Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነውን የብሔራዊ ምርመራ ሊያካሂድ ነው

  የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነውን የብሔራዊ ምርመራ ሊያካሂድ ነው

  ቀን:

  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ዙሪያ በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነውን የብሔራዊ ምርመራ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ፡፡

  ይህ ብሔራዊ ምርመራ በብዙ አገሮች የተለመደና በተግባር ላይ የዋለ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ለረዥም ጊዜ መፍትሔ ያላገኙ፣ ውስብስብና ሥልታዊ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ላይ የሚያተኩር መሆኑ ተገልጿል፡፡

  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የካቲት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሦስት ዓመት ሚቆየውን ብሔራዊ ምርመራ በሚመለከት ከክልል ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በፕሮጀክቱ ማስጀመርያ ላይ ገለጻ የሰጡት ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ራኬብ መሰለ እንዳስረዱት፣ ብሔራዊ ምርመራው ከዚህ ቀደም ሲደረግ ከነበረው ምርመራ አድርጎ ሪፖርት የማቅረብ ሥራ የሚለይና ብዙ ሰዎችን የሚመለከት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን በተመለከተ ተግባር ላይ የሚውል ነው፡፡

  ከዚህም በተጨማሪ የምርመራ ሪፖርት በሚዘጋጅበት ጊዜ እንደሚደረገው ተጠቂና ባለድርሻ አካላትን ለየብቻ ከማናገር በተለየ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአንድ መድረክ ውስጥ ቀርበው የሚነጋገሩበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ወ/ሮ ራኬብ ገልጸዋል፡፡

  ይኼንን ዓይነቱን የብሔራዊ ምርመራ ማካሄድ ሰፊ ጊዜና በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ በሁሉም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ላይ መተግበር አስቸጋሪ እንደሚሆን ያነሱት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፣ በዚህ ፕሮጀክት ትኩረት የተሰጠው ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

  ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች የሚለው ሐሳብ በተለያዩ ጉዳዮች በፖሊስ ጣቢያ ያሉ፣ በማረሚያ ቤት የሚገኙ፣ ወይም ሰዎች ሊታገቱ የሚችሉባቸው ቦታዎች ላይ የሚገኙ ሰዎችን እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡ አገራዊ ምርመራው እነዚህ ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ባሉበት ቦታ በሚያጋጥሟቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን እንደሚመለከት አብራርተዋል፡፡

  ‹‹ይኼ ፕሮጀክት ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ያተኮረው ከቀደመው ሥርዓት ጀምሮ ያልተፈቱ ጉዳዮች ስላሉ ነው፤›› በማለት የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ያስረዱት ወ/ሮ ራኬብ በውስጡ ብዛት ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚይዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

  ወ/ሮ ራኬብ፣ ግለሰቦቹ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ በእስርና በፍርድ ቤት ውስጥ ችግር እንደሚያጋጥማቸው አንስተው፣ በሕጉ ባስቀመጠው ጊዜ ፍርድ ቤት ያለመቅረብና በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች መታሰርን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡

  አንዳንዱ እንደዚህ ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጸመው ሕግ ስለተጣሰ ሳይሆን፣ ሕጉ በራሱ ያስከተለው ሊሆን እንደሚችል በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡ የሕፃናት ታሳሪዎች ጉዳይ ከእነዚህ መካከል አንዱ ሲሆን፣ ከዘጠኝ ዓመት ጀምሮ ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት እስር ቤት ውስጥ የሚያጋጥማቸው ሁኔታ የወደፊት ሕይወታቸውን ሊያበላሽ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ለዚህም ሲባል ሕፃናቱን ከእስር ቤት ይልቅ የሕፃናት ማገገሚያ ማዕከል ውስጥ ማስገባት የተሻለ አማራጭ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

  ከልጆቻቸው ጋር የሚታሰሩ እናቶችንም በተመለከተም ከፍተኛ የሆነ ወንጀል እስካልፈጸሙ ድረስ፣ እናቶችን ከእስር ቤት ማስወጣት ለልጆቹ ጤንነትና የወደፊት ሕይወት እንደሚበጅ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አስረድተዋል፡፡

  አገራዊ ምርመራው እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ በሚያዘጋጃቸው መድረኮች አማካይነት ባለመብቶችና ባለድርሻ አካላት ፊት ለፊት ተገናኝተው ውይይቶችን የሚያደርጉ ሲሆን፣ ይኼም የችግሩን ጥልቀት ለመረዳትና መፍትሔ ለማምጣት እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡

  የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኑ ለሦስት ዓመታት የሚቆየውን ይኼንን ፕሮጀክት የሚተገብረው በ15 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ሲሆን፣ ድጋፉን ያገኘው ከአውሮፓ ኅብረት መሆኑ ታውቋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...