Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለኮስታሪካ የዓለም ዋንጫ 180 ደቂቃዎችን የሚጠብቁት የሉሲዎቹ ተተኪዎች

ለኮስታሪካ የዓለም ዋንጫ 180 ደቂቃዎችን የሚጠብቁት የሉሲዎቹ ተተኪዎች

ቀን:

ኮስታሪካ ለምታስተናግደው ዕድሜያቸው ከሃያ ዓመት በታች የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ አገሮች በየአኅጉሮቹ ሲያከናውኑት የቆየው የማጣሪያ መርሐ ግብር ፍጻሜውን ሊያገኝ ከጫፍ ደርሷል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ በማጣሪያው እየተሳተፈች የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ለመጨረሻው ደርሶ መልስ የማጣሪያ ጨዋታ ከበቁት ዝርዝር ተካታለች፡፡ ተጋጣሚዋም ምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና መሆኗ ታውቋል፡፡ ኮቪድ-19 ከመከሰቱ በፊት ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመርያውን የማጣሪያ ጨዋታ ከቡሩንዲ አቻው ጋር አድርጎ በድምሩ 7 ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ ውድድሩ በኮቪድ ምክንያት ለወራት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ውድድሮች እንዲጀመሩ ተደርጓል፡፡ ዝግጅቱን በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል የጀመረው ቡድኑ ጨዋታውን ቀጥሎ ሩዋንዳን በደርሶ መልስ ጨዋታ 8 ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ ከማጣሪያው ጎን ለጎን በዑጋንዳ  የተካሄደውን የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ዋንጫ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በቅርቡ የታንዛኒያ አቻውን በደርሶ መልስ ውጤት 2 ለ1 ማሸነፍ የቻለው ቡድኑ፣ ወደ ዓለም ዋንጫ ለመግባት ከጋና አቻው ጋር ወሳኝ ጨዋታ ይጠብቀዋል፡፡ ለዚህም ወሳኝ ጨዋታ አሠልጣኙ ለ27 ተጨዋቾች ጥሪ አድርገው ዝግጅት ጀምረዋል፡፡ በቡድኑ ዝግጅትና በተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ደረጀ ጠገናው ከቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ሆነው ለሁለት ዓመት አገልግለዋል፣ አሁንም በኃላፊነት ይገኛሉ፡፡ ስብስብዎ ከዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ጎን ለጎን ለመጀመርያ ጊዜ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ውጤቱን ጠብቀውት ነበር?

አሠልጣኝ  ፍሬው፡- ከዚህ ቡድን ጋር በዋና አሠልጣኝነት ለሁለት ዓመት ያህል ቆይታ አድርጌያለሁ፡፡ በዚህ ደረጃ ኃላፊነት የሚቀበል አሠልጣኝ ምንም ይሁን ምን ውጤት አልጠብቅም የሚል እምነት የሚኖረው ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም  አንድ ባለሙያ ኃላፊነት ሲቀበል ለውጤት ካልሆነ ለምን ይቀበላል? ኃላፊነትን የምትቀበለው ለውጤት ነው፡፡ ውጤት ለማምጣት መሥራት ያለብኝን ሁሉ ከተጨዋቾቼ ጋር ሠርተናል፣ ፈጣሪም አላሳፈረንም፡፡ ከምሥራቅ አፍሪካ ዋንጫ በተጨማሪ በትልቁ የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመርያ ተጋጣሚያችሁ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ ቡሩንዲ ነበረች፡፡ 7 ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት ካሸነፋችሁ በኋላ በመሀል ኮቪድ-19 ተከስቶ ውድድሮች ለስምንት ወራት ያህል ተቋርጠው ነበር፡፡ በወቅቱ የኮንትራት ጉዳይን ጨምሮ ስሜቱን እንዴት ይገልጹታል?

አሠልጣኝ ፍሬው፡- ስሜቱ እውነቱን ለመናገር ከባድ ነበር፡፡ ምክንያቱም ወረርሽኙ ስፖርታዊ ክንውኖችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ እስካሁን እንዳለ ነው፡፡ ችግሩ እንዳለ ሆኖ አሠልጣኝ እንደመሆኔ ብሔራዊ ተጨዋቾችን ጨምሮ ሌሎችም ውድድሮች በሚያደርጉባቸው ቦታዎች እየተንቀሳቀስኩ ልጆችን እመለከት ነበር፡፡ የቡድኔ ስብስብ ከሁሉም ውድድር በተወጣጡ ልጆች እንዲዋቀር ምክንያት የሆነው ለዚያ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በቅርበት ሆኜ ነበር ሊጉን ስከታተል የነበረው፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ከቡሩንዲ ቀጥሎ ከሩዋንዳ ጋር ነው ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የተጫወትነው፡፡ ውጤቱም ሁሉም እንደሚያውቀው ከሜዳችን ውጭም ሆነ በሜዳችን በተመሳሳይ አራት ጎሎችን በማስቆጠር በድምሩ 8 ለ0 ማሸነፍ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሩዋንዳው ጨዋታ በኋላ በዑጋንዳው የሴካፋ ዋንጫ ላይ ተሳትፋችሁ የዋንጫ ባለቤትም ሆናችኋል፡፡

አሠልጣኝ ፍሬው፡- ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ካደረግናቸው ሁለት ጨዋታዎች ቀጥሎ እንደተባለው ዝግጅት እንድናደርግ መመርያ የተሰጠን ለሴካፋ ዋንጫ ነበር፡፡ ኃላፊነቱ ተደራራቢ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የዋንጫ ውድድሮች ላይ እውነቱን ለመናገር ልምዱም ስላልነበረኝ ከሜዳ ላይ ልምምድ በተጨማሪ የትላልቅ ሙያተኞች ልምድና በዚያ ዙሪያ የተዘጋጁ የሲኒየር ተጨዋቾችን ተሞክሮዎችን በመቀመር ነው ዝግጅት የጀመርኩት፡፡ ተጋጣሚዎቻችንም ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ቡሩንዲ፣ ዑጋንዳና ታንዛኒያ ነበሩ፡፡ ከዚያም በውድድሩ ሊገጥመኝ የሚችለውን ማለትም የቡድኔ ስብስብ ጥራትና ብዛት ከዚያም በላይ ተወዳዳሪዎቹ ሴቶች እንደመሆናቸው ባዮሎጂካል በሆኑ ጉዳዮች ጭምር ሊገጥመኝ የሚችለውን ተግዳሮት በሚገባ ገምግሜ ነው ወደ ውድድር የገባሁት፡፡ የመጀመርያ ጨዋታችን ከጅቡቲ ጋር አድርገን 7 ለ1፣ ቀጣዩ ደግሞ ከኤርትራ ሲሆን እሱንም 5  ለ0፣ ቀጥሎ ለውድድሩ አሸናፊነት ትልቅ ግምት የተሰጠው ታንዛኒያ ሲሆን እሱንም 2  ለ1 ማሸነፍ ችለናል፡፡ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ አንዳንዶች እኛን ለዋንጫ ግምት መስጠት የጀመሩት ከዚያ በኋላ ነበር፡፡ ቀጣዩ ጨዋነታ ከቡሩንዲና ዑጋንዳ ሲሆን፣ በጨዋታው ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች ይልቅ ምንም ግምት ካልተሰጣት ቡሩንዲ ጋር የተጫወትነው፣ ከዋንጫውም በበለጠ ፈታኝ ነበር፣ በጣም ተቸግረን ነው ባለቀ ሰዓት 1 ለ0 ያሸነፍናቸው፡፡ በመጨረሻ ከዑጋንዳ ጋር በነበረው የዋንጫ ጨዋታ ላይ ወሳኝ ተጨዋቻችን ጨዋታው በተጀመረ በሰባተኛው ደቂቃ የቀይ ካርድ ሰለባ በመሆኗ፣ በመጀመርያው የጨዋታ ጊዜ 2 ለ0 ተመርተን በሁለተኛው 45 የጨዋታ ጊዜ እኔም ሁለት እኩል እያለን የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኜ ነበር በጎዶሎ ልጅ 3 ለ2 አሸንፈን ዋንጫ ማንሳት የቻልነው፡፡ የሚገርመው ዓለም ላይ በሌለ ሕግ በቀይ ካርድ ከቴክኒካል ቦታ ከተወገድኩ በኋላ በቀጥታ የወሰዱኝ ጨዋታውን በርቀት እንኳ መከታተል በማልችልበት የሆነ ክፍል ውስጥ አስገብተው ነው የቆለፉብኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ክፍል ውስጥ አስገብተው ሲቆልፍብዎ ምን አስበው ይመስልዎታል?

አሠልጣኝ ፍሬው፡- ዑጋንዳ አስተናጋጅ እንደመሆኗ ዋንጫ መብላት ይገባታል ከሚል እኔ በርቀት ሆኜ ለተጨዋቾች በምልክት ምክር እንዳልሰጥ ታስቦ ከሆነ አላውቅም፡፡ የሚገርመው ዋንጫ መብላታችን ከተረጋገጠ በኋላ እንኳ ፖሊሶች ግባ አልተፈቀደልህም፤ በሚል እንዳልወጣ ሲያደርጉ የነበረበት አጋጣሚም ነበር፡፡ ምስጋና ለጨዋታው ኮሚሽነር ይሁንና መከልከል እንደማይችሉ ከተናገሯቸው በኋላ ነው ተጨዋቾቼን ማግኘት የቻልኩት፡፡ እግር ኳስ በሚመጥን ሥርዓት የሚመራ ከሆነ ውጤቱ ያምራል፡፡ ካልሆነ ግን ከባድ ነው፣ ወደ ዝርዝር ጉዳዩ ሳንገባ አገራችን የሁላችንም ነች በአቅምና ችሎታችን የሚገባንን ቦታና ግልጋሎት ልንሰጥ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሳችኋል፡፡ ከጋና ጋር አንድ የመጨረሻ  የደርሶ መልስ ጨዋታ ይጠብቃችኋል፡፡ ምን እንጠብቅ?

አሠልጣኝ ፍሬው፡- ማሸነፍ ነዋ ሌላ ምን እንጠብቃለን፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ተጋጣሚያችን ጋና ስለሆነ ከባድ ነው በሚል እኛን ለማንኳሰስ የሚጥሩ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ትክክል ነው ተጋጣሚያችን ጋና ነው፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ ምክንያቱም ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ ከቻልን ጋና ማን ነው? ለዚህ ትልቁ ማሳያችን ሊሆን የሚችለው በቅርቡ በሴነጋል አሸናፊነት የተጠናቀቀው የአፍሪካ ዋንጫ ነው፡፡ ትልቅ ከምንላቸው መካከል ጋና በምድብ ማጣሪያ እንዴትና በእነማን እንደተሰናበተ ተመልክተናል፡፡ ተጨዋቾቼም ሆኑ እኔ ስም አናስተናግድም፣ ማድረግ የምንችለውን እናደርጋለን ለዚያም ዝግጁ ነን፡፡ የሚገርመው አንዳንዶች የሰውነት ግዝፈትን እንደ አንድ ማሳያ አድርገው ሊመለከቱ የሚሞክሩ አጋጥመውኛል፣ የጣልናቸው ዑጋንዳ ወይስ ታንዛኒያ ነው አካላዊ የሰውነት ግዝፈት የሌለው? በተደጋጋሚ ተገናኝተን ያሸነፍናቸው ናቸው፡፡ ጋናን ከነዚህ የሚለው በምንድነው? ሜዳ ውስጥ የምገጥማቸው በእኩል ቁጥር ነው፣ ለዚያ የሚሆነውን አቅም ደግሞ እየሠራን ነው፣ እውነታው ይህና ይህ ብቻ ነው፡፡ በቃ የምችለውን ለመሥራት እንዘጋጃለን፣ ዝግጁም ነን፡፡ እርግጥ ነው በአገራችን ውጤት ሲጠፋ ሁሌም የምንቆጨው ብሔራዊ ቡድን ሲሸነፍ ነው፡፡ ይህ መቅረት አለበት፣ ምክንያቱም ለብሔራዊ ቡድናችን ውጤት የምንቆረቆር ከሆነ መጀመርያ ለብሔራዊ ቡድን ግንባታ የሚሆነውን ሥርዓት ዘርግተናል ወይ? ብለን መጠየቅ ከቻልን ብቻ ነው፡፡ ያ ነገር በሌለበት ብሔራዊ ቡድን ላይ ውለድ ማለት ትርጉም የሚሰጥ አይመስለኝም፡፡ ለመሆኑ በአገራችን ምን ያህል አካዴሚዎች ናቸው ያሉን? የምናሠለጥናቸው ልጆች አሁን የደረሱበት ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት የታዳጊ እግር ኳስ ሕይወታቸውን እንዴት ነው ያሳለፉት? ከቤተሰብ እስከ ተቋም ለታዳጊዎች ያለን አመለካከት መገለጫው ምንድነው? እነዚህና ሌሎችም ተግዳሮቶች መቀረፍ ይኖርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎን ጨምሮ ሙያተኛ ነን የምትሉት በሚነግሩን ልክ ብቻ ሳይሆን የዘመኑ እግር ኳስ የሚጠይቀውን አሟልቶ ለመሄድ ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ?

አሠልጣኝ ፍሬው፡- ሥርዓት ያስፈልጋል ስል የእግር ኳሱን ሙያተኛ አይመለከትም ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ችግሩ በዋናነት ያለው ሙያተኛው ጋ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ስንቶቻችን ነን ሌላው ለሠራው ሥራ ተገቢውን ዕውቅና የምሰጠው? የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በስፖርት ቤተሰቡም ሆነ በሌላው ኅብረተሰብ ዘንድ እግር ኳስ ሲባል ከሴቶቹ ይልቅ ለወንዶቹ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ይህን ጉዳይ እንዴት ይመለከቱታል?

አሠልጣኝ  ፍሬው፡- ትክክል ነው ክለብ የሚያስተዳድሩ ተቋማት ከክፍያ ጀምሮ ለወንድ ተጫዋች ለፊርማ ብቻ እስከ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚከፍል እንዳለ እናውቃለን፡፡ በዚህ ልክ ወደ ሴቶቹ ስንመጣ ክፍያው ቀርቶ ቡድን እንኳ ለማቋቋም ያለፈው መከራ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ክለብ የማቋቋሙ ጉዳይ ባለበት ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ የምሥራቅና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ስትሆን፣ በርካታ የሴት ሚኒስትሮች ባሉበት አገር አንድ ወይም ሁለት ካልሆኑ ብዙዎቹ ሞራል እንኳ ሲሰጡ እያየን አይደልም፡፡ ከዚህ በፊት ወንዶች የምሥራቅ አፍሪካ ዋንጫ በሉ ተብሎ መሬት ሳይቀር በሽልማት መልክ እንደተሰጣቸው እናስታውሳለን፡፡ ዛሬ የሴቶች ቡድን የምሥራቅ አፍሪካ ዋንጫ ቀርቶ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ታዲያ እነዚህ ልጆች በሴት ሚኒስትሮቻችን እንዴት ናችሁ ተብለው መጠየቅ አይገባቸውምን? ቀደም ሲል ስናገር የነበረው የአሠራር ሥርዓት ከዚህ ጀምሮ የአመለካከት ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ የሴት እኩልነት የቱ ጋ ነው? አሁንም ጊዜው ስላለ ልጆቹን ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ ራሱ ይህን ጉዳይ በተመለከተ እንዴት ነው ብሎ ሲጠይቅ አይስተዋልም፡፡ ከዚህ ይልቅ አበው ‹‹ላም ባልዋለበት…›› እንዲሉ በአሠልጣኝ ሥራ ገብቶ እገሊት ወይም እገሌ ለምን አልተመረጠችም፣ አልተመረጠም በሚል ትልቅ ክርክር ሲያነሳ ነው የምንሰማው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...