Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው ግብረ ኃይል በአማራና አፋር ክልሎች የምርመራ ቡድኖች ሊልክ ነው

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው ግብረ ኃይል በአማራና አፋር ክልሎች የምርመራ ቡድኖች ሊልክ ነው

ቀን:

ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሁለቱ ክልሎች ምርመራውን በቅርቡ ይፋ ያደርጋል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በትግራይ ክልል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን አስመልክቶ ያወጡትን ሪፖርት ተከትሎ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል በአፋር፣ በአማራና አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው የምዕራብ ትግራይ ክልል አካባቢዎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን የሚመረምሩ ቡድኖችን ሊልክ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል በመጀመርያ የተቋቋመው በትግራይ ክልል በተደረገው ጥምር ምርመራ ላይ የተቀመጡ ምክረ ሐሳቦችን ተቀብሎ ምርመራ ለማድረግና ክስ ለመመሥረት ቢሆንም፣ ጦርነቱ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች በመስፋፋቱ ግብረ ኃይሉ ከምርመራ ሪፖርቱ ወሰን ውጪ ምርመራ ሊያደርግ መሆኑን ገልጿል፡፡ 

የግብረ ኃይሉ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታደሰ ካሳ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከተለያዩ ሙያዎች የተወጣጡ ባለሙያዎችን የያዙ ዘጠኝ ቡድኖች፣ ሰፋፊ ጥሰቶች በተካሄዱባቸው ዘጠኝ ዋና ዋና ቦታዎች ምርመራ ለማድረግ በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ይጓዛሉ፡፡

ግብረ ኃይሉ ተመሥርቶ ሥራ ከጀመረ በኋላ አራት ኮሚቴዎችን በሥሩ ማቋቋሙን ያስረዱት ታደሰ (ዶ/ር)፣ የመጀመርያው ኮሚቴ ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጣና የመከላከያና ፍትሕ ሚኒስቴሮች በበላይነት የሚመሩት የምርመራና የክስ ኮሚቴ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ እንዲሁም የክልል ፖሊስና የፍትሕ ቢሮዎች ተሳታፊ እንደሆኑበት ታውቋል፡፡

የፆታዊ ጥቃቶች ኮሚቴ፣ የስደተኞችና የአገር ውስጥ ተፈናቃች ኮሚቴ፣ እንዲሁም የሀብት ማሰባሰብ ኮሚቴ መቋቋማቸው ታውቋል፡፡ አራቱም ኮሚቴዎች የተቋቋሙበት መሠረት ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት፣ በትግራይ ያደረጉት የጥምር ምርመራ ውጤት፣ ድምዳሜዎች፣ እንዲሁም በሁለቱም ጥምር አካላት ተሰጡት ምክረ ሐሳቦች መሆናቸውን ታደሰ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሲስተካከል ግብረ ኃይሉ ወደ ክልሉ ሄዶ ምርመራ የሚያደርግበት ሁኔታ እንደተጠበቀ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው፣ የምርመራና ክስ ኮሚቴው በአማራና በአፋር ክልሎች ምርመራ ለማድረግ ተጨማሪ ሥልጣን እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡ 
በዚሁም መሠረት ኮሚቴው ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልል ፖሊስ ኮሚሽንና ከፍትሕ ቢሮዎች፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተወጣጡ 150 ገደማ ባለሙያዎች እንደሚላኩ ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጉዳዩ በቀጥታ ባይመለከተውም፣ ፆታዊ ጥቃት ምርመራ ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች ስላሉት መካተቱን ታደሰ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

የምርመራ ቡድኖቹ ምርመራውን የሚያካሂዱት በጥምር ሪፖርቱ ላይ በተቀመጠው ምክረ ሐሳብ መሠረት መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፣ 40 የምርመራ ቡድን አመራሮች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን እንዲሁም ዓለም አቀፍ የወንጀል ምርመራ ቴክኒኮች ትግበራና ሒደትን የተመለከተ ጥልቅ ሥልጠና ከሚቀጥለው ሳምንት አንስቶ ለአራት ቀናት እንደሚወስዱ ታውቋል፡፡ ሥልጠናው የሚሰጠው በተመድ የአደንዛዥ ዕፆችና ወንጀል ቢሮ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነርና በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ነው፡፡

ታደሰ (ዶ/ር) እነዚህ አካላት ሥልጠና ስለሚሰጥባቸው ጉዳዮች ከፍተኛ የሆነ የሥልጠናና የተግባር ልምድ እንዳላቸው ገልጸው፣ ሥልጠናውን የሚሰጡትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያዘጋጇቸው የሥልጠና ማንዋሎችን ተከትለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሥልጠናውን የወሰዱ የቡድን አመራሮችም ለአባሎቻቸው ገለጻ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

ታደሰ (ዶ/ር) ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ ሊጠፉ የሚችሉ አካላዊ መረጃዎችን የማሰባሰብና በቪድዮ የማስቀረት ሥራ ሲሠራ መቆየቱን፣ ነገር ግን መደበኛ ምርመራው የሚደረገው ቡድኖቹ ወደ ሥፍራዎቹ ካመሩ በኋላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የምርመራ ቡድኖቹ የሚሄዱባቸው ዘጠኝ አካባቢዎች ላይ እንዲሠፍሩ የሚደረግ ቢሆንም፣ ጥናታቸው በሠፈሩበት አካባቢ ዙሪያ የሚገኙ ቦታዎችንም እንደሚያካትት ገልጸዋል፡፡

እነዚህ የምርመራ ቡድኖች የሚልከው የምርመራና የክስ ኮሚቴ ክስ የመመሥረት ኃላፊነትም እንዳለው ያስረዱት ኃላፊው፣ የምርመራ ቡድኖቹ የሚያገኙት ውጤት ላይ ተመሥርቶ ክስ የመመሥረት ሒደት እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት እስከ ሰኔ መጨረሻ 2013 ዓ.ም. ድረስ በትግራይ ክልል ያደረጉት የምርመራው ውጤት ይፋ የሆነው፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በትግራይ ክልል በተጀመረ በዓመቱ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም.  ነበር፡፡

የምርመራው ውጤት በትግራዩ ጦርነት የተሳተፉ አካላት በሙሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መፈጸማቸውን አረጋግጦ፣ ጥሰቶቹ በርካታ የዓለም አቀፍ የጦርነትና የሰብዓዊ መብቶች ሕጎችን የሚተላለፉ፣ እንዲሁም አገሪቱ ያፀደቀቻቸውና የተቀበለቻቸውን የሰብዓዊ መብት ሕጎችን የሚጥሱ ጥፋቶች መሆናቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሪፖርቱ ይፋ በሆነበት ዕለት በፌስቡክ ገጻቸው ባወጡት መግለጫ፣ ሪፖርቱ ከሞላ ጎደል  የተጨበጡ ማስረጃዎችን ይዞ መምጣቱን ገልጸው፣ ምክረ ሐሳቦቹን ተግባራዊ የሚያደርግ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል እንደሚቋቋም ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡ 

የጥምር ምርመራው አንዱ አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ከተደረገው ምርመራ በኋላ በተናጠል በአፋርና አማራ ክልሎች ምርመራ እያደረገ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የዚህ ጥናት የሚያስፈልጉ መረጃዎች ተሰብስበውና ተተንትነው መጠናቀቁን ለሪፖርተር የተናገሩት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወ/ሮ ራኬብ መሰለ፣ ሪፖርቱን የማጠናቀር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ወ/ሮ ራኬብ በአማራና አፋር ክልል የተደረገው ምርመራ በሚፈለገው መጠን ሁሉንም ቦታዎች ማዳረስ አለመቻሉን ገልጸው፣ ከዚህ በላይ ሪፖርቱን ሳያወጡ መቆየት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

‹‹ሪፖርቱን የሚጠብቁት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ውጭ ያሉ አካላትም ስለሆኑ የትርጉም ሥራው ትንሽ ሊያቆይብን ይችላል፤›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ፣ በሁለት ወይም በሦስት ሳምንት ውስጥ ሙሉ ሪፖርቱ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...