Tuesday, May 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር መስመር የ800 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ያስፈልገዋል ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ3.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ወጥቶበት ላለፉት አራት ዓመታት የማዳበሪያ፣ የሲሚንቶና የብረታ ብረት ምርቶችን እያጓጓዘ የሚገኘው የኢትዮ-ጂቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ባቡር ትራንስፖርት፣ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥ የ800 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልገው ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበሩ ተጨማሪ አምስት የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን ባስጀመረበት፣ እንዲሁም ከምሥረታው አንስቶ ላለፉት አራት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰኞ የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. በፉሪ ለቡ የባቡር ጣቢያ በዳሰሰበት ሴሚናር ነው፡፡

በሴሚናሩ ላይ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ እንዳስታወቁት፣ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ ወደ ሥራ የገባው የሁለቱ እህትማማቾች አገሮች የዘመናዊ ባቡር መስመር ለአገሮቹ የስትራቴጂክ አጋርነት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በተለይም የስታንዳርድ ጌጅ ፕሮጀክቱ የመጀመሪያው አፍሪካዊ የቤልትና ሮድ ኢንሼቲቭ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር አገልግሎት ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ የኢትዮጵያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሲስተም እውነተኛ የመልቲ ሞዳል ባህርይ እያሳየ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ የባቡር አገልግሎቱ ኢትዮጵያ ከምታደርገው አጠቃላይ የዓለም አቀፍ ንግድ 11 በመቶ የሚሆነውን የገበያ ድርሻ ለመሸከም መቻሉን አስረድተዋል፡፡ በተለይም ካለው አነስተኛ የጉዞ ማቋረጫ ቆይታ፣ እንዲሁም ከተወዳዳሪ ዋጋ አኳያ የጭነት ባቡር አገልግሎት በተለይም ለጭነት አስመጪዎች ጥሩ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የባቡር መስመሩ በሚፈለገው አቅሙ ልክ እያገለገለ ነው ለማለት አያስደፍርም ያሉት ሚኒስትሯ፣ በአቅሙ ልክ እንዲሠራ ተከታታይና የማያቋረጥ ድጋፍ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በቅርቡ ባስጠናው ጥናት መሠረት የባቡር መስመሩን አቅም በማሳደግ 12 ጥንድ ባቡሮችን በየቀኑ ለሦስት ዓመታት ቢያሰማራ፣ 10.2 ሚሊዮን ቶን ጭነት በዓመት ውስጥ የማስተናገድ አቅም አለው፡፡

በጥናቱ የተቀመጠው መረጃ እንዲሳካ የአሠራር ሥርዓቱ ሊሰተካከል ይገባል ያሉት ወ/ሮ ዳግማዊት፣ ይህም ማኅበረሰቡና ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉት ቁርጠኝትና የባለቤትነት ስሜት አንደኛው ሲሆን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ተሳቢ የባቡር ግብዓቶችን ለማሟላት፣ የሎጂስቲክስ መሣሪያዎችን ለማደራጀት፣ የጥገና ቁሳቁሶችን ለማደርጀት፣ እንዲሁም ተጨማሪ መሠረተ ልማትን ለማድረግ 800 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ወጪ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

የኢትዮ-ጂቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥላሁን ሳርካ (ኢንጂነር) በሰጡት ማብራሪያ፣ ተቋሙ ከአራት ዓመት በፊት ወደ ሥራ ሲገባ በመጀመሪያው ዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን ጭነት አጓጉዟል፡፡ በየዓመቱ በጭነት መጠን ጭማሪ እያሳየ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለሁለት ሚሊዮን የተጠጋ ጭነት ለማጓጓዝ እንደበቃ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የመጠን ጭማሪው በጥሩ ጎኑ የሚጠቀስ ቢሆንም በቂ ነው ተብሎ የሚወሰድ አይደለም ብለዋል፡፡

የባቡር ትራንስፖርት በየትኛውም ዓለም አትራፊ አይደለም ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ይህም አገልግሎቱ የማኅበራዊ መሠረተ ልማት ስለሆነ ነው፡፡ ‹‹ቻይና፣ ጃፓን፣ ጀርመንና መሰል አገሮች በዘርፉ አትራፊ ሊባሉ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ አትራፊ እንዲሆን ከተፈለገ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማደረግ ግድ ይላል፡፡ ለአብነትም ተቋሙ ባሉት ዋና ዋና የባቡር ጣቢያዎች ላይ የሚገኙ ክፍት መሬቶችን በመንግሥት ፈቃድ ኢንቨስት ቢደረግባቸው  የባቡሩን ወጪ ለመደጎም ያስችላል፡፡ ሆኖም ከትኬት ሽያጭና ከጭነት ገቢ ብቻ ባቡርን ትርፋማ ማድረግ አስቸጋሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተያያዘም የኢትዮ-ጂቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ በሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ከዚህ ቀደም በነበሩት 14 ጣቢያዎች ላይ አምስት ተጨማሪ ጣቢያዎችን በመክፈት የጣቢያዎቹን ቁጥር ወደ 19 ከፍ አድርጓል።

በተከፈቱት አምስት ጣቢያዎች የሚሰጠው አገልግሎት በሳምንት ሁለት ቀን ከፉሪ ለቡ ጣቢያ ተነስቶ አዲስ በተከፈቱት ጣቢያዎች እንደ ታክሲ ትራንስፖርት እየጫነና እያራገፈ የሚያሳፍር ባቡር (ኮሚተር ትሬይን) አገልግሎት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የተከፈቱት ጣቢያዎች ኅብረተሰቡ አማራጩን እንዲጠቀም ከሚል ሐሳብ የቀረበ እንጂ፣ ለትርፍ ተብሎ የቀረበ እንዳልሆነ ጥላሁን (ኢንጂነር) አስታውቀዋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ እንዳስታወቁት፣ መንግሥት በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ውስጥ ከአዲስ አበባ-ጂቡቲ ያለውን የባቡር መስመር በማስፋትና ተጨማሪ የባቡር ማቋረጫ መስመሮችን በመዘርጋት፣ ከሌሎች የጎረቤት አገሮች የባህር ወደብ ጋር በማቀራረብ የባቡር መስመር ኔትወርኩን 4,000 ኪሎ ሜትር ለማድረስ አቅዷል፡፡ ይህ ሲሆን የአገሪቱን የሎጂስቲክስ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምርና አገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የምትጫወተውን ሚና የሚያሳድግ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ በሻገርም መንግሥት የባቡር መሠረተ ልማት ሥራውን ሪፎርም በማድረግ  የግሉ ሴክተር እንዲገባ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚተገበሩ የተጠቀሰ ሲሆን ይህም የዘርፉን ቅልጥፍና፣ ዘመናዊነት፣ የገቢ አማራጭና አዋጭነትን በማሳደግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚደግፍ ተመላክቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች