Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የጦርነት ኢኮኖሚ መዘዙ የከፋ ነው!

  ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ጦርነት ውስጥ መቆየት እንደማይቻል የደቀቀው ኢኮኖሚ በሚገባ እየተናገረ ነው፡፡ መደበኛው በጀት አልበቃ ብሎ በተጨማሪ ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ ኢኮኖሚው ውስጥ ሲገባ፣ በየቀኑ እያሻቀበ ያለው የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎችና የሌሎች ምርቶች የዋጋ ግሽበት ከሕዝቡ አቅም በላይ ሲሆን፣ የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ አቅም በየቀኑ ሲመናመን፣ በዓመት ከወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ማደግ ተስኖት፣ የገቢ ንግድ ግን ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ አሻቅቦ የንግድ ሚዛኑ ሲዛባና የውጭ ብድርና ድጋፍ ሲነጥፍ የኢኮኖሚው ጉዳይ ያሳስባል፡፡ የጦርነት ኢኮኖሚ በሁሉም አቅጣጫ ወጪ እንጂ ገቢ ስለሌለው፣ እንኳንስ ከድህነት የሚያወጣ ልማት ለማቀድ በልቶ ማደር ከባድ ይሆናል፡፡ ጦርነት ማለት ለልማት የሚውል ገንዘብን እሳት ውስጥ መክተት በመሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ በድርብ አኃዝ የዋጋ ግሽበት ምክንያት ሕዝቡ በኑሮ ውድነት ቁምስቅሉን እያየ ነው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም የሚያስፈልገው ሀብት በራሱ ከአገር አቅም በላይ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ በአሜሪካ የተረቀቀው የማዕቀብ ሕግ፣ የዓለም ባንክንና የአይኤምኤፍን ብድርና ድጋፍ ጭምር ለማስከልከል አድፍጧል፡፡

  በቅርቡ የተደረገው ከበድ ያለ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከሌሎች ጭማሪዎች ጋር ተዳምሮ፣ መጪውን ጊዜ አስፈሪ አድርጎታል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት አምራች ኢንዱስትሪው ከአቅሙ በታች ለማምረትመገደዱ፣ በጦርነቱና በድርቁ ሳቢያ የተረጂዎች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይመጨመሩ፣ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ኢኮኖሚው በመዳከሙ የዓለም አቀፍ ንግድመቀዛቀዙና ከኤክስፖርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በተከታታይ ዓመታት ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ከውጭ የሚገኘው ዕርዳታና ብድር በመቀነሱ ሳቢያ ኢኮኖሚው በጣም ተጎድቷል፡፡ የፖለቲካ  ትኩሳት  ውጤት የሆነው የጦርነት  ኢኮኖሚ  ችግር  በጊዜ  መላ  ካልተፈለገለት፣ የቀውሶች  ሁሉ  እናት  ሊሆን  ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ የጦርነት ኢኮኖሚ ለመምራት የሚያስችል አቅም የላትም፡፡ በግብርና ላይ ጥገኛ የሆነው ኢኮኖሚ የተለያዩ ዘርፎቹ ተንቀሳቅሰው ውጤት ማግኘት የሚቻለው፣ አውዳሚ ከሆነው ጦርነት ውስጥ በፍጥነት በመውጣት ነው፡፡ የአገሪቱን ውስን ሀብት እሳት ውስጥ የመክተት ውጤቱ ኪሳራና ውድመት ነው፡፡ ሕዝቡን እንደ ሰደድ እሳት ከሚጋረፈው የኑሮ ውድነት ማስጣል የሚቻለው፣ ጦርነቱን በፍጥነት በማቆም ወደ ልማት በመሰማራት ብቻ ነው፡፡ ጦርነት ውስጥ ተገብቶ ልማትም ሆነ ዕድገት አይታሰብም፡፡ የልማት አጋር በመባል የሚታወቁትም ቢሆኑ ጀርባቸውን ይሰጣሉ እንጂ ዕገዛ ስለማያደርጉ፣ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ችጋር ይከሰታል፡፡  

  ጦርነቱን ከማስቆም ጎን ለጎን ቢሮክራሲው ውስጥ የተሰገሰገውን የሌባ ሠራዊት ማስወገድ ይገባል፡፡ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምር በመሬት ወረራ፣ በጉቦና በምልጃ፣ ከቀረጥ ነፃ ዕድል በመጠቀም፣ የመንግሥት በጀትና ንብረት በመዝረፍና በመሳሰሉት ኢሞራላዊ ድርጊቶች የተተበተበው ኃይል አደብ መግዛት ይኖርበታል፡፡ ለዕርዳታና ለመልሶ ማቋቋም ከተሰባሰበ ንብረትና ገንዘብ ዘረፋ ጀምሮ፣ በተለያዩ የስርቆት ድርጊቶች ህሊናው የተበላሸ ኃይል፣ ከመንግሥትና ከገዥው ፓርቲ መዋቅር ውስጥ መፅዳት አለበት፡፡ የጦርነት ኢኮኖሚ በግዥና በሥርጭት ወቅት ከፍተኛ ዝርፊያ ስለሚፈጸምበት፣ የዝርፊያ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ጦርነቱ እንዲቆም አይፈልጉም፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ግዙፍ የውድመት ፕሮጀክት በመሆኑ፣ የዝርፊያ ተቀራማቾች ጦርነቱ እንዳይቆም የፕሮፓጋንዳ ሠራዊታቸውን በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ያሰማራሉ፡፡ ሕዝብ የሚበላው እየቸገረውና ደኅንነቱ ዋስትና እያጣ እነሱ ሙሉ ትኩረታቸው ዝርፊያ ላይ ስለሆነ፣ ስለሚፈሰው የንፁኃን ደምም ሆነ ስለሚወድመው የአገር ሀብት ደንታ የላቸውም፡፡ የጦርነት ኢኮኖሚ ጥቂቶችን እያበለፀገ ብዙኃኑን የሚያደቅና ለጠኔ የሚዳርግ በመሆኑ፣ ጦርነቱ በፍጥነት አጠናቆ ሰላም ማስፈን የግድ ነው፡፡

  ኢትዮጵያ  ቁጥሩ  ከፍተኛ  የሆነ  ወጣት  የሰው  ኃይል፣  ለግብርና  አመቺ  የሆነ  መጠነ  ሰፊ  ለም  መሬት፣  በአፍሪካ  አንደኛ  የሆነ  የእንስሳት  ሀብት፣  ክረምት ከበጋ  የማይነጥፍ  ትልቅ  የውኃ  ምንጭ፣  ለግብርና  አመቺ  የሆኑ  የተለያዩ  የአየር  ፀባዮች፣  የቱሪዝም  መስህቦችና  የተለያዩ  ማዕድናት  ባለቤት  ናት፡፡ በጦረኝነት አባዜ  ታላቅ  የተፈጥሮ  ፀጋ  ታቅፎ  መደህየት  ነውር  ነው፡፡  መሠረታዊ  የመዋቅር  ለውጥ  የአገሪቱን  ወጣቶች፣  ምሁራንና  ባለሙያዎችን በማንቀሳቀስ  ከዘመናት  ድህነት ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡  ኢትዮጵያ የሰላም ረሃብተኛ፣ የድህነትና  የልመና  ተምሳሌት  መሆን  የለባትም፡፡  እጅግ አስመራሪ የሆነ ድህነት ውስጥ እየኖሩ በማያባራ ጦርነት እርስ በርስ መፋጀት ማብቃት አለበት፡፡  አሁን  በሚታየው አደገኛ ሁኔታ  መዝለቅ  አይቻልም፡፡ ለማመን የሚያዳግት ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ተቀምጠው እየተዋጉ እጅን ለምፅዋት መዘርጋት አሳፋሪ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ምንም ሳይጎድልባት ዜጎቿ ምግብ ሲቸገሩ፣ መጠለያ ሲያጡና በጦርነት ምክንያት ሰላማቸው ተቃውሶ ሲገደሉና ሲፈናቀሉ ማየት አይገባም፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አስከፊ አረንቋ ውስጥ መውጣት የሚቻለው ጦርነትን በማስወገድ ብቻ ነው፡፡

  የኢኮኖሚው  ጉዳይ  ያሳስባል ሲባል  ሥራ  ከሌለ  ገቢ  የለም፣  ገቢ  ከሌለ  አማራጩ  ዝርፊያ  ውስጥ  መግባት  ይሆናል፡፡  ዘረፋ  የሥርዓተ  አልበኝነት  መገለጫ  ከመሆኑም  በላይ፣  ወደ  ቀውስ  የሚያንደረድር  አደገኛ ጎዳና ነው፡፡ ፖለቲከኞችም  ሆኑ  ሌሎች  የአገር  ጉዳይ  የሚመለከታቸው  ወገኖች  በሙሉ፣ የኢኮኖሚው  ሁኔታ  ትልቅ  ትኩረት  እንደሚያስፈልገው መገንዘብ  ይኖርባቸዋል፡፡  ወጣቱ  ሥራ  ያስፈልገዋል፡፡  ኢንቨስተሮች  የተረጋጋና  ሰላማዊ  ሁኔታ እንዲፈጠር  ይፈልጋሉ፡፡ አርሶ አደሩ ማምረት የሚችለው ሰላም ሲኖር ነው፡፡  የኑሮ  ውድነት  የሚረግበውና የተሻለ ሕይወት መምራት የሚቻለው ጦርነት ሲቆም ነው፡፡  የብዙዎች  ጉጉት ሰላም ሰፍኖ የተደላደለ ሕይወት መምራት ነው፡፡  ይህ  ሊሳካ  የሚችለው ግን  ጦርነቱን አስቁሞ  ኢኮኖሚውን ከገባበት ማጥ ውስጥ ማውጣት  ሲቻል  ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከፍተኛ መጠን ያለው ዕዳ  ውስጥ ከቶ  መፋጀት  ቀውሱን  ያባብሰዋል  እንጂ  መፍትሔ  አያመጣም፡፡  ይልቁንም  የሕግ የበላይነት  ተከብሮ  ለሁሉም  ኢትዮጵያውያን  የምትመች  አገር  ለመገንባት  ሰላም መስፈን አለበት፡፡  ከምንም  ነገር  በላይ  ቅድሚያ  ለሚሰጣቸው አገራዊ ጉዳዮች  በመጨነቅ፣  ኢትዮጵያ  ካለችበት  ኢኮኖሚያዊ ቀውስ  ውስጥ  እንድትወጣ  ርብርብ  ይደረግ፡፡  አገራቸውን  የሚወዱ  ኢትዮጵያውያን  በሙሉ  ወደ ውድቀት  የሚንደረደረውን ኢኮኖሚ  ለመታደግ  የሚያስችሉ  መላዎችን  ወዲህ  ይበሉ፡፡

  የዝናብ  ጥገኛ  የሆነው  የአገሪቱ  ግብርና  አሁንም  በጣም  ኋላቀር  ነው፡፡  ከውጭ  በከፍተኛ  የውጭ  ምንዛሪ  በሚገባ  ማዳበሪያ  ታግዞም  ምርታማነቱ አስተማማኝ  ስላልሆነ፣  በምግብ  ራስን  መቻል  ከባድ  ፈተና  ሆኗል፡፡  ስንዴ፣  ዘይት፣  ወተትና  ሌሎች  የምግብ  ሸቀጣ  ሸቀጦች  ከፍተኛ  የውጭ  ምንዛሪ እያስወጡ  ነው፡፡  ለነዳጅ  የሚወጣው  ወጪ  በጣም  ከፍተኛ  ነው፡፡  ከኤክስፖርት  የሚገኘው  ገቢ  ሊያድግ አልቻለም፡፡  ከቀጥተኛ  የውጭ  ኢንቨስትመንት የሚገኘው  ገቢም  መጠኑ  እየቀነሰ  ነው፡፡  ሥራ  አጥነት  በከፍተኛ  መጠን  እየጨመረ  ነው፡፡  ብዙዎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከመቀዛቀዛቸውም በላይ፣ አብዛኞቹ ፋብሪካዎች የሚያመርቱት ከአቅማቸው ከግማሽ በታች ነው፡፡  የኢኮኖሚው  ችግር  ለወንጀል  መበራከት  መንስዔም  እየሆነ  ነው፡፡  የመሠረታዊ ምግብ  ሸቀጦች፣ የቤት  ኪራይ፣  የትምህርት  ቤትና  ሌሎች  ወጪዎች  ከአቅም  በላይ  እየሆኑ  ነው፡፡ ጦርነቱ በፍጥነት አብቅቶ ለኢኮኖሚው  ከፍተኛ  ትኩረት  ካልተሰጠ፣ አገሪቱን የማትወጣበት ቀውስ  ውስጥ  ይከታታል፡፡  መንግሥትም  ሆነ  ፖለቲከኞች፣  እንዲሁም  የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ  ለኢኮኖሚው ማገገም የሚረዱ ጠቃሚ ሐሳቦችን  ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡  የጦርነት ኢኮኖሚ  መዘዙ  የከፋ ስለሆነ ከፍተኛ ርብርብ ያስፈልጋል!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...

  የጉድለታችን ብዛቱ!

  ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...