Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበበልግ ወቅት ዝቅተኛ የዝናብ መጠን ስለሚኖር በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ድርቁ እንደሚቀጥል ተነገረ

በበልግ ወቅት ዝቅተኛ የዝናብ መጠን ስለሚኖር በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ድርቁ እንደሚቀጥል ተነገረ

ቀን:

ከየካቲት አጋማሽ እስከ ግንቦት ወር ድረስ በሚቆየው የበልግ ወቅት ዝናብ የሚዘገይና ከመደበኛው በታች ይሆናል የሚል ትንበያ በመኖሩ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የ2014 ዓ.ም. የበልግ ወቅት አገባቡ የዘገየ በመሆኑ፣ የካቲትና መጋቢት ወራት እንደማይዘንብ፣ በሚያዝያና በግንቦት ወራት ደግሞ የዝናብ መጠኑ ከመደበኛው በታች እንደሚሆን ትንበያው ማሳየቱን፣ በኢንስቲትዩቱ የረዥም ጊዜ የአየር ፀባይ ትንበያ ቡድን አስተባባሪ አቶ በቃሉ ታመነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ ምንም እንኳን በሚያዝያና በግንቦት ወራት ከመደበኛው ጋር ተቀራራቢ ዝናብ ቢኖርም፣ በየካቲትና መጋቢት ወራት ዝናብ ስለማይኖር አካባቢዎቹ ካለፈው ዓመት አንስቶ ዝናብ ባለማግኘታቸው የተከሰተው ድርቅ ይቀጥላል የሚል ምልከታ አለ፡፡

ከየካቲት እስከ ግንቦት ባሉት አራት ወራት የሚቆየው የበልግ ወቅት የሶማሌ፣ የኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ለሚካተቱበት የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የዝናብ ድርሻ የሚገኝበት ዋነኛ የዝናብ ጊዜ ነው፡፡ እንደ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ሪፖርት በ2013 ዓ.ም. በነበረው የበልግ ወቅት የበልግ አብቃይ በሆኑት አካባቢዎች ዝናቡ ዘግይቶ በመድረሱ፣ በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ከተስተዋለው አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ በስተቀር፣ በብዙ ቦታዎች በአብዛኛው ደረቃማ የአየር ሁኔታ ተስተውሏል፡፡

- Advertisement -

እነዚህ አካባቢዎች የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ ስላልሆኑ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ከመስከረም አጋማሽ እስከ ታኅሳስ ወራት የሚቆየው የበጋ ወቅት ነው፡፡ ባለፈው የበጋ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ባሌ፣ አርሲ፣ ጉጂና ቦረና ዞኖች፣ እንዲሁም የሶማሌ ክልል ደቡባዊ አጋማሽ ክፍል ያገኙት የዝናብ መጠን ማግኘት ከነበረባቸው በታች ነው፡፡

በዚህም ምክንያት በሁለቱ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ ቀጥሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአርብቶ አደሮች እንስሳት ሲሞቱ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል፡፡

ነገር ግን አሁን እየገባ ያለውና ለደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ዋነኛ የዝናብ ጊዜ የሆነው የበልግ ወቅት በሁለት ወራት ዘግይቶ ከገባ በኋላ፣ ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚያገኙ ትንበያ ተቀምጧል፡፡ በትንበያው መሠረት በኦሮሚያ ክልል ማዕከላዊ ክፍል በመጀመሪያዎቹ የበልግ ወራት አነስተኛ ዝናብ ሲያገኝ የቦረና፣ጉጂና የባሌ ቆላማ ዞኖች ደግሞ መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ ያገኛሉ፡፡

በሶማሌ ክልልም በተመሳሳይ የሊበን፣ የአፍዴር፣ የሻብሌ፣ የቆራሄ፣ የዶሎና የኖጎበ ዞኖች በአመዛኙ መደበኛና ከመበደኛ በታች ዝናብ አግኝተው የፋፈንና የሲቲ ዞኖች ደግሞ ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ ያገኛሉ የሚል ትንበያ ተቀምጧል፡፡ ዝቅተኛ የሆነው የዝናብ መጠን የደቡብና የሲዳማ ክልሎችንም እንደሚመለከት ተገልጿል፡፡

የረዥም ጊዜ የአየር ፀባይ ትንበያ ቡድን አስተባባሪው አቶ በቃሉ፣ ሁለቱ ክልሎች በ2013 ዓ.ም. በልግና ባለፈው በጋ ማግኘት የሚጠበቅባቸውን የዝናብ መጠን እንዳላገኙ አስታውሰው፣ አሁንም የሚመጣው በልግ አገባቡ ስለሚዘገይና ከመደበኛው በታች የሆነ የዝናብ መጠን ስለሚያስተናግድ ድርቁ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

‹‹በበልግ አጋማሽ ላይ ከመደበኛው በታች ቢዘንብም እንኳን በቂ አይሆንም፣ ዝናቡ በሚዘገይባቸው ሁለት ወራት ላይ ማግኘት የሚገባቸውን ስለማያገኙ የውኃ እጥረቱን ያባብሰዋል፤›› በማለት አስተባባሪው አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም በበልጉ ወቅት የደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ቆላማ የአገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ ሙቀት እንደሚኖር ያመላከተው የኢንስቲትዩቱ ሪፖርት፣ ይህ ሙቀት ከዝናብ እጥረትና መቆራረጥ ጋር በመዳመር ከዕፅዋትና ከአካባቢያው የሚኖረውን ትነት እንደሚያባብሰው ተጠቁሟል፡፡ እንዲሁም የዝናብ እጥረት በሚጠበቅባቸው አካባቢዎች የእርጥበት መቆራረጥና የሙቀት መፈራረቅ መኖሩ፣ ለፀረ ሰብል ተባይና በሽታ መከሰት አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ፣ ከዚህ ቀደም ከሰባት እስከ አምስት ዓመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ይከሰት የነበረው ድርቅ አሁን ድግግሞሹ እያጠረ መሆኑን ተናግረው፣ ይህም ከዓለም  የአየር ንብረት ለውጥ ጋር እንደሚያያዝ አስረድተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ኮሚሽኑ ከሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚያገኘውን መረጃ ለክልሎች እንደሚሰጥ በመግለጽ፣ የቅድመ መከላከል ሥራውን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሚያከናውኑት ክልሎቹ ራሳቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር የሚነፃፀር “በጣም ዘመናዊ” የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት እንደሌለው የተናገሩት አቶ ደበበ፣ ድርቁ ከደረሰ በኋላ ግን ኮሚሽኑ በሁለቱም ክልሎች የተጠየቀውን የምግብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የዝናብ መጠን ከመደበኛ በታች በተተነበየባቸው አካባቢዎች ሊከሰት የሚችለውን  የእርጥበት ችግር ለመቅረፍ ከዝናብ የሚገኘውን ውኃ ልማዳዊ በሆኑ ዘዴዎች ማቆርና በአግባቡ መጠቀም በሪፖርቱ ላይ በምክረ ሐሳብነት ተቀምጧል፡፡ በተጨማሪም ገበሬዎች በአጭር ጊዜ የሚደርሱና የእርጥበት እጥረትን ሊቋቋሙ የሚችሉ ሰብሎችን እንዲዘሩና ከተተነበየው የወቅቱ ዝናብ ዘግይቶ መግባት ጋር ትክክለኛና አስተማማኝ የዘር ጊዜ እንዲከተሉ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ክር ቤት ማክሰኞ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ሦስተኛው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በሶማሊያና በኦሮሚያ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ በሁለት መንገድ ለመፍታት እየተሞከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመጀመርያው መንገድ ዕርዳታ ማቅረብ መሆኑን ያወሱት ዓብይ (ዶ/ር) 750 ሺሕ ኩንታል የዕለት ደራሽ ምግብ፣ 259 ቦቴ ውኃ፣ እንዲሁም የከብት መኖ፣ የሕፃናት ምግብና ክትባት መላኩን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም የሰው ሕይወት እንዳያልፍ ቢደረግም በእንስሳት ላይ ግን ትልቅ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለረዥም ጊዜ መፍትሔ የሚሆነው የውኃ አስተዳደርን ማጎልበትና የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሆነ ከገለጹ በኋላ፣ በቂ ውኃ እንዲኖር በማድረግ አርብቶ አደሮች እንዲያርሱና ከብቶቻቸውን እንዲያረቡ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...