Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንን ጨምሮ አምስት የልማት ድርጅቶች አሠራራቸውን የሚቀይር ጥናት ሊደረግላቸው ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ ሥር የሚገኙ አምስት የልማት ድርጅቶች፣ ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ አሠራራቸውን ይቀይራል የተባለለት ጥልቅ የስትራቴጂ ጥናት ሊደረግላቸው ነው፡፡ ጥናቱን የሚያካሂደው ኤምቲአይ ኮንሰልቲንግ የተሰኘ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ሲሆን ስምምነት መፈራረሙ ታውቋል፡፡

በፈረንሣይ ልማት ድርጅት በሚደገፈው ፕሮጀክት፣ የስትራቴጂ ጥናት እንዲደረግላቸው ከተመረጡት የልማት ድርጅቶች ውስጥ በዚህ ዓመት የስንዴ ግዢን እንዲያከናውን ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ይገኝበታል፡፡ በስድስት ወር አፈጻጸሙ ኪሳራ የደረሰበት የኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት አክሲዮን ማኅበር፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንም የስትራቴጂ ጥናቱ አካል ናቸው፡፡

ድርጅቶቹ የተመረጡት ጠቃሚ ዘርፍ ላይ የሚሠሩ በመሆናቸውና ያለባቸው ችግር ተለይቶ ዕገዛ ቢደረግ ውጤታማ መሆን ይችላሉ ተብሎ በመታሰቡ መሆኑን፣ በፈረንሣይ ልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ሪፎርም ቴክኒካል ድጋፍ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አደራጀው ሹመቴ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ ኤምቲአይ ኮንሰልቲንግ የተሰኘው ተቋም፣ አሥር ወራት በሚወስደው የጥናት ሥራ አራት ዋና ዋና ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ የጥናቱ የመጀመሪያ ዕርምጃ  የተመረጡት የልማት ድርጅቶች ያሉበትን ሁኔታ የሚመለከት ጥልቅ ግምገማ ማካሄድ ነው፡፡ በዚህ ግምገማ ድርጅቶቹ የሚሠሩት ውጫዊና ውስጣዊ የሥራ ሁኔታ፣ ያላቸው የንግድ ተወዳዳሪነት፣ የፋይናንስ ሁኔታና የኦፕሬሽን አቅም ይገመገማል፡፡

ከእነዚህ ግምገማዎች በመነሳት በሚሠራው የማመሳከሪያ ሥራም ድርጅቶቹን ከተመሳሳይ አገራዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጋር የማነጻጸር ሥራ እንደሚሠራ አደራጀው (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

በሦስተኛ ደረጃም አማካሪ ድርጅቱ እንደ የንግድ ዕድገት፣ ኮሙኒኬሽንና የሀብት አሰባሰብ ባሉ የተመረጡ ዘርፎች ላይ የስትራቴጂ ቀረፃ ሥራ ካከናወነ በኋላ ስትራቴጂዎቹ መሬት የሚወርዱበት የትግበራ ፍኖተ ካርታ እንደሚያዘጋጅ ተገልጿል፡፡ እነዚህ ሥራዎች አከናውኖ ለማጠናቀቅም አሥር ወር ይወስዳል የሚል ግምት ተቀምጧል፡፡

በፈረንሣይ ልማት ድርጅት ድጋፍ የሚተገበረው ጥልቅ የስትራቴጂ ጥናት፣ ድርጅቱ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ጋር ባደረገው ስምምነት ለሦስት ዓመት የሚተገብረው የሁለት ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት አካል ነው፡፡

አደራጀው (ዶ/ር) ይኼንን ጥልቅ ጥናት የሚያደርገውን ተቋም ለመምረጥ ለአንድ ዓመት ያህል የጨረታ ሒደት መከናወኑን አስታውሰው፣ 18 ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶች የፍላጎት መግለጫቸውን አስገብተው እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል ስድስቱ ተመርጠው ሦስቱ ቴክኒካልና ፋይናንሻል ፕሮፖዛል አቅርበው 80 በመቶ ለቴክኒካል 20 በመቶ ደግሞ ለፋይናንሻል ፕሮፖዛል ቦታ ተሰጥቶት መረጣው መካሄዱን አብራርተዋል፡፡

ፕሮፖዛላቸውን ካቀረቡት ድርጅቶች ውስጥ በቴክኒካል ብቃት ከፍተኛ ውጤትና በፋይናንስ ዝቅተኛ ገንዘብ ያቀረበው ኤምቲአይ ኮንሰልቲንግ የተሰኘውን ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡  

ኤምቲአይ ኮንሰልቲንግ በ50 አገሮች ከ680 በላይ ፕሮጀክቶችን እንዳከናወነ የሚገልጸው ከድርጅቱ የተገኘ መረጃ፣ ፕሮጀክታቸው በድርጅቱ ከተሠራላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ቶዮታ፣ ሂልተንና አሜሪካን ኤክስፕረስ ተጠቅሰዋል፡፡

አማካሪ ድርጅቱ በመጋቢት አጋማሽ ሙሉ የጥናት ቡድኑን ይዞ ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት አደራጀው (ዶ/ር)፣ በተደረገው ስምምነት መሠረት ጥናቱን የሚያከናውኑት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ የሠሩ፣ የአፍሪካና የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚያውቁ እንዲሁም የስትራቴጂ ቀረፃ ላይ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ባካሄደው በሥሩ ያሉት የልማት ድርጅቶች፣ የስድስት ወር አፈጻጸም ግምገማ ጥናት እንዲደረግላቸው ከተመረጡ አምስት ተቋማት ውስጥ የሦስቱን አፈጻጸም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን 176.9 ሚሊዮን እንዲሁም ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ብር 107.4 ሚሊዮን ብር ትርፍ ሲያገኙ የኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት አክሲዮን ማኅበር የ394 ሺሕ ብር ኪሳራ ደርሶበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች