Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለውጭ ምንዛሪ ችግር ተግባራዊ መፍትሔ ይሰጥ

የውጭ ምንዛሪ ችግር በእጅጉ በተንሰራፋባት ኢትዮጵያ፣ ከውጭ የሚገባው ዕቃ መጠንና ለዚህም የሚውለው የውጭ ምንዛሪ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው፡፡ ወጪያችንና ገቢያችንን የሚመጥንም አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ለገቢ ዕቃዎች የሚወጣው ወጪ ዛሬ ላይ ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡ ይህ በ2013 በጀት ዓመት አማካይ የምንዛሪ ዋጋ ካሠላነው ከ800 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል ማለት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በ2013 በጀት ዓመት 3.6 ቢሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ ገቢ አግኝታለች፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የተሻገረበት መትም ነው፡፡ ይህም በአማካይ የምንዛሪ ዋጋ በበጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ በብር ሲመነዘር ከ155 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ በገቢና በወጪ ንግድ መካከል ያለው ልዩነት ወይም ጉድለት ከ650 ቢሊዮን ብር በላይ በዶላር ከታሰበ ደግሞ ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ ልዩነት አለው፡፡ በገቢና ወጪ ንግድ መካከል ያለው እጅግ የሰፋ ልዩነት ከዓመት ዓመት እያደገ ለመምጣቱ አንዱ ምክንያት የወጪ ንግዳችን አዝጋሚ ብቻ ሳይሆን ዕድገቱ ከአምስት በመቶ በታች ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ የብር የመግዛት አቅም ከዓመት ዓመት እየተዳከመ መሄድም በወጪና በገቢ ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት እያሰፋ እንዲሄድ አድርጓል፡፡

እንደ አገር ሲታይ ይህ የአፈጻጸም ትልቅ ችግር ነው፡፡ የንግድ ሚዛን ጉድለቱን ለማጥበብ አለመቻሉን ከማመላከቱም በላይ አሁንም ክፍተቱን ለማከም ይህ ነው የሚባል ተግባራዊ ሥራ እየተሠራ አለመሆኑን ያመለክታል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ እየጨመረ መምጣት በአንፃሩም የብር የመግዛት አቅም ፈጣን በሚባል ደረጃ እየቀነሰ መሄድ፣ በገቢና በወጪ ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት በእጅጉ እያሰፋው መምጣቱ ብቻ ሳይሆን ልዩነቱን ለማጥበብ ከልብ ያለመሠራቱን ያመለክታል፡፡ ይህ አካሄድ አሁን ላይ ሲታይ አደገኛ ሊባል የሚችል ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ በእጅጉ እያደገ የመጣው የገቢ ንግድ ምርት እንዳሻው እንዲገባ መፈቀዱና በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶችን ሳይቀር ያለ ልክ ገበያውን ሲያጥለቀልቁ የሚወሰድ ዕርምጃ ወይም ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር ባለመዘርጋቱ የንግድ ሚዛኑ ጉድለት የበለጠ እንዲሰፋ አድርጓል፡፡

ከወጪ ንግዱ የሚገኘው የምንዛሪ ገቢ ያለበት የዕድገት ደረጃ ሲታይ ደግሞ፣ ፈፅሞ የገቢ ንግድ ወጪን ለመሸፈን አይደለም ለማጥበብ እንኳን ዕድል የሌለው መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡ በየዓመቱ የሚገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ነዳጅና ማዳበሪያ ለመግዛት እንኳን የማያስችል መሆኑ እየታወቀ በሌለ የውጭ ምንዛሪ የሸቀጣ ሸቀጥ መራገፊያ መሆናችንም ያሳስበኛል፡፡

በዶላር እጥረት የምትቸገር አገር፣ ዶላር ከፍላ የምታመጣቸው ዕቃዎች መብዛትና ለዚህም የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ሆኖ መገኘት፣ አገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ጫና እያሳረፈ የመሆኑን ያህል ይህንን እንዴት እንግታ በማለት ችግሩን ለመፍታት የሚደረግ ርብርብ አናሳ መሆን ያሳስባል፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት የአገሪቱ ዋነኛ ራስ ምታት ከሆነበት በርካታ ምክንቶች መካከል የተመጣጠነ የንግድ ሚዛን መታጣቱ ከሆነ ደግሞ ለአሰስ ገሰሱ መግዣ የውጭ ምንዛሪ መፈቀድ ፈጽሞ አግባብ አይሆንም፡፡

የብር የመግዛት አቅም እየተዳከመ በሄደ ቁጥር በውጭ ሸቀጣ ሸቀጦች የተሞላው ገበያ ዋጋም በዚያው ልክ እያደገ ለዋጋ መናር ምክንያት መሆኑም በግልጽ እየታየ ነውና እንዲህ ያለውን አካሄድ መግታት ካልተቻለ የዋጋ ንረቱን በቀላሉ ለመቆጣጠር ከባድ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ተፅዕኖዎች ገበያ ውስጥ የሚታየው ንረት ከዚህም በላይ እንዳይሻገር፣ እንዲሁም ለሆነውም ላልሆነውም የውጭ ምርት የውጭ ምንዛሪ እያወጡ መቀጠል ስለማይቻል መንግሥት በቆራጥ ውሳኔ ቢያንስ በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ አንዳንድ ምርቶችን ከውጭ እንዳይገቡ በሕግ ማስቆም አስገዳጅ ሊሆን ይገባል፡፡ የምናስገባቸውን ዕቃዎች መመጠን ከምንችልባቸው ዘዴዎች አንዱም ይህ ነው፡፡

ዛሬ ወደ አገር የሚገቡ አንዳንድ ምርቶች በዚህ ወቅት ለዚህች አገር ዶላር እየወጣበት መምጣት የነበረባቸው ናቸውን? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳም ነው፡፡ በእርግጥ አገሪቱ ካለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንፃር ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የሚፈቅዱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው ቅደም ተከተል መሠረት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ምርቶች ቀድመው የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ በማድረግ ነው፡፡

የኢትዮጵያን የወጪና የገቢ ንግድ ጉድለት ለማጥበብ በዋናነት የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ማሳደግ ቀዳሚው መፍትሔ ቢሆንም፣ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ግን ለገቢ ንግድ የሚፈቀድ የውጭ ምንዛሪ በቅደም ተከተል እንዲሠራ ማድረግ ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ አንገብጋቢ ያልሆኑ እንዲሁም በቀላሉ በአገር ውስጥ ምርት ሊተኩ የሚችሉ ምርቶች ፈፅሞ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ ለዘለቄታውም ጠቃሚ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ምርት እንዲበረታታም ያስችላል፡፡ ተወዳዳሪ አምራቾችን ማፍራት የሚቻልበት ዕድል መፍጠሩን መዘንጋትም የለበትምን፡፡

ካለንበት ችግር አንፃር የቅንጦት ዕቃዎችንም በተመሳሳይ መንገድ እንዳይገቡ መከልከል የግድ ይላል፡፡ ከዚህ ላይ የቅንጦትና ተያያዥ ዕቃዎች ከመከልከል እንዲገቡ በመፍቀድ ከፍተኛ ቀረጥ እንዲጣልባቸው ማድረግ ጠቃሚ ነው ሊባል ቢችልም ይህ አመለካከት የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳይውል እጥረቱም እንዲፈጠር ያደርጋልና እዚህ አካባቢ ያለው አሠራርም መቃኘት አለበት፡፡

ገደብ በራሱ እንደ መፍትሔ ላይወሰድ ቢችልም፣ ኢኮኖሚውን ለማዳን ሲባል መሻሻሎች እስኪመጡ ወሳኝ ከሚባሉ ምርቶች ሌላ ሌላውን ማቆም ግድ ይላል፡፡

የገቢ ንግድን እንዲህ መገደብ የራሱ የሆነ ችግር እንዳለው ቢታመንም፣ እየገዘፈ የመጣውን ችግራችንን ላለማባባስ ልጓም አድርጎ አቅምን ማጠንከር ተገቢ ነው፡፡ ዛሬ በቆላ ስንዴ ምርት የተጀመረው ዓይነት ዕርምጃ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ብቻ ሳይሆን በገፍ የሚገቡትን እንደ ፓስታ፣ ሞኮሮኒ የተለያዩ ብስኩቶችና የስንዴ ዱቄትና ሌሎች ምርቶችንም ማስቀረት የሚቻልበት ዕድል ይፈጥራል፡፡

አልባሳትና ጫማዎችም እንዲሁ በአገር ምርት ቢተኩ ምንም የሚመጣ ችግር የለም፡፡ የታሸጉ ፍራፍሬ ጭማቂዎችና የመሳሰሉትንም ከማስመጣት እዚሁ እንዲመረት ግዳጅ በመጣል ዜጎች በአገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀሙ ማበረታታት ጭምር ያስፈልጋል፡፡ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠርና የአገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ልምድን ለማዳበርም ጠንከር ማለት ያስፈልጋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወጪ የምታወጣባቸውን የገቢ ንግድ ምርቶች በአግባቡና በጥንቃቄ መጠቀም የግድ የሚለን ወቅት ላይ ነን፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ከተዝናና ሕይወት መለስ ማለት ሁሉ ይጠይቃል፡፡ ዘለዓለም ከመቸገር ለተወሰነ ጊዜ ተቸግሮ በውጭ ምንዛሪ የሚመጡ ዕቃዎች ላይ ያለንን ጥገኝነት መቀነስ፣ በቁጠባ መጠቀም ያስፈልገናል፡፡ ለምሳሌ ነዳጅ ትልቁን የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ የሚባላ ነው፡፡ ስለዚህ ነዳጅ በቁጠባ የመጠቀም ባህል ማዳበር የግድ ነው፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በጥንቃቄ መጠቀም ሌላው መላ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የተሽከርካሪ አደጋን መቀነስ በራሱ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ ቀላል አይደለም፡፡፡፡ 

በተለይ በተለይ አብዛኛው ዜጋ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን በበቂ ለማቅረብ በአገር ውስጥ በምግብ ራስን ለመቻል በሚያስችል ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ፣ አሁን ላይ ላያስፈልጉን የሚችሉ የውጭ ምርቶችን ለመግዛት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ግብርናውን ለማሳደግ ለሚያስፈልጉ ግብዓቶች ማዋል ያስፈልጋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የአገር ውስጥ ምርትን መግዛት ልምዱን ከታች ጀምሮ በማስተማር እያጠናከሩ መሄድ ካልተቻለ ያለንበት ችግር የበለጠ እየሆነ ስለሚሄድ አገራዊ ምርትን እናሳድግ፡፡ በአገር ምርት መጠቀም እንውደድ፡፡    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት