለመላክ ሲስማሙ፣ ጀርመን ወታደራዊ ቁሳቁስ እንደማትልክ አስታውቃለች፡፡
ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬን የሩሲያ ደጋፊ የሆኑ በምሥራቅ የዩክሬን ክፍል የሚገኙ ነዋሪዎችን ለመውጋት እየተዘጋጀች ነው ስትል ወንጅላለች፡፡ የዩክሬን ወታደሮች እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ ከሞስኮ ደጋፊዎች ጋር እየተዋጉ ሲሆን፣ አሁን እየተደረገ ያለው ዝግጅት ከፍተኛና ከዚህ በፊት ከነበረው የበለጠ ነው ሲሉ የሩሲያ (ክሪምሊን) ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ተናግረዋል፡፡