Sunday, June 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዓይነቶች  የተሠሩበት ንጥረ ነገርና ያሉበት ደረጃ አሁናዊ ሁኔታ

በታደሰ ኃይሌ ፈረጃ (ዶ/ር)

ክትባቶች ሁሉንም የምርምርና የሙከራ ሒደት አልፈው ወደ ኅብረተሰቡ ከመድረሳቸው በፊት የዓመታት ጥናትና ምርምርን ይጠይቃሉ። ነገር ግን የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ በኋላ የቫይረሱን አደገኛነትና እያስከተለው ያለው አስከፊ ጉዳት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ በ2020 ሳይንቲስቶች ደኅንነታቸው የተጠበቀና የመከላከል አቅማቸው አመርቂ የሆኑ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን በአጭር ጊዜ ለማምረት ውድድር ጀመሩ። ተመራማሪዎች በአሁኑ ጊዜ በሰዎች ላይ በተደረገ ክሊኒካዊ ሙከራ 114 ክትባቶችን እየሞከሩ ሲሆን፣ 48 ደግሞ የመጨረሻው የሙከራ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ከ75 በላይ ቅድመ ክሊኒካዊ ክትባቶች በእንስሳት ላይ በንቃት እየተመረመሩ ነው፡፡

አንድን  አዲስ  ክትባት  ለማምረት  መደረግና  ማለፍ  የሚገባቸው  ሒደቶች

በአጠቃላይ አንድ አዲስ ክትባት ሙሉ ለሙሉ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን አምስት የጥናትና ምርምር ሒደቶችን ማለፍና በሒደቶቹም የተገኙት ሙሉ መረጃዎችን መቅረብ አለበት።

ቅድመ ምርመራ (ፕሪ ክሊኒካል ቴስቲንግ)ሳይንቲስቶች በሴሎች ላይ አዲስ ክትባት ከፈተኑ በኋላ የበሽታ መከላከያ አቅም እንደሚፈጥር ለማየት እንደ አይጥ ወይም ጦጣ ላሉ እንስሳት ይሰጣሉ።

የመጀመርያ ሒደት የጥንቃቄ ሙከራዎች የዚህ ሒደት ጥቅም ተመራማሪዎቹን ስለክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳት ለማጥናት፣ የሚወሰድበትን መጠን ለመወሰን እንዲሁም የሰውነትን በሽታ የመከላከል ሥርዓት የሚያነቃቃ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው። ጥናቱንም የሚካሄደው ክትባቱን ጤነኛና ፈቃደኛ ለሆኑ ጥቂት ሰዎች በመስጠት ነው።

ሁለተኛው ሒደት የተስፋፋ ሙከራዎች ሳይንቲስቶች ክትባቱ በእነሱ ውስጥ በተለየ መንገድ እንደሚሠራ ለማየት በመቶዎች ለሚቆጠሩ እንደ ሕፃናትና አረጋውያን በቡድን ለተከፋፈሉ ሰዎች ክትባቱን ይሰጣሉ። እነዚህ ሙከራዎች የክትባቱን ደኅንነት የበለጠ ይፈትሹታል።

በዚህ ሁለተኛ ሒደት ላይ ሆነው በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አገሮች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ የተሰጣቸው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዓይነቶች በጥቂቱ

ፕሮቪደንስ ቴራፒዩቲክስ (Providence Therapeutics)፡- በካናዳ የምርምር ተቋም ጥናት ላይ ያለው ጂንን መሠረት ያደረገ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ከነሐሴ 2021 ጀምሮ የሁለተኛው ሒደት ጥናት ላይ ይገኛል። ተቋሙም በህንድ ከሚገኘው ባዮሎጂካል ኢ (Biological E) ከሚባል ክትባት አምራች ድርጅት ጋር በጥምረት ለመሥራት ከስምምነት ደርሷል።

ቫክሳር (Vaxart)፡- የፈረንሣይ ሳን ፍራንሲስኮ የተባለ ኩባንያ (የቻይናው ካንሲኖባዮ ቫክሲን እና የሩሲያው ስፑቱኒክ የተባሉ ክትባቶች ከተሠሩበት ንጥረ ነገሮች ጋር ተመሳሳይ) ኤዲ5 (Ad5) የተባለ የኮሮና ቫይረስ በ2021 ግንቦት አካባቢ ጀመረ።

ሶቤራና ፕላስ (Soberana Plus) ለአስቸኳይ ጊዜ በሚል በኩባ ለኅብረተሰቡ እየተሰጠ ያለው ክትባት ሲሆን ጥናቱም በፊንላይ ቫክሲን ኢንስቲትዩት (Finlay Vaccine Institute) እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ሦስተኛው ሒደት የውጤታማ ሙከራዎች ሳይንቲስቶች ክትባቱንና ከክትባቱ ጋር ተመሳሳይነት የሌለው ንጥረ ነገር/ፕላሴቦ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ይሰጣሉ። ክትባቱን የተቀበሉ ሰዎች ክትባቱን ካልተቀበሉ ሰዎች (ፕላሴቦ ከተቀበሉ) ሲነፃፀር ምን ያህሉ በቫይረሱ እንደተያዙ ለማየት ይጠብቃሉ። እነዚህ ሙከራዎች ክትባቱ ከኮሮና ቫይረስ የሚከላከል ከሆነ፣ የውጤታማነት መጠን ተብሎ የሚታወቀውን ይለካሉ። የዚህ ሒደት ሙከራዎች በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ያልተለመዱ የጎንዮሽ ጉዳቶች ማስረጃዎችን ለማየትና ለመሰብስብ ይረዳል።

በዚህ ሒደት ላይ ሆነው በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አገሮች ጥቅም ላይ እንዲውሉ  ፈቃድ  የተሰጣቸው  የኮሮና  ቫይረስ  ክትባት  ዓይነቶች፡-

ፋይዘር ኤንድ ባዮንቴክ (Pfizer and BioNTech)፡- እ.ኤ.አ. በኅዳር 9 2020 የኒውዮርኩ ፋይዘርና የጀርመኑ ባዮ ንቴክ ለመጀመርያ ጊዜ 90 በመቶ ውጤታማ የሆነ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ማምረት መጀመራቸውን አሳወቁ። ከሐምሌ 23 ቀን 2021 ዓ.ም. ጀምሮ በአሜሪካ የመድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣን ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በላይ ለሆኑ ኅብረተሰብ ሁሉ እንዲሰጥ ፈቃድ አገኘ። እ.ኤ.አ. ከግንቦት 10 ቀን 2021 ጀምሮ ክትባቱን ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች ቀጥሎም ከአምስት ዓመት በታች አንዲሰጥ አሜሪካ ጨምሮ በብዙ አገሮች ፈቃድ አገኘ።

ስፑትኒክ ቪ (Sputnik V)፡- የሩሲያ ጤና ሚኒስቴር አካል የሆነው ጋማለያ ሪሰርች ኢንስቲትዩት 91.6 በመቶ ውጤታማ የሆነ ስፑትኒክ ቪ  የተሰኘ የኮሮና ክትባት 2020 ማለቂያ ላይ አምርቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል ከሩሲያ መንግሥት ፈቃድ አገኘ።

ካንሲኖ ባዮሎጆክስ (CanSino Biologics)፡- አንድ ጊዜ ብቻ የሚወሰድ እስካሁን ከ40,000 እስከ 50,000 ስዎች የተከተቡት በነሐሴ 2020 ሦስተኛ ሒደት የጀመረና በቻይና እየተመረተ ያለ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ነው፡፡ የምርምር ግኝቱ እንደሚያመለክተው፣ ይህ ክትባት ለኮሮና ቫይረስ ያለው ውጤታማነት 57.5 በመቶ ሲሆን ለሌሎች ሥር ለሰደዱ የሕመም ዓይነቶች ያለው ውጤታማነት ደግሞ 91.7 በመቶ ነው።

ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን (Johnson & Johnson’s vaccine)፡- በታኅሣሥ 27 ቀን 2021 በአሜሪካ የመድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣን ለአስቸኳይ ጊዜ እንዲሰጥ በሚል ፈቃድ ያገኘው በአሜሪካ ተመራማሪዎች የተገኘ አንድ ጊዜ ብቻ የሚወሰድ የክትባት ዓይነት ነው፡፡ ይህ ክትባት አገራችንም ጨምሮ በብዙ አገሮች እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ሲኖቫኽ (Sinovac)፡- በቻይና የግል ኩባንያ የተገኘ እስከ ነሐሴ 2021 ድረስ ከቢሊዮን በላይ ተመርቶ ለዓለም እየተሠራጨ የሚገኝ የክትባት ዓይነት ነው።

ሲኖፋርም (Sinopharm)፡- ኡሃን ኢንስቲትዩት ኦፍ ባዮሎጂካል ፕሮዳክት እና በቤጂንግ ኢንስቲትዩት ቫክሲን በጥምረት እየተመረተ ያለ 72.8 በመቶ ውጤታማ የሆነ የክትባት ዓይነት ነው።

ማፅደቅ (APPROVAL)፡- ተቆጣጣሪዎች ሙሉውን የሙከራ ውጤቶችንና የክትባት ማምረት ዕቅዶችን ይገመግማሉ፣ ሙሉ ፍቃድ እንዲሰጥ ይወስናሉ።

የተጣመሩ ደረጃዎች፡- የክትባት ሒደት ለማፋጠን የመጀመርያ ሒደት ከሁለተኛው ሒደት፣ የሁለተኛው ሒደት ከሦስተኛው ሒደት በማጣመር የሚሠራ የምርምር ሒደት ነው።

የምርምር ሒደት ሁለትና ሦስት አንድ ላይ ተጣምረው እየተጠኑ ያሉ የክትባት ዓይነቶች፡-

አስትራዜኒካ (AstraZenica)፡- በህንድና በብራዚል ሙሉ ፈቃድ ያገኘ፣ በብዙ አገሮች ደግሞ ለአስቸኳይ ጊዜ በሚል ፈቃድ የተሰጠው።

ዳይቺ ሳንክዮ (Daiichi Sankyo)፡- በጃፓን ተመራማሪዎች እየተጠና ያለ ክትባት ሲሆን፣ የተጣመረው የሙከራ ሒደቱንም  እ.ኤ.አ. ኅዳር 28/2021 ተጀመረ።

 ብሪላይፍ (Brilife)፡- በእስራኤል፣ በዩክሬን በጆርጂያና በአሜሪካ ተመራማሪዎች በጥምረት እየተጠና ያለ ክትባት ሲሆን፣ የተጣመረው የሙከራ ሒደቱንም እ.ኤ.አ. ሐምሌ 2021 ተጀመረ።

ሂፕራ (HIPRA)፡- በእንስሳት ጤንነት ላይ ትኩረት ያደረገው ሂፕራ የተባለው የስፔን የምርምር ድርጅት በፕሮቲን ላይ የተመሠረተ ሂፕራ የተባለ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ላይ የሙከራ ምርምር እያካሄደ ይገኛል፡፡ ድርጅቱም በ2022 መጨረሻ ከ400 ሚሊዮን በላይ ክትባቶችን አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ ይገኛል። የስፔን የጤና ቢሮ ከጥር 1 ቀን 2022 ጀምሮ ወደ ሒደት ሦስት እንዲያልፍ ፈቃድ ሰጥቶታል።

ለአፍታ የቆመ ወይም የተተወ፡- መርማሪዎች በበጎ ፈቃደኞች ላይ አሳሳቢ ምልክቶችን ካዩ፣ ክትባቱ በሽታን የመከላከል ብቃቱ ውጤታማ እንዳልሆነ የሚያሳይ ከሆነ ሙከራውን ለአፍታ ወይም ሙሉ ለሙሉ ማቆም ይችላሉ።

ቅድመ ወይም የተገደበ ይሁንታ፡- ብዙ አገሮች ደኅንነታቸው የተጠበቀና ውጤታማ መሆናቸውን በሚያሳዩ የመጀመርያ ማስረጃዎች ላይ በመመርኮዝ ለክትባት የድንገተኛ ጊዜ ፈቃዶችን የመስጠት ሒደቶች አሏቸው። በተጨማሪም  አንዳንድ አገሮች ዝርዝር የደረጃ ሦስት የሙከራ መረጃ ይፋ ከመደረጉ በፊት ክትባቶችን መስጠቱ ጀመሩ። ማንኛውም ክትባት ለሰዎች ከመሰጠት በፊት በእያንዳንዱ ሒደት ማለፍና መፈተሽ እንዳለበት ሒደቶቹም መዝለል ከባድ አደጋዎች እንዳሉ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

የኮቪድ-19 ቫይረስ ክትባቶች የተሠሩበት ንጥረ ነገር አሁናዊ ሁኔታ፡- በአሁኑ ወቅት የኮቪድ ክትባትንም ጨምሮ ማንኛዎችንም የክትባት ዓይነቶች በይዞታ ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት ንጥረ ነገሮች አንዱን እንደ መነሻ ቀመር (Precursor) በመጠቀም ይሠራል።

የጂን ክትባቶች (Genetic Vaccines)፡- በሽታ መቋቋም ምላሽን ለማነሳሳት አንድ ወይም ከዚያ በላይ የኮሮና ቫይረስን ጂኖች (የቫይረሱን ፕሮቲኖችን መፍጠር የሚችሉ) ወደ ሴሎቻችን የሚያደርሱ አዲስ የክትባትና የበሽታ መከላከያ ዘዴዎች ናቸው። የዚህ አካሄድ ዓላማ ከዚህ በፊት የሚታወቁ ክትባቶችና ሕክምናዎች ያልሠሩባቸውን በሽታዎች ላይ የመከላከል አቅምን መፍጠር፣ ክትባቶችን ማሻሻልና ሥር የሰደዱ በሽታዎችን ማከም ነው። የጂን ክትባቶች ወደ ሰውነት ሲገቡ ሰውነታችን ለጂኑ ፀረ እንግዳ አካላትን (Antibodies) በማመንጨት የተወሰኑ ሴሉላር ምላሾችን ይፈጥራሉ። በተጨማሪም ፀረ እንግዳ አካላትን የሚያመነጩ ልዩ ፕሮቲኖች ከጂኖቹ ብቻ በማቅረብ ሌሎች የክትባት ዓይነቶች ሊያደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ያስቀራሉ።

ይህን ንጥረ ነገር በመጠቀም በመሠራት ላይ ያሉ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዓይነቶች በጥቂቱ፡- ፋይዘር፣ ባዮንቴክ፣ ሞዴርና፣ ጄኔክሲን

የቫይራል ቬክተር ክትባቶች፡- ጠቃሚ መመርያዎችን ለሴሎቻችን ለማድረስ ዒላማ ከተደረገው ቫይረስ የተዳቀለ የቫይረስ ሥሪት ይጠቀማሉ። የተዳቀለው የቫይረሱ ሥሪት ቬክተር ቫይረስ ይባላል።

የቫይረስ ቬክተር ክትባቶች እንዴት እንደሚሠሩ፡- በመጀመሪያ የኮቪድ-19 ቫይረስ ቬክተር ክትባት በላይኛው ክንድ ጡንቻ ላይ ይሰጣሉ። የኮቪድ-19 ቬክተር ቫይረስ ኮቪድ-19ን የሚያመጣው ቫይረስ ሳይሆን የተዳቀለና ጉዳት የሌለው ቫይረስ ነው። ቬክተር ቫይረሱ ወደ ጡንቻ ሴሎች ከገባ በኋላ የሴሎች ማሽነሪዎችን ምንም ጉዳት የሌለው ንጥል ፕሮቲን (Spike Protein) የሚባለውን ቁራጭ ለማምረት እንደ መነሻነት ይጠቀሙበታል። ንጥል ፕሮቲን (Spike Protein) ኮቪድ-19ን በሚያመጣው ቫይረሱ ላይ ይገኛል።

በመቀጠል የተመረተው ንጥል ፕሮቲን በጡንቻ ሴሎቹ በውጨኛው አካላቸው እንዲቀመጥ ያደርጋሉ። በዚህም የተነሳ የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ሥርዓት፣ በጡንቻ ሴሎች አካል ላይ ያለው ንጥል ፕሮቲን፣ በጡንቻ ሴሎች ላይ ከተፈጥሯዊ ቀመር ዉጪ የሆነ አዲስ ፕሮቲን እንደሆነ ይገነዘቡና እንደ ባዕድ ነገር ይቆጥሩታል። ይህ በሽታን የመከላከል ሥርዓታችን ፀረ ባዕድ አካላትን እንዲያመርትና ሌሎች የበሽታ ተከላካይ ህዋሳትን በማንቀሳቀስ ኢንፌክሽን ነው ብሎ የገመተውን ለመከላከል ያነሳሳል።

ይህ እንግዲህ ሰውነታችን ከዚህ በኋላ ለኮቪድ-19 ቫይረስ ቢጋለጥም በሽታን የመከላከል ሥርዓታችን አዘጋጅቶ ያስቀመጣቸውን ፀረ ባዕድ አካላትን ቫይረሱን በመዋጋት የሕመም ስሜት እንዳይሰማን ያደርጋሉ። ጥቅሙ በኮቪድ-19 መታመም የሚያስከትለውን አስከፊ መዘዝ አደጋ ላይ ሳያደርሰን ይህንን ጥበቃ ከክትባት ማግኘታችን ነው። ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ የሚከሰት ማንኛውም ጊዜያዊ ተጓዳኝ ስሜቶች የሒደቱ ተፈጥሯዊ አካልና ክትባቱ እየሠራ መሆኑን የሚያመለክት ስለሆነ ብዙም መሥጋት አስፈላጊ አይደለም።

ስለ  ኮቪድ-19  ቫይረስ  ሴክተር  ክትባቶች እውነታዎች

የኮቪድ-19 ቫይረስ ቬክተር ክትባቶች ምንም ዓይነት በኮቪድ-19 ወይም በሌሎች ቫይረሶች ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን አያስከትሉም። በቫይራል ቬክተር የሚተላለፈው የጄኔቲክ ቁሳቁስ በምንም መልኩ ወደ ሰው ተፈጥሯዊ ቀመር (ዴኤንኤ) ውስጥ አይዋሃድም።

ሳይንቲስቶች እንደሚገምቱት የንጥል ፕሮቲን፣ ልክ እንደሌሎች ሰውነታችን እንደሚፈጥራቸው ፕሮቲኖች፣ በሰውነት ውስጥ እስከ ጥቂት ሳምንታት ብቻ ይቆያሉ።

ይህን አሠራር በመጠቀም በመሠራት ላይ ያሉ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዓይነቶች፦ ስፑትኒክ ቪ፣ አስትራዜንካ፣ ካንሲኖ፣ ባዮሎጂክስ፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ (Johnson & Johnson’s) ብሪላይፍ ናቸው፡፡

በፕሮቲን ላይ የተመሠረቱ ክትባቶች፡-  የኮሮና ቫይረስ ፕሮቲኖችን የያዙ ግን ምንም ዓይነት የቫይረሱ የዘረመል ቁሳቁስ (Genetic Material) የሌላቸው ክትባቶች ናቸው። አንዳንድ ክትባቶች የቫይረሱ ሙሉ ፕሮቲኖችን፣ አንዳንዶቹ የቫይረሱ ቁርጥራጭ ፕሮቲኖችን ይይዛሉ። ብዙዎቹ ክትባቶች እነዚህ ፕሮቲኖች በናኖፓርቲክልስ (Nanoparticles) ውስጥ ይታሸጋሉ። ፕሮቲንን መሠረት ያደረጉ ክትባቶች በሽታን የመከላከል አቅምን ለማዳበር በሽታ የመከላከል ሥርዓቱ ሊገነዘበው የሚገባውን የቫይረሱን የተወሰነ ክፍል (ፕሮቲን) ይጠቀማሉ። ተግባራቸው የበሽታ መከላከያ ሥርዓቱ ቫይረሱን በፕሮቲኑ አማካይነት እንዲያውቅ ማድረግና ከተያዙ እሱን እንዲዋጋ ማድረግ ነው።

በፕሮቲን ላይ የተመሠረተ ክትባት ሲወስዱ በሰውነት ውስጥ ምን ይከሰታል?

ክትባቱን ሲወስዱ ሰውነትዎ ከቫይረስ ፕሮቲን ጋር ይገናኛል፣ የሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓት የውጭውን ፕሮቲን በመለየት ፀረ እንግዳ አካላትንና የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳትን ያመነጫል፣ ሰውነት ፕሮቲኑን ያስወግዳል። ክዚህ በኋላ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ የበሽታ መከላከል ሥርዓትን ቫይረሱን እንዴት ከሰውነት ማጥፋት እንደሚቻል ያስታውላል።

ይህን አሠራር በመጠቀም በመሥራት ላይ ያሉ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዓይነቶች ኖቫቫክስ፣ ሂፕራ፣ ሶቤራና.2፣ ኮቫ-ፓርስ ራዚ ናቸው፡፡

ያልተነቃቁ ወይም የተዳከሙ የኮሮና ቫይረስን በመጠቀም የሚሠሩ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች፡- የተዳከመውን ወይም ያልተነቃቃውን ሙሉ የሆነው የኮሮና ቫይረስ አካል በመጠቀም በሰውነታችን በሽታን የመከላከል አቅም መፍጠርና ማነሳሳትን ነው።

የተዳከመ የቫይረስ ዓይነት (Live Attenuated Vaccines)፣ ሊያድግና ሊባዛ ይችላል፣ ነገር ግን ሕመም አያስከትልም፡፡

ያልተነቃቁ የቫይረስ ዓይነት (Inactivated Vaccines)፣ በሙቀት፣ በኬሚካል ወይም በጨረር የዘረመል ቁሳቁስ አካል (Genetic Material) የተበላሹ ቫይረሶችን ይይዛሉ፡፡ ስለዚህ ሴሎችን ሊበክሉና ሊባዙ አይችሉም፡፡

ሁለቱም የተሞከሩና ጥቅም ላይ የዋሉ የክትባት ግኝት ሥልቶች ናቸውለአብነትም የቢጫ ወባና የኩፍኝ ክትባቶች (በቀጥታ የተዳከሙ ቫይረስ ክትባቶችየኢንፍሉዌንዛና የሄፓታይተስ (ያልተነቃቁ ቫይረስ ክትባቶች) መጥቀስ ይቻላል። የተዳከሙ ባክቴሪያ በመጠቀም የተሠሩ ክትባቶችም አሉ፣ ለምሳሌ የቢሲጂ ክትባት ለሳንባ ነቀርሳ (BCG Vaccine for Tuberculosis)።

ይህን አሠራር በመጠቀም በመሠራት ላይ ያሉ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዓይነቶች፦ ሲኖቫክ፣ ሲኖፋርም፣ ቢቢአይቢፒ-ኮርቪ፣ ኮቫክሲን፣ ሻፋ፣ ፋርምድ ፓርስ ናቸው፡፡

ይህን ጥናታዊ ጽሑፍ ሲዘጋጅ በዋቢነት የተጠቀምንባቸው የመረጃ ምንጮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ (ሀ) The New York Times- Corona Virus Tracker (ለ) WHO – The different types of COVID-19 vaccines (ሐ) Gavi the vaccine alliance – COVID-19 vaccine types in development፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ረዳት ፕሮፌሰር ታደሰ ኃይሌ ፈረጃ (/ር) በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በፋርማሲ ትምህርት ክፍል በመምህርነትና በምርምር ዘርፍ እያገለገሉ ሲሆን፣ በፋርማሲ ዘርፍ ከ26 በላይ የምርምር ውጤቶችን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች አሳትመዋል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles