Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለአፍሪካ ባዳ የሆነው የክረምቱ የኦሊምፒክ ጨዋታ

ለአፍሪካ ባዳ የሆነው የክረምቱ የኦሊምፒክ ጨዋታ

ቀን:

በርካታ ስፖርቶችና ውድድሮች የሚከናወኑበት ነው፣ በአራት ዓመታት አንዴ የሚመጣው የክረምት ኦሊምፒክ፡፡ (ከአፍሪካ ውጭ ላሉት ክረምት ቢሆንም ለአፍሪካ ግን በጋ ነው፡፡) በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) አማካይነት የሚሰናዳው የክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ የሚሳተፉት አገሮች ክረምታዊ ጨዋታዎችና አትሌቶች ያሏቸው ናቸው፡፡  ይህን ጨዋታ በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በሰሜን አሜሪካና በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ አገሮች በጉጉት የሚጠብቁት ጨዋታ ነው፡፡ በአፍሪካ ግን በክረምት የሚዘወተሩ ስፖርቶችና መሠረተ ልማቱም በየአገሮቿ የሌሉ በመሆኑ የመሳተፏ ነገር እምብዛም ነው፡፡

እ.ኤ.አ. 1924 በፈረንሣይ አገር የተጀመረው የክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታ፣ በሒደት የጨመሩትን የስፖርት ዓይነቶችን ጨምሮ 15 የስፖርት ኩነቶች ላይ አትሌቶች በበረዶ ላይ ይወዳደራሉ፡፡

የአገሮችን የአየር ፀባይ ሁኔታ መሠረት ያደረገው የክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታ፣ እ.ኤ.አ. 1940 እና 1944 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ሳይከናወን ቀርቷል፡፡ ዘንድሮ 24ኛውን ኦሊምፒያድ የቻይና መዲና ቤጂንግ ከጥር 27 እስከ የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. እያከናወነች ትገኛለች፡፡ ከአፍሪካ ውጭ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ የአፍሪካ ልጆች ኢትዮጵያን ጨምሮ በሚኖሩባቸው አገሮች ምቹ ሁኔታ ስላጋጠማቸው በተለያዩ የክረምት ኦሊምፒኮች ላይ ከመካፈል አልቦዘኑም፡፡

ኢትዮጵያን በሁለት የክረምት ኦሊምፒኮች በ2006 እና በ2010 በአገር አቋራጭ ሸርተቴ የ15 ኪሜ ውድድር  ሮቤል ተክለማርያም መወከሉ ይታወሳል፡፡

በዘንድሮ የቤጂንግ የክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታ ከአምስት የአፍሪካ አገሮች የተገኙ አትሌቶች እየተካፈሉ ነው፡፡ እነዚህም ከኤርትራ፣ ማዳጋስካር፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያና ጋና የተገኙ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. 2018 በደቡብ ኮሪያ በተካሄደው ኦሊምፒክ ጨዋታ ከተካፈሉት ላይ ስምንት የአፍሪካ አገሮች በሦስት ቀንሷል፡፡

ማዳጋስካር ኑሮዋን በፈረንሣይ ባደረገች አትሌቷ በቁልቁለት ስካይንግ (Down Skiing) ለሁለተኛ ጊዜ ትወከላለች፡፡ የ16 ዓመቷ ማሊታኒያ ክላርክ ያለፈውን የደቡብ ኮርያን ጨምሮ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የምትሳተፍ ሲሆን፣ ሜዳሊያ በማምጣት የመጀመርያው አፍሪካዊት መሆን እንደምትፈልግ ትናገራለች፡፡ አትሌቷ ከዚህ ቀደም በደቡብ አሜሪካና አውሮፓ አገሮች ላለፉት አራት ዓመታት ስትወዳደር ቆይታለች፡፡

ሌላዋ ተሳታፊ ከኤርትራ የተገኘውና በካናዳ የሚኖረው ሻኖንን አብደላ በአልፓኒ ስካይንግ (Alpine Skiing) ስፖርት ዓይነት አገሩን ይወክላል፡፡ ሻኖንን ለሁለተኛ ጊዜ ኤርትራን በክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታ የወከለ ሲሆን፣ ባለፈው የኦሊምፒክ ጨዋታ ዘረኞች በስድብ ተንኩሰውት ነበር፡፡ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ የተለያዩ ቪዲዮዎችን የሚለቀው ኤርትራዊው ሻኖን፣ በርካታ ኤርትራውያን ስፖርተኞችን ለማነቃቃት ተስፋ ሰንቄያለሁ ብሏል፡፡

ከሞሮኳዊ አባቱና ከካናዳዊት እናቱ የተወለደው ሳሚላም ሐምዲ ሞሮኮን ወክሏል፡፡ በወንዶች አልፓይን ስካይንግ የስፖርት ዓይነት የሚወዳደር ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የነበረውን ውጤት ለማሻሻል ማቀዱን ገልጿል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2010 በክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታዎች መካፈል የጀመረው ሳሚ፣ በ2012 የአውስትራሊያ የወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ወርቅ ማግኘት ችሏል፡፡ ከዚያም እ.ኤ.አ. 2014 በሩሲያ ሶቺ በተሰናዳው ኦሊምፒክ ሞሮኮን ወክሎ መካፈል ችሏል፡፡

በዘንድሮ የቤጂንግ ኦሊምፒክ ጨዋታ በአገር አቋራጭ ስካይንግ (Cross Country Skiing) ናይጄሪያ በሳሙኤል ኢኪፒፋን ተወክላለች፡፡ የፈረንሣይና የናይጄሪያ ጥምር ዜግነት ያላው ሳሙኤል እ.ኤ.አ. በ2021 ፈታኝ ቅድመ ማጣሪያን አልፎ ለዘንድሮ ኦሊምፒክ ጨዋታ መድረስ እንደቻለ ይገልጻል፡፡ በፈረንሣይ ልምምዱን ሲያደርግ የቆየው አትሌቱ በ2021 በተደረገው የዓለም ዋንጫ ተካፋይ ነበረ፡፡ በዘንድሮ ጨዋታ በሚኖረው ተሳትፎ ጥሩ ውጤት አምጥቶ በ2026 ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ የመሳተፍ ህልም እንደሰነቀ አልሸሸገም፡፡

ሌላዋ በቤጂንግ የምትካፈለው አፍሪካዊት አገር ጋና ስትሆን በአውሮፓ በማደጎ ያደገው ካርሎስ ሜደር ትወከላለች፡፡ በአልፒን ስካይር (Alpine Skier)  ስፖርት የሚወዳደር በዕድሜ ተለቅ ያለ አትሌት ነው፡፡ ካርሎስም እንደ ሌሎቹ አፍሪካውያን ተሳታፊዎች ለወጣቶች ምሳሌ ለመሆን ማቀዱን ጠቅሷል፡፡

ደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ የመጀመርያዋ በክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታ የተሳተፈች አገር ያሰኛት እ.ኤ.አ. በ1960 በካሊፎርኒያ በተደረገ ስኳቫሊይ ጨዋታ (Squaw Valley Games) በመገኘቷ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በምታራምደው የአፓርታይድ ሥርዓት ምክንያት በመታገዷ ለ34 ዓመታት ተለይታ ነበር፡፡ ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ደቡብ አፍሪካን ካገደ በኋላ 15 የአፍሪካ አገሮች መሳተፍ የቻሉ ሲሆን፣ በዚህም ከአፍሪካ 54 አገሮች 18 በመቶ የሚሆኑት በክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታ መካፈል ችለዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካ፣ ቶጎና ኬንያ ለዘንድሮ ኦሊምፒክ ጨዋታ መካፈል የሚያስችላቸውን ዕድል በቅድመ ማጣሪያ ማሳካት አልቻሉም፡፡

የክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ለመካፈል እምባዛም ማሳካት ያልቻሉት የአፍሪካ አገሮች፣ ለጨዋታው በቂ ልምምድ ለማድረግ የልምምድ ሥፍራዎች ያለመኖርና የተሟላ መሠረተ ልማት ማጣታቸው እንደ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡

በቤጂንግ ኦሊምፒክ ከአምስቱ አገሮች ከተገኙት አፍሪካውያን ሜዳሊያ ሊያመጡ የሚችሉ ይኖራሉ የሚል ግምት የሚሰነዝሩም አልታጡም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...