Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉስለማይታዩት ሴቶች እንናገር

ስለማይታዩት ሴቶች እንናገር

ቀን:

በበልዩ እስጢፋኖስ

ፆታ የተፈጥሮ መለያ ምክንያት ያለው ተፈጥሮ ከመሆን ባለፈ፣ በሰዎች አዕምሮ የተፈጠሩት አተያዮች ማኅበራዊ ውጤት ናቸው፡፡ ይህም ምን ማለት ነው? ወንድ ወይም ሴት ስንል የሚሰማን ሁሉ በሰዋዊ ፍልስፍና የምንገነዘብበት መንገድ እንደ ማኅበረሰቡና ዘመኑ የተለየ ነው፡፡ ይሁንና የማይካዱ መሬት ላይ ያሉ ትልልቅ እውነታዎች አሉን፡፡ መናናቅ፣ መፈራራት፣ አገልጋይና ተገልጋይ የመሆን፣ ጨቋኝና ተጨቋኝ መሆን የመሳሰሉት ስሜቶች ተንሰራፍተው ይገኛሉ፡፡ ይሁንና እነዚህን ሁኔታዎች ለመከላከልም ሆነ ለመካስ፣ በየዘመኑ በተለይም ሴቶችን በተመለከተ የተለያዩ ንቅናቄዎች በቡድንም በተናጠልም ይስተዋላሉ፡፡ ከእነዚህ መንገዶች አንዱ የሴቶች እኩልነት የሚለው ጥያቄ በስፋት ይስተጋባል፡፡

በተለይም በአገራችን የሴቶች እኩልነት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ መልከ ብዙ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ አንዳንዶች ሴቶች ከወንዶች እኩል ዕድል አልተሰጣቸውም ይሉናል፡፡ አንዳንዶቹ የኢኮኖሚ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የትምህርት፣ አንዳንዶቹም የትዳር እኩልነት እያሉ በተለያዩ መንገዶች ጥያቄያቸውን ለማጉላት ሲጥሩ ይታያል፡፡ በእኔ ዕይታ ሁሉንም መንገዶች አንድ የሚያደርጋቸው ሴቶች እኩል አይደሉም የሚለውን ቅድመ ድምዳሜ የያዙ መሆናቸው ሲሆን፣ ሌላው እጅግ በጣም የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር የእኩልነት ጥያቄ መለኪያቸው ወንዶች መሆናቸው ነው፡፡ 

እንደ አንድ ኢትዮጵያዊት ሴት ከወንድ አንፃር ለትምህርት በሚሰጥ ጊዜ፣ የቤት ውስጥ ኃላፊነት ሸክም፣ የመንገድ ዳር ጉንተላና ለከፋው፣ ከዚህም ሲያልፍ ጠለፋና ደፈራውን ተቋቁሞ፣ ፍርኃትና ይሉኝታን ታቅፎ ማደግ የዕለት ተዕለት ልማድ በመሆኑ መደበኛ አኗኗር ዘይቤ እስኪመስል ድረስ ተላምደን አድገናል፡፡ ነገር ግን እንደ አንድ የፍጥረት አካል ሁሌም ያለኝ ጥያቄ እንደ ሴት ዕውቅና የመሰጠት እንጂ የእኩልነት አይደለም፡፡ የእኩልነት ጥያቄ በመሠረቱ እኩል አይደለሁም የሚለውን እምነት መጀመርያ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ እኩል ያለ መሆን መለኪያ ተደርገው የሚጠቀሱት ጉዳዮች በአብዛኛው ወንድን የመሆን እንጂ ሴትን የመሆን አይመስልም፡፡ የእኔ ሐሳብ ማኅበረሰባችን ሴትን የሚያይበት መነጽር ቢስተካከል፣ ሴት እንደ አንድ ፍጥረት ወንድም እንደ አንድ ፍጥረት በተፈጥሮ በተሰጠን ማንነት በሕይወት ልምድ ታግዘን፣ ውስጣችንን አዳምጠን፣ አንዱ የአንዱን ጉድለት ሞልቶ መኖር እንዳለብን ብናምን ይህ ሁሉ ጥያቄ ተገቢ ባልነበረ የሚል ነው፡፡

 በተለይም ዘመነኛው የከተማ የሴትነት ጥያቄዎች አሁን አሁን ወንዶች በረገጡበት ሁሉ ሴቶች መርገጥ አለባቸው የሚል እንጂ፣ እውነተኛ የሴቷን ጥያቄ ያነገቡ ስለመሆናቸው ያጠራጥረኛል፡፡ በተለይም በተቋማት ደረጃ ሴትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ለውጥ እናመጣለን የሚሉ አካላት በየቀኑ መከራቸውን በተለያየ መንገድ በሚያዩ ሴቶች ላይ መቀለድ የያዙ ይመስላል፡፡ በተለይ ሴትነትን ከፖለቲካ ጋር እያነካኩ በሚዲያ በማጮህ እየተሄደበት ያለው መንገድ ንግድ እንጂ ትክክለኛ ጥያቄ ላለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

አገራችን የሴቶችን ጉዳይ በተለየ ሁኔታ ለመሥራት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ተቋም ካሏቸው አገሮች መካከል ትጠቀሳለች፡፡ ነገር ግን በመንግሥት የአፈጻጸም ግምገማና እንደ አንድ የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በደካማ አፈጻጸም ቅድሚያ ተጠቃሽ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ ከመንግሥት ውጪም መንግሥታዊ ያልሆኑ የተለያዩ ተቋማት ብቅ ማለታቸው አልቀረም፡፡ ነገር ግን ‹‹ያው በገሌ…›› ዓይነት አካሄድ በብዛት ይስተዋላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገነነ የመጣው አካሄድ ደግሞ የበለጠ አሳዛኝ ነው፡፡ የብዙኃን ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ችግር ከመመለስ ይልቅ፣ ጥቂት የካሜራ ፊት ተግባራትን ማጉላት የተለመደ እየሆነ ነው፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት በሥልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ካቢኔ አባላትን ግማሽ በግማሽ ሴቶችን አደረጉ ተብሎ ትልቅና አዲስ ነገር በአገሪቱ ተፈጠረ በሚል፣ በድጋፍም በተቃውሞም ታጅቦ ሲወራ ከረመ፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ ግን የሴት ሚኒስትሮቹ በአብዛኛው በወንዶች ተተክተዋል፡፡ ይህ ለምን ሆነ ብንል መልከ ብዙ ምክንያቶች ሊሰጡ ቢችሉም፣ በእኔ ዕይታ ግን ሁኔታው የበለጠ በሴቶች ላይ የቀልድ ያህል ሆኗል ባይ ነኝ፡፡ እንኳንስ በሚኒስትርነት ደረጃ በየትኛውም የሥራ መስክ ላይ ሴቶች በኃላፊነት ሲቀመጡ በጀ የማይለው ማኅበረሰብ ሲጠነክሩ ‹‹ቦሲ››፣ ሲደክሙ ደግሞ ሴት ስለሆኑ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ የተለመደ በሆነበት ቁጥርን ብቻ ባገናዘበ መንገድ ለታይታ ተሰጠ ሹመት መጨረሻው አላማረም፡፡ እናም በአደባባይ የተሾሙት እንደ ነገሩ ሲሻሩ ሴት ስለሆኑ እንጂ፣ ከሥራው አንፃር ታይተው መገምገማቸውን እንደ ማኅበረሰብም እንደ መንግሥትም አናነሳውም፡፡

እንዲህ ያለ ትልቅ ለውጥን አመጣ የተባለ ጉዳይ ዓመታትን መዝለቅ አለመቻሉ ለታይታ እንጂ፣ ከልባችን አምነን ያደረግነው እንዳልሆነ ማሳያ ነው፡፡ ታዲያ በሴቶች ስም የሚነግዱ ተቋማት ይህንን መሰል አስተሳሰብ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮችን ትተው፣ ‹‹ማነው ባለተራ?›› በሚል መንፈስ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ባገኘ ጉዳይ ሁሉ ሴቶች ከሌሉበት በሚል እየጮሁ የዜና ርዕስ መሆን ልማድ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ በ2013 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት ከነበሩ ግርግሮች መካከል፣ ‹‹ሴቶች በምርጫ ወቅት ለሚደርስባቸው ጥቃት ጥቆማ የሚሰጥ የስልክ መስመር ዘርግተናል›› የሚል ነበረ፡፡ ልክ ሴቶች ምርጫን ጠብቀው ጥቃት ይደርስባቸው ይመስል ለደጓሚ የሚመች ርዕስ እየፈጠሩ፣ የዕለት ተዕለት ኑሮ ከተራራ በላይ ሸክም ሆኖባቸው ዙሪያው ገደል ለመሰላቸው ሴቶች የማይጠቅም ሐሳብ ይወራል፡፡ ከምርጫ በኋላስ? የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፣ ድጋፉ በጥቂቶች የምቾት መዳፍ ውስጥ ሆኖ ውጤት አልባ እየሆነ ነው፡፡ መንገዳቸውን ከሥር መጥረግ እንጂ ታግለውና ተቸግረው አንድ የሆነ ቦታ ላይ የደረሱ ሴቶችን መጠቀሚያና ተጠቃሚ ለማድረግ ብቻ መጣር፣ የሴቶችን ጥያቄ ይመልሳል ብዬ አላምንም፡፡ በxገራችን የወንዶች ትልቁ ፈጠራ ብዬ የማስበው የሴቶችን ሥነ ልቦና መቀየር መቻላቸው ይመስለኛል፡፡ ሴቶች በአካላቸው፣ በውሳኔያቸውና በሐሳባቸው እንዲሸማቀቁ በማድረግ ራሳቸውን ሆነው እንዲኖሩ አለመደረጋቸው ነው፡፡ በዚህ በኩል የሚታይን ችግር በየመሥሪያ ቤቱ ሥልጣን ካላገኙ በማለት አንፈታውም፡፡

ሰሞነኛ ማሳያዎችን በመጥቀስ ሐሳቤን ላብራራው፡፡ በሕግ አስገዳጅነት የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ በዚህም የሥራ አስፈጻሚ አባላትና ፕሬዚዳንቶች ተመርጠዋል፡፡ ሆኖም የማኅበሩ አባላት ከሆኑ ጠበቆች በነፃነት የተመረጡ ሳይሆኑ ቅድመ ስብሰባ በተደረገ ስምምነት በሚመስል መንገድ የተደረገ ነበር፡፡ ከሁሉ ያስደነቀኝ ግን የሴት ፕሬዚዳንት በነፃ ምርጫ ቢደረግ ሊኖር አይችልም ከሚል እምነት ይሁን ለዕይታ እንዲመች፣ አንድ ሴት መኖር አለበት በሚል የውስን ባለሙያዎች ቅድመ መግባባት ሊመረጡ ችለዋል፡፡ በእርግጥ ተመርጠዋል ለማለት ይቸግራል፡፡ ምክንያቱም አባላት አምነውባቸው ቢያደርጉት እንጂ፣ በግድ በመሆኑ ተቀባይነቱ ላይ ነጥብ የሚያስጥል ነው፡፡ በዚህ ተገርሜ ሳልጨርስ፣ ‹‹በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች አባላት ውስጥ ግማሹ ሴት መሆን አለባቸው ሲሉ ሃያ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጠየቁ›› የሚል ዜና ሰማሁ፡፡ እነዚህ ሃያዎቹ በእርግጥም ይህንን በማለታቸው የሚያገኙት ነገር ያለ ይመስላል፡፡ አሁንስ ከመገረም አልፎ የሚያናድድ እየሆነ ነው፡፡ የሚመረጡት አሥራ አንድ ኮሚሽነሮች ናቸው፡፡ አሥራ አንድ ቁጥር ደግሞ ግማሽ መሆን እንደማይችል እንኳ አላስተዋሉም ብዬ ተራ የንዴት ሐሳብ አሰብኩ፡፡

ሴት ግማሽ ስለሆነ ብቻ ምን እንደሚያረጋግጥ እንኳን እኔ ጠያቂዎቹም የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ ማንሳት ያለብን ቁጥርን ነው ወይ የሚለው ይከነክነኛል፡፡ ለምሳሴ ከግማሽም በላይ ሴቶች ቢሆኑ በሥነ ልቦናና በራስ መተማመን ባልዳበረ አዕምሮ ቢቀመጡ፣ በጥቂት ወሳኝ የወንዶች ተፅዕኖ ሥር ከመዋል የሚከለክላቸው አይደለም፡፡ ብቃቷን ማሳመን የቻለች አንድ ሴት እንኳ ብትገኝ ግን ሁሉንም ማሳመን ይቻላል፡፡ ምንም ሴት ባለመኖሩም የኢትዮጵያ ሴቶች አልተወከሉም ለማለት ይቸግረኛል፡፡ በኮሚሽኑ ውስጥ ሴት ግማሽ ስለሆነ ፖለቲካዊና መንግሥታዊ ያልሆኑት ተቋማት የሥራ ሪፖርት ከመሆን ባለፈ፣ ለብዙኃኑ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ተምሳሌት ይሆነናል ብለን እንዳናምን በግድ እንጂ በውድ የሆነ፣ ስለሆነ በተገኘው አጋጣሚ ተለምኖ የሚገኝ ኃይል ተቀባይነቱ ደካማ ነው፡፡

በእኔ እምነት በትክክል የሴቶች በደል ምላሽ እንዲያገኝ የሚፈልግ ተቋምም ሆነ ግለሰብ፣ ጥረው ተጣጥረው የሆነ ቦታ ላይ በደረሱ ሴቶች ላይ መረባረብ ሳይሆን፣ ከሥር ከመሠረቱ ሴቶች ራሳቸውን ከፍ አድርገው እንዲያዩ ቀና ብለው ራሳቸውን ሆነው እንዲኖሩ ከጥገኝነት አስተሳሰብ እንዲወጡ የሚያደርግ ማኅበረሰብ ለመፍጠር መጣር እንጂ፣ ወንዶች በረገጡበት ሁሉ በመርገጥ የሴቶች ጥያቄ ምላሽ ያገኛል ብዬ አላምንም፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት የተሰማኝ ይህ ነበር፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ለሰባ ሺሕ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ሴቶች የስልክ ቀፎ እሰጣለሁ የሚል ዜና አሠራ፡፡ የእኔ ጥያቄ የነበረው ግን በዓመት አንድ ቀን ታሪክን ለመዘከር በሚከበር ዕለት በሚወጣ ወጪ፣ የሴቶችን እኩልነት ነው ወይስ ጥገኝነት የምናረጋግጠው የሚል ነው፡፡ እነዚህ ሰባ ሺሕ ሴቶች የሚሰጣቸውን የስልክ ቀፎ ካርድ አይፈልግም እንዴ? ነው ወይስ ምግቧን እንኳ ለመብላት የባሏንና የልጆቿን ተራ እንድትጠብቅ በሚያደርግ ባህል ውስጥ እየኖረች ያለች ሴት ካርድ ሙላልኝ ብላ እንድትጠይቀው ነው፡፡ ዳሩ አጠቃቀሙንም ማወቅ የምትጠቀምበት ምክንያትም ሊኖር ይገባል፡፡ የእኔ ሐሳብ ሴቶች ከልጅነታቸው በራሳቸው መንገድ ተምረውም ይሁን ነግደው ራሳቸውን እንዴት ማኖር እንደሚችሉና መወሰን እንደሚችሉ ማገዙ የተሻለ ነበር፡፡ ዋናው ነገር ሰሞንኛ አጀንዳን እየተከተሉ ግማሾቹ ሴት ካልሆኑ የሚል ጩኸት ምን ጥቅም እንዳለውም አብረው ቢያስረዱን? አለበለዚያ በእኛ በሴቶች ስም መነገዱን ትተው ሌላ አዋጭ መንገድ ቢፈልጉ ጥሩ ነው፡፡

እኛ ሴቶችም ብንሆን በችግርም ይሁን በድሎት አንድ ስም ያለው ቦታ ስንደርስ፣ የሴቶች እኩልነት የሚሉት ሽፋን በመጠቀም ሁሉ ነገር ላይ በግድ ጣዱን ከማለት በፊት ማሰብ ያለብን ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ ይኸውም በሥራችን እንጂ ፆታችንን ብቻ መሠረት በማድረግ የምንጠይቀው ቦታ ምቾቱ ለግለሰቦች እንጂ እንደ ማኅበረሰብ የሚፈጥረውን አስተሳሰብና ለሌሎች ሴቶች መሸማቀቂያ ከማድረግ መቆጠብ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ‹‹እንኳንስ ዘምቦብሽ…›› እንደሚሉት ቀድሞውኑ በሴቶች ችሎታ በሚጠራጠር ማኅበረሰብ ውስጥ በግዳጅ ቦታ ይሰጠን ሲባል የምናረጋግጠው ችሎታን ሳይሆን፣ ጥቅምን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በሴትና በወንድ መካከል ልዩነት እንጂ፣ የእኩልነት ሚዛን እንደሌለ ልናምን ይገባል፡፡ ምክንያቱም አሁን በገበያ ውስጥ ያለውን የእኩልነት ጥያቄ ስናስተውለው ወንድ የመሆን ጥረት እንጂ፣ ሴት እንደ ሴትነት ያላትን አቅምም ሆነ ችሎታ ዕወቁልኝ የሚል ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ማኅበረሰባችን መከባበርን እንዲለምድ መሥራት ትተን ለዕይታ ቅርብ በሆኑ ጥቂት ሴቶች ላይ ለመሥራት መጣር፣ ሴትነት እየተበዘበዘ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ እንድደርስ አድርጎኛል፡፡ ለማይታዩት ግፍን በየዕለቱ እንደ መና ለሚቀበሉ ብዙኃን የኢትዮጵያ ሴቶች እንናገርላቸው፡፡

ከአዘጋጁጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...