Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአኅጉራዊ የንግድ ትስስሮች ለሚቀርቡ ምርቶች የጥራት ፖሊሲ ረቂቅ ተዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገሮች መካከል ተመጋጋቢ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር በሚል ወደ ሥራ በገባው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አማራጭ ላይ፣ ኢትዮጵያ የምታቀርባቸው ምርቶች፣ ዓለም አቀፋዊ የጥራት ደረጃን ያረጋገጡ እንዲሆኑ የሚያስችል ብሔራዊ የጥራት ፖሊሲ ረቂቅ እያዘጋጀች እንደሆነ ተገለጸ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ረቂቅ ፖሊሲው ከመፅደቁ በፊት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ በረቂቅ ሰነዱ ላይ የመጨረሻ የሆነ አስተያየታቸውን የሚያቀርቡበት ዓውደ ጥናት፣ የካቲት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል አዘጋጅቷል፡፡

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የብሔራዊ ጥራት መሠረተ ልማትና ማረጋገጥ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አቶ እንዳለው መኰንን፣ አገሪቱ ከዚህ ቀደም የጥራት ስትራቴጂ እንጂ አገራዊ ፖሊሲ አልነበራትም ብለዋል፡፡ የነበረው ስትራቴጂ ተቋማትን ሪፎርም ተሠርቶ እንዲቋቋሙ ከማድረግ የዘለለ ሚና አልነበረውም ብለው፣ በፖሊሲ ደረጃ እንዲዘጋጅ የተደረገው ሰነድ ከፍ ያለ የመንግሥት ቁርጠኝነት የታየበት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በአገር ውስጥ ተመርተው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡና ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ላይ የጥራት ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል ያሉት አቶ እንዳለው፣ እነዚህ ችግሮች ምላሽ የሚያገኙበት ዘዴ ቢኖር የጥራት ፖሊሲ ሰነድ ነው ብለዋል፡፡

ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና በርካታ ባለሀብቶች እንዲመጡ ጥራትን በተመለከተ የሚከናወኑ ሥራዎች ወሳኝ ናቸው ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ በተለይም ከውጭ የሚመጡ ባለሀብቶች የሚጠይቁት የመጀመሪያው ጥያቄ ከጥራት መቆጣጠሪያ አኳያ ያለው ፖሊሲ ምንድነው የሚለውን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት የጥራት ደረጃዎችን የሚያረጋግጥበት ፖሊሲ እንደሚያስፈልገው፣ የጥራት ፖሊሲው የሚያቋቁማቸው ተቋማት እንደሚኖሩና በተጨማሪም በቀጣይ የሚወጡ ስትራቴጂዎችም ይኖሩታል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ደረጃ የፓን አፍሪካ ኳሊቲ ኢንፍራስትራክቸር ፖሊሲ ተዘጋጅቷል ያሉት አቶ እንዳለው፣ በመስከረም ወር በአፍሪካ ሚኒስትሮች ደረጃ ስምምነት የተደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በተከናወነው 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ጉባዔ ላይ እንደ አጀንዳ ይቀርባል ተብሎ በአጀንዳ መጣባብ ምክንያት ሳይፀድቅ መቅረቱን አስታውቀዋል፡፡

የአፍሪካ ጥራት ፖሊሲ በሚኒስትሮች ጉባዔ ስምምነት ተደርሶበት ተዘጋጅቶ እንደተጠናቀቀ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም ከተካተቱት ጉዳዮች ውስጥ አገሮች በቀጣና ደረጃ የአፍሪካ የጥራት ፖሊሲ እንደሚኖራቸው፣ እንዲሁም አባል አገሮች ደግሞ የራሳቸው የጥራት ማረጋገጫ ፖሊሲ እንዲኖራቸው የሚጠይቅ ወይም የሚያስገድድ ነው ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ አባል አገር የራሷ የጥራት ፖሊሲ በቅርቡ እንደምታፀድቅ ተገልጾ፣ ይህም በቀጣናው ላይ ሊኖራት የሚችላትን አስተዋፅኦ ሊያሳይ በሚችል መንገድ የተቀረፀ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተብሎ ሲደራጅ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አኅጉር ነፃ የንግድና ቀጣና ላይ ምን ዓይነት ምርት ይዛ ነው መግባት የምትችለው የሚለውን ታሳቢ ያደረገ ነው ያሉት አቶ እንዳለው፣ ጥራት በሌለው ምርት የተፈለገውን የገበያ መዳረሻ ማፈላለግና ማግኘት ስለማይቻል የጥራት ፖሊሲው ይህንን ለመመለስ ያስችላል ብለዋል፡፡

የፖሊሲው መዘጋጀት የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማስተካከል የሚያስችል እንደሆነ የተገነገረ ሲሆን፣ በተጨማሪም የአገር ውስጥ አምራቾች ግዴታና ኃላፊነታቸው ምን እንደሆነ በግልጽ ለማስቀመጥ ፖሊሲው አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ ክፍተቶችንም ፖሊሲው የሚዘጋ እንደሆነ ያስረዱት ሚኒስትር ደኤታው፣ በቀጣይ ይህንን ለማስፈጸም የሚረዱ የማስተግበሪያ ሰነዶች፣ በተጨማሪም ለአፈጻጸም የሚረዱ ተቋማትም የሚቋቋሙ ይሆናል፡፡

‹‹በአገር ውስጥ ኢኮኖሚው በሚፈልገው ደረጃ የተደራጀ ላብራቶሪ የለንም፤›› ያሉት አቶ እንዳለው፣ ‹‹ያንን ሊመልስ የሚችል እንደ አዲስ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችል፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ላብራቶሪ ማቋቋም ይጠይቅ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ መንግሥት ጉዳዩን ለማስተካከል ሪፎርም ሲሠራ ነበር፡፡ ከፍተኛ ሀብት ተመድቦ የላብራቶሪና የቢሮ ግንባታዎች እየተገነባ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ እንዳለው እንዳስታወቁት፣ በቀጣይ ዓለም አቀፍ ይዘትና ደረጃ ያለው የፍተሻ ላብራቶሪ ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ያንን ለማድረግ ከዓለም ባንክ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት ተመድቦ የላብራቶሪ ዕቃዎች እየተገዙ ናቸው፡፡ ብቃት ያላቸው የሰው ሀብት ባለሙያዎች የማደራጀት ሥራ እየተሠራ መሆኑን፣ መሠረተ ልማቱ ከተገነባና የሰው ኃይል ከተደራጀ፣ ጊዜው የሚጠይቀውን የላብራቶሪ ዕቃዎች አደራጅቶ ወደ ሥራ በመግባት ከሌሎች አገሮች የሚስተካከል፣ ኢኮኖሚው የሚጠይቀውን፣ የኢትዮጵያ ማምረቻ ተቋማት የሚጠይቁትን ዓይነት ምላሾችን የሚሰጥ ቁመና ላይ መድረስ ይቻላል፡፡

ረቂቅ ፖሊሲው የመጨረሻውን የማጠቃለያ መድረክ ካከናወነ በኋላ ግብዓቶቹ በአጭር ጊዜ ተጠናቅረው ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ተመርቶ፣ በተያዘው ዓመት እንዲፀድቅ ጥረት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች