Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለሕፃናት የሚያገለግለው ፅኑ ሕሙማን ክፍል

ለሕፃናት የሚያገለግለው ፅኑ ሕሙማን ክፍል

ቀን:

በሕፃናት ሕክምና ሥርዓት ውስጥ በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙ አብዛኛዎቹ የመንግሥትና የግል ሆስፒታሎች ውስጥ የሚታየው አንዱ ችግር የሕፃናት የፅኑ ሕሙማን ክፍል አለመኖር ነው፡፡ ይህም ሕፃናት በዚህ ሕክምና መዳን እየቻሉ አገልግሎቱን በማጣት ብቻ ሕፃናት እንዲሞቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን የሕፃናት ድንገተኛ ፅኑና የልብ ሕሙማን ሰብ ስፔሻሊስት ይናገራሉ፡፡

የሃሌ ሉያ የግል አጠቃላይ ሆስፒታል የሕፃናት ፅኑ ሕሙማን ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት በሆነበት ሥነ ሥርዓት ላይ ሰብ ስፔሻሊስቷ ትዕግሥት ባጫ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ሕፃናትን በአብዛኛው ለሞት የሚዳርገው የሳምባ ምች ሲሆን፣ በሁሉም ሆስፒታሎች የሕፃናት ፅኑ ሕሙማን ክፍል ቢኖር ብዙዎቹን በሽታው ከሚያስከትለው ሞት መታደግ ይቻል ነበር፡፡

ከኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል 50 ከመቶ ያህሉ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ በአገሪቱ ከሚገኙ 78 የመንግሥትና የግል ሆስፒታሎች ውስጥ የሕፃናት ፅኑ ሕሙማን ክፍል ያላቸው ከሰባት እንደማይበልጥና ይህም ለሕፃናት ልዩ ትኩረት አለመሰጠቱን እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕፃናት ሐኪሞች ማኅበር ዳይሬክተር አቶ ቦጋለ ወርቁ፣ ‹‹በገጠርና በከተማ ከሚገኙ ትልልቅና ትንንሽ ሆስፒታሎች መካከል አብዛኛዎቹ የሕፃናት ፅኑ ሕሙማን ክፍል የላቸውም፡፡ የማቋቋም ሥራም በቅርቡ ነው የተጀመረው፤›› ብለዋል፡፡

ከአምስት ዓመት በታች የሆኑና የሳምባ ምች የያዛቸው ሕፃናት ተገቢውን ሕክምና ለማግኘት በፍጥነት ሆስፒታል ቢደርሱም፣ የሕፃናት ፅኑ ሕሙማን ክፍል ባለመኖሩ የተነሳ ወዲያውኑ ለሕልፈተ ሕይወት እንደሚዳረጉ፣ ይህም ሁኔታ ልብ እንደሚሰብርም አክለዋል፡፡

ሃሌ ሉያ የግል አጠቃላይ ሆስፒታል የሕፃናት ፅኑ ሕሙማን ክፍል ማቋቋሙ ለሕፃናት ትልቅ ተስፋ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የጨቅላ ሕፃናትና የሕፃናት ክፍል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ገበየሁ፣ የግሉ ጤና ዘርፍ እንደዚህ ዓይነቱን የሕክምና ክፍል በማቋቋም ኅብረተሰቡን ለማገልገልና ተደራሽነቱንም ለማስፋት እያደረገ ያለው ጥረት አበረታችና አርዓያም እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ በርካታ ጨቅላ ሕፃናትና ሕፃናት በየቀኑ፣ በየወሩና በየዓመቱ በሕክምና ሊድን ወይም መከላከል በሚቻል በበሽታ ለሕልፈተ ሕይወት እንደሚዳረጉ ገልጸው፣ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚይዙትን ሕፃናት ከሞት መታደግ የሚያስችል ጠንከራ የሕክምና ሥራ መከናወን እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ጤና ሚኒስቴርም የሕፃናትንና በአጠቃላይ የኅብረተሰቡን ጤንነት በማሻሻል ረገድ የበኩሉን ዕገዛና አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ የታመነበትን ሁለተኛውን የጤና ዘርፍ ፕሮግራም ከግብ ለማድረስ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በዚህ መልኩ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ፣ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራቸውና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ 80 ልዩ ልዩ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን ገዝቶ በ80 የመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ በአገልግሎት ላይ እንዲውሉ ማድረጉን የፕሮግራም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ አጋርነት ለማጠናከር የሚያስችል መመርያ መዘጋጀቱንና በጨቅላ ሕፃናት የጤና ፕሮግራም ላይ ብሔራዊ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ለመግባት ሙከራ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የሃሌ ሉያ ጠቅላላ ሆስፒታል ባለቤትና ቺፍ ክሊኒካል ኦፊሰር ጌታቸው አደራዬ (ፕሮፌሰር)፣ የግሉ ጤና ዘርፍ እጅግ በጣም ደካማና በሚፈለገው መጠን ያልተሳተፉ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህም የደርግ ሥርዓት ይከተለውና ያራምደው የነበረው የሶሻሊስት ሥርዓት የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ እንዳያድግና ቀጭጮ እንዲቀር ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን ዘርፉን ለማሻሻልና ለማሳደግ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፣ አሁንም ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቀው ከጌታቸው (ፕሮፌሰር) ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ይህ ማዕከል በሕፃናት የሠለጠኑ ሰባት ነርሶች፣ ጠቅላላ ስፔሻሊስትና ሰብ ስፔሻሊስቶች እንዲሁም የልብ ሐኪሞችና አማካሪዎች እንዳሉት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የየራሳቸው ልዩ ልዩ የመገልገያ ቁሳቁሶችና ማሞቂያ ያላቸው አምስት አልጋዎችን እንዳካተተ የሆስፒታሉ የሕፃናት ስፔሻሊስት ራቢያ ጀማል (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ሆስፒታሉ ለሕፃናት ልብ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ኢሲጂ ማሽኖችን በመንግሥት ለሚተዳደሩ አራት ሆስፒታሎች በነፃ አበርክቷል፡፡ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት መርህ መሠረት ማሽኖቹ የተበረከቱት ለአለርትና ለዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል፣ ለየካቲት 12 ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅና ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ነው፡፡ ሃሌ ሉያ ጠቅላላ ሆስፒታል ማሽኖቹን ያገኘው በትብብር አብሮ ከሚሠራቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሆኑን የሆስፒታሉ ምክትል ሚዲካል ዳይሬክተር ቃለ አብ ደረጀ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...