Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከችግር ያልፀዳው የኤቲኤም አገልግሎት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኤቲኤም የባንክ አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ 13 ዓመታትን ተሻግሯል፡፡ በወቅቱ በአንድ ባንክ ይሰጥ የነበረው የኤቲኤም አገልግሎት አሁን ላይ 17ቱም የንግድ ባንኮች ተቀላቅለውታል፡፡

ባንኮቹ በግል ከሚሰጡት አገልግሎት ባሻገር ሁሉንም ባንኮች በማገናኘት ካርዶቻቸው ከሁሉም ባንኮች የኤቲኤም ማሽኖች ገንዘብ እዲያወጡ የሚያስችል አሠራር በኤትስዊች ኩባንያ በኩል እየተከናወነ መሆኑ አገልግሎቱ እየሰፋ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡

ቀስ በቀስ አገልግሎቱ እየተለመደ የመጣው ይህ በኤቲኤም ካርድ ገንዘብ የማውጣት ልምድ አሁን ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የባንክ ደንበኞችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡

እስካለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ የኤቲኤም ባንክ ተገልጋዮች ከ225.6 በላይ የኤቲኤም የገንዘብ ልውውጦች በባንኮች ኤቲኤም በኩል የተካሄደ ሲሆን፣ እንደ ኢትስዊች መረጃ መሠረት ደግሞ የአንዱ ባንክ የሌላውን ባንክ በመጠቀም ከ38.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ገንዘብ የማውጣት እንቅስቃሴዎች በኢትስዊች በኩል ተከናውኗል፡፡

ይህም ከቀዳሚው ዓመት 41.5 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑ የካርድ ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎችና በዚህም የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ባንኮች ካሉዋቸው ከሰባት ሺሕ በላይ የኤቲኤም ማሽኖች ከ3,100 በላይ የሚሆነውን የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተውም፣ የኤቲኤም ካርድ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት እያደገ መጥቷል፡፡

ባንኩ ካሉት ከ33 ሚሊዮን በላይ የቁጠባ ደብተር ካላቸው ደንበኞች ውስጥ ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የባንክ ደንበኞች የኤቲኤም ካርድ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ በ2013 የሒሳብ ዓመትም በሁሉም ባንኮች የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን  ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በየዓመቱ ከአራት ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ ይዞ እየሠራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከፍተኛ ቁጥር የካርድ ተጠቃሚዎች ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሆነ ሌሎች ባንኮች የኤቲኤም ካርድ ለማግኘት ወራት እየጠበቁ ነው፡፡ ኤቲኤም ካርድ እንዲኖራቸው ጥያቄ ያቀረቡ አንዳንድ ደንበኞች ከአራት ወራት በላይ እንደፈጀባቸው ይናገራሉ፡፡

የአገልግሎት ጊዜው ያበቃ የኤቲኤም ካርድ ለማስቀየር እየፈጀ ያለው ጊዜም በደንበኞች ዘንድ ቅሬታ እየቀረበበት ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተወሰነ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ችግር የተፈጠረው የሲስተምና የተያያዥ ጉዳዮች ችግር ቢሆንም አሁን ችግሩን ፈትቻለሁ ብሏል፡፡  

በዋናነት ይህን ጥያቄ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሚመለከት ቢሆንም እንዲህ ያለው የደንበኞች ጥያቄ አሁን ላይ በአንዳንድ ባንኮች ላይም እየቀረበ ነው፡፡ በወቅቱ ከሲስተምና ከአንዳንድ ሁኔታዎች የደንበኞችን ጥያቄ ወዲያው መፍታት ባይችልም አሁን ችግሩን መፍታት መጀመሩን የሚገልጸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በአንፃሩ ግን በካርድ የመጠቀም ልምዱ እየዳበረ መሄዱን ያመለክታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ6.8 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑ ቆጣቢ ደንበኞቹ ውስጥ 1.7 ሚሊዮን ያህሉ የኤቲኤም ካርድ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚያመለክተው ከአዋሽ ባንክ የተገኘው መረጃ ደግሞ አንድ ደንበኛ የኤቲኤም ካርድ ተጠቃሚ ለመሆን ባመለከተ በአንድ ሳምንት ውስጥ ካርዱን ማግኘት የሚቻል አሠራር መዘርጋቱን ያመለክታል፡፡

የኤቲኤም ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚሹ ደንበኞች ቁጥር እያደገ በመሆኑ በቀጣይ ይህ አገልግሎት የበለጠ እያሳደጉ መሄዱ የሚጠበቅ መሆኑን የሚገልጹት የአዋሽ ባንክ የካርድ ባንኪንግ ዳይሬክተር አቶ መልካሙ ታደሰ እንደሚገልጹት፣ አዋሽ ባንክ አገልግሎቱን እየሰፋ በመምጣቱ አንድ ኤቲኤም ካርድ ለማግኘት ያመለከተ ደንበኛ በአንድ ሳምንት ውስጥ ካርዱን እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ ከተያዘው የአንድ ሳምንት ጊዜ በላይ ቢዘገይ ከባንኩ አቅም በላይ በሆነ ጉዳይ ነው፡፡

ባንኮች ይህንን የኤቲኤም ካርዶች ፕላስቲኩንና ቺፕሱን ከውጭ በማምጣት እዚህ ስም በማተም የሚጠቀሙ መሆኑን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ ካርዱ ላይ የሚታተመውን የደንበኛውን ስምና ቁጥር የሚያትም ማሽን ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ በፕሪሚየም ስዊች ሥር ያሉ ስድስት ባንኮችም ካርዶቻቸውን በጋራ የሚያትሙበት ማሽን እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ኢትስዊችም በራሱ ማተሚያ የሚጠቀም መሆኑ ታውቋል፡፡

 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እነዚህን የኤቲኤም ካርዶች ፕላስቲክ ካርዱን በማስመጣት የደንበኛውን ስም የሚያትመው በራሱ ማሽን በመሆኑ በቶሎ አገልግሎቱን ለመስጠት ያስችለኛል ይላል፡፡ በኤቲኤም ካርድ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን በየጊዜው እየጨመረ ቢሆንም፣ ካርዱ ግን ከዚህም በላይ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት የሚጠቁሙት አቶ መልካሙ፣ ብዙ ተጠቃሚዎች የኤቲኤም ካርድ ገንዘብ ለማውጣት ብቻ የሚጠቀሙበት መሆኑ አግባብ እንዳልሆነ ያመለክታሉ፡፡ ካርዱ ገንዘብ ከማውጣት በላይ ሁነኛ የዘመናዊ ግብይት ማከናወኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

በኤቲኤም ገንዘብ የማውጣት ልምዱ ማደጉ በቅርንጫፎች አካባቢ ያለውን መጨናነቅ በእጅጉ ቀንሶታል ያሉት አቶ መልካሙ በጥሬ ገንዘብ መገበያየትን ለመቀነስ የኤቲኤም ካርድ በፖስ ግብይት በሚፈጸምባቸው የተለያዩ የንግድ መደብሮችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በካርዳቸው ክፍያ መፈጸም ይችላሉ ብለዋል፡፡ ይህ ግን እንብዛም በመሆኑ ሰዎች ክፍያቸውን  በካርድ እንዲፈጽሙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፖስ ማሽንን መጠቀም አለባቸው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ ባንኮች ፖስ ማሽኖችን በነፃ የሚሰጡ መሆኑ መልካም ዕድል መሆኑን የጠቀሱት አቶ መልካሙ፣ ድርጀቶችም ተጠቃሚዎችም ፖስ ማሽን ተጠቅመው ክፍያ እንዲቀበሉና እንዲከፍሉ የሚገፋ ሕግ ሊኖር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የኤቲኤም አገልግሎትን ከማስፋፋት አኳያ አሁን አሉ የተባሉ ተግዳሮቶች መካከል ካርዱን ከውጭ ለማስመጣት የሚጠየቀው ቀረጥ ከፍ ማለት አንዱ መሆኑን የሚጠቀሙት ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች፣ አገልግሎቱን የበለጠ ለማስፋት ከቀረጥ ጋር የተያያዙ ችግሮች መፈታት ይኖርባቸዋል ይላሉ፡፡ ባንኮቹ ካርዱን ለማሳተም ከሚያወጡት ወጪ ጋር የተመጣጠነ የቀረጥ ክፍያ እየተጠየቁ ባለመሆኑ የአገልግሎት ወጪያቸው እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ አቶ መልካሙ ደግሞ አገልግሎቱን የበለጠ ለማስፋትና በጥሬ ገንዘብ የሚደረግ የገንዘብ ዝውውርን ለመቀነስ የኤቲኤም ካርዶች ያላቸውን ጠቀሜታ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡

ከኤቲኤም አገልግሎት መስፋፋት ጋር በተያያዘ እየተገለጸ ያለው ሌላው ችግር ደግሞ የኤቲኤም ማሽኖችን ማኖሪያ ቦታ ነው፡፡

አሁን ላይ በብዙ ሕንፃዎች ላይ ለአንድ ኤቲኤም ማሽን ማኖሪያ እየተጠየቀ ያለው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ የአገልግሎት ወጪው እንዲጨምር አድርጓል፡፡ የካርድ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ ቢገኝም አገልግሎቱን የበለጠ ለማሳደግ አሁንም ተጨማሪ ዕርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው አቶ መልካሙ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

በፖስ የሚደረገው ግብይት ከኤቲኤም ካርድ አንፃር ሲታይ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ መደብሮች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ክፍያቸውን በፖስ ማሽን ተጠቅመው የመገበያየቱ ልምድ መዳበር አለበት፡፡ በብዙ ቦታዎች የፖስ ማሽን ተፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጥ በሁለቱም ዘንድ ፍላጎቱ መኖር አለበት፡፡ ከጥሬ ገንዘብ ግብይት ለመውጣት አንዱ መንገድ ይህ መሆኑን በመገንዘብ አሁን ባለው መሠረተ ልማት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ አስገዳጅ ሁኔታም ተፈጥሮ ይህ መከናወን አለበት ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች