Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከተማ አስተዳደሩ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንፃ መገንቢያ የሰጠውን ቦታ መልሶ ሊወስድበት ነው

ከተማ አስተዳደሩ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንፃ መገንቢያ የሰጠውን ቦታ መልሶ ሊወስድበት ነው

ቀን:

‹‹የፌዴራል ተቋምን በማፍረስ የአስተዳደርን ተቋም ማጠናከር አይኖርም››

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት

ፓርላማው በጀት ባለመመደቡ ግንባታ መጀመር አልተቻለም

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዲስ ለሚገነባው ሕንፃ የተሰጠውን 2.1 ሔክታር መሬት፣ ለራሱ ሊገነባቸው እየተዘጋጀ ላለበት የቢሮዎች ግንባታ ፕሮጀክት ሊወስደው መሆኑ ተገለጸ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በልደታ ክፍለ ከተማ ተክለ ሃይማኖት አካባቢ የሚገኘውን መሬት ከከተማ አስተዳደሩ ተረከበው በ2011 ዓ.ም. ሲሆን፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታም ተቀብሏል፡፡ ይሁንና የአዲስ አባባ ከተማ ሜጋ ፕሮጀክቶች ቢሮ ቦታው በኪራይ ላሉ የከተማ አስተዳደሩ ቢሮዎች ሕንፃ ለመገንባት ጥያቄ ማቅረቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋሽ ባልቻ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሁን ያለበትንና ልደታ አካባቢ የሚገኘውን ከ50 ዓመት በፊት የተገነባ ሕንፃ በአዲስ የመተካት ዕቅድ ያለው ሲሆን ለዚህም የሚሆን የዲዛይን ሥራ አጠናቋል፡፡ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ መስቀል ዋጋሪ ለሪፖርተር እንደተናገሩት ከመሬቱ አቀማመጥ ጋር በተያያዘ የዲዛይን ሥራው የተሠራው ሁለት ጊዜ ነው፡፡

ሊገነባ የታሰበው ሕንፃ ዘጠኝ ወለሎች እንዲሁም ከምድር በታች ሦስት ወለሎች ይኖሩታል፡፡ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ኮርፖሬሽ አማካኝነት የተዘጋጀው የመጨረሻው የዲዛይን ሥራ የተጠናቀቀው በ2013 ዓ.ም. መሆኑ ታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዲዛይን ሥራን ለማጠናቀቅና የተሰጠውን ቦታ ለማጠር አሥር ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ ማድረጉን አቶ ብርሃነ መስቀል አክለዋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በልደታ የሚገኘው ሕንፃው አሁን ያለውን የተገልጋይ፣ የችሎትና የሠራተኛን ብዛት የሚያስተናግድ እንዳልሆነ ያስረዱት ፕሬዚዳንቱ ፍርድ ቤቱ በተለያዩ ሕንፃዎች ላይ ቢሮ መከራየቱንና ለዚህም በየዓመቱ 11 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ አዲሱ ሕንፃ በተበታተነ ቦታ የሚሰጡትን አገልግሎቶች በአንድ ቦታ ያደርጋል የሚል ሐሳብ እንዳለም አክለዋል፡፡

ይሁንና ፍርድ ቤቱ ቦታ ተረክቦ የሕንፃ ዲዛይን ቢያሰራም በጀት ባለመፈቀዱ ምክንያት ግንባታው ሊጀመር እንዳልቻለ አቶ ብርሃነ መስቀል ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ተያይዞ ገንዘብ ሚኒስቴር ግንባታው እንዲዘገይ መጠየቁን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ በዚህ ዓመት እስከ ጥር ወር ድረስ ግንባታው እንዲጀመር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ አለመሰጠቱን አስረድተዋል፡፡

አቶ ብርሃነ መስቀል ፍርድ ቤቱ የልደታውን ሕንፃ የማደስ ሐሳብ እንደነበረው ተናግረው አዲስ ሕንፃ ሊገነባ እየተዘጋጀ ባለበት ሁኔታ እድሳት ማድረጉ ‹‹ተደራራቢ ወጪ ይሆናል›› የሚል ሐሳብ በመነሳቱ የማደስ ሐሳቡም እንደቀረ አብራርተዋል፡፡

ይሁንና ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በቢሊዮን ብሮች ወጪ አድርጎ በሜጋ ፕሮጀክትነት አዲስ ሕንፃ እገነባበታለሁ ብሎ የተቀበለው መሬት ለሌላ የቢሮዎች ግንባታ ሜጋ ፕሮጀክትነት ታጭቷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋሽ እንደተናገሩት የአዲስ አባባ ከተማ ሜጋ ፕሮጀክቶች ቢሮ መሬቱ ላይ ቢሮዎችን ለመገንባት ጥያቄ በማቅረቡ ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጋር ንግግር ይደረጋል፡፡

የከተማዋ ሜጋ ፕሮጀክቶች ቢሮ ሊያካሂድ ያሰበው ብዛት ያላቸው የከተማ አስተዳደሩን ሕንፃዎች በአንድ ላይ ሰብስቦ የሚይዝ የግንባታ ፕሮጀክት ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ካሉት 46 ተቋማት መካከል የራሳቸው መገልገያ ቢሮ ያላቸው 14 ያህሉ ብቻ ሲሆኑ፣ የከተማ አስተዳደሩ በአጠቃላይ ለ569 ተቋማት ቢሮ ኪራይ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚያደርግ ባሳለፈው ሳምንት በተደረገው የከተማዋ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ተገልጾ ነበር፡፡

ይሄንን ወጪ ለመቅረፍ ያስችላል የተባለለትና ሁሉንም ቢሮዎች በአንድ ላይ የሚያደርግ የግንባታ ፕሮጀክት ለማስጀመር መታሰቡን በጉባዔው ላይ የተናገሩት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ትልቅ ፕሮጀክት እንደሚሆንና ስድስት ዓመት ሊፈጅ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

ይሄ ፕሮጀክት ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ለሕንፃ ግንባታ ተብሎ የተሰጠው ቦታን እንደሚመለከት ያስረዱት አቶ ነጋሽ፣ ተመሳሳይ ዓይነት ስፋትና ደረጃ ያለው ሌላ ምትክ ቦታ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና ምትክ ቦታ የመስጠቱ ጉዳይ ‹‹ከእነሱ ጋር በመግባባትና በመስማማት ነው የሚሠራው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ቢሮው መሬቱ ላይ ጥያቄ ሲያቀርብ ቦታው ቀድሞ ለፍርድ ቤቱ እንደተሰጠ አይታወቅም ነበር?›› የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ምክትል ቢሮ ኃላፊው የቦታ መረጣ የሚያካሄደው በከተማዋ ሜጋ ፕሮጀክቶች ቢሮ መሆኑን ተናግረው ‹‹የእኛ ሥራ መሬት ማቅረብ ብቻ ነው›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለዚህ ሜጋ ፕሮጀክት ዲዛይንና ግንባታ የሚያካሂድ ተቋራጭ ለመምረጥ የጨረታ ሒደት ላይ መሆኑን ለሪፖርተር የተናገሩት የከተማዋ ሜጋ ፕሮጀክቶች ቢሮ ኃላፊ ደቦ ቱንጋ (ኢንጅነር)፣ የግንባታ ሳይቶች የአዋጪነት ጥናትም እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠውን ቦታ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም የቦታዎችን ተገቢነት ማየት እንደሚቻል ገልጸው፣ ጉዳዩን የጥናቱ ውጤት የሚወስነው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አክለውም ‹‹ሕጋዊ ሒደቱን ተከትሎ ሁሉም ነገር ሊፈጸም ይችላል›› ካሉ በኋላ ‹‹ሁለቱም የመንግሥት አካላት ስለሆኑ አንዱ አንዱን የሚገፋበት ጉዳይ አይደለም›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በመሬቱ ላይ ዲዛይን አሠርቶ ያጠናቀቀው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ መስቀል፣ የከተማ አስተዳደሩ ለፍርድ ቤቱ የተሰጠው ቦታ ላይ ሕንፃ ለመሥራት እንደሚያስብ መስማታቸውን በመግለጽ፣ ‹‹አንድ የፌዴራል ተቋምን በማፍረስ ወይም እንዳይጠናከር በማድረግ አንድ የከተማ አስተዳደር ተቋምን ማጠናከር አይኖርም›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ የበጀቱ ጉዳይ እልባት አግኝቶ የ2014 በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ግንባታ ይጀመራል የሚል ተስፋቸውንም ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...