Monday, March 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ታላቁን ግድብ የገነባ ትውልድ በአገር ጉዳይ መነጋገር አያቅተውም!

የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ሲበሰር፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተፈጠረው የዘመናት ቁጭት የተላበሰ ወደር የሌለው ደስታ ነው፡፡ ይህ ደስታ ወደ ውስጥ የሚፈስ ዕንባን ዋጥ የሚያስደርግ ብቻ ሳይሆን፣ ተባብሮ መሥራት ከተቻለ ተዓምር መፍጠር የሚያስችል ዕምቅ አቅምን የሚያወጣ እልህ ጭምር የተላበሰ ነው፡፡ ይህ እልህ የዓባይ ውኃ ለዘመናት ለምን ሲፈስ ዝም ብለን ስናየው ኖርን አሰኝቶ፣ በርካታ ግድቦችን ለመገንባት ምንም የሚሳን ነገር እንደሌለም ማሳያ ነው፡፡ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ለምን ጨለማ ውስጥ ሆነው የድህነት መጫወቻ ሆኑ የሚለው የዘመናት ቁጭት፣ ‹‹ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል›› ከሚለው ዕድሜ ጠገብ ምሳሌያዊ አባባል ጋር ማክተም ይኖርበታል፡፡ ለሥራ ታጥቀው የተነሱ እጆችና አዕምሮዎች የኢትዮጵያን የዘመናት ዋይታዎች በመቀየር፣ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አልፋ እስከ መካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓ ድረስ የኃይል ቋት ማድረግ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የጀመረችው ቆራጥ ተነሳሽነት በዚህ ግለት ከቀጠለ፣ ድህነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመገላገል የሀብት ማማን መቆጣጠር አያዳግትም፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ፣ ለኢትዮጵያውያን አንድነት ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ዳግማዊ ዓድዋ ሊባል የሚችል ታላቅ ገድል በማከናወናቸው በጣም ሊደሰቱ ይገባል፡፡ ከግድቡ ዕቅድ ጀምሮ እስከ የመጀመሪያው ኃይል ማመንጨት ድረስ አስተዋጽኦ ላደረጉ ወገኖች በሙሉ፣ ታላቅ ክብርና ምሥጋና መቅረቡ ተገቢ ነው፡፡ የዘመናት የቁጭትና የብሶት ምንጭ የነበረው ዓባይ ወንዝ ተገርቶ፣ ለአገር የድል ብሥራት ሲሰማ ይህ ትውልድ ሊኮራ ይገባል፡፡ ከመኩራት ባሻገርም ኢትዮጵያን ከድህነት ወደ ባለፀጋነት ለሚያሸጋግሩ የወደፊት ታላላቅ ፕሮጀክቶች ዕቅድና አፈጻጸም መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሚያምርባቸው በአንድነት ቆመው አገራቸውን ሲያበለፅጉ እንጂ፣ ድህነት ውስጥ ሆነው እርስ በርስ ሲተናነቁ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ከድህነት መንጥቆ የማያወጣ የፖለቲካ አጀንዳም ሆነ ሌላ ትርክት መቆም አለበት፡፡ ልዩነት ለጋራ ዕድገት የሚበጁ የተሻሉ ሐሳቦች የሚፈልቁበት እንጂ፣ ንፁኃን ለዕልቂት የሚዳረጉበትና የደሃ አገር አንጡራ ሀብት የሚወድምበት የሴረኞች መሣሪያ መሆን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአስመራሪው ድህነት ውስጥ መንጥቆ የሚያወጣቸው፣ በእኩልነትና በነፃነት የሚያኖራቸው ሥርዓት ግንባታ ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡ አንድ ላይ የኖረን ሕዝብ በተልካሻ ልዩነቶች በማጣላት ማፋጀት ለዘመኑ የማይመጥን የፖለቲካ ቁማር ነው፡፡ የሚያዋጣው በኅብረት እየተደጋገፉ ማደግ ነው፡፡

በዚህ ታሪካዊ ወቅት መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ባለሙያዎችና እያንዳንዱ አገር ወዳድ ዜጋ የአገር ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም የሚከበረው በአንድነት በመቆም ብቻ እንደሆነ ሊረዱ ይገባል፡፡ አሁን ከአገር ህልውና በፊት የሚቀድም ምንም ነገር እንደሌለ በመረዳት፣ ሙሉ ጊዜያቸውን ለኢትዮጵያ ደኅንነትና ጥቅም ብቻ ሙሉ መሰዋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከድህነት ካልወጣች ማንም አያከብራትም፡፡ በዓለም አደባባይ ተደማጭነት የሚገኘው በተባበረ ክንድ ከድህነት በመውጣት ብቻ ነው፡፡ ውስጣዊ ችግሮችን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ ምክክር በመፍታት፣ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቅ መረባረብ የግድ ነው፡፡ ይህ ግድብ በግብፅም ሆነ በሌሎች ኃይሎች ተንኮል ተደናቀፈ ማለት ለኢትዮጵያውያን ውርደት ነው፡፡ ግድቡ በየተራ ተርባይኖቹ ተንቀሳቅሰው የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ፣ አስፈላጊው መስዋዕትነት መከፈል አለበት፡፡ ግብፅም ሆነች ሌሎች ኃይሎች የኢትዮጵያን አንገት ለማስደፋት ብዙ ሙከራዎች ስለሚያደርጉ፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሙከራዎቹን ማክሸፍ የሚችሉት ውስጣዊ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መልክ ለማስያዝ ሲተባበሩ ብቻ ነው፡፡ በጠላት ፊት እርስ በርስ የመበላላት አሳፋሪ የታሪክ ምዕራፍ መዘጋት ይኖርበታል፡፡ የህዳሴ ግድብ ትሩፋትን ከአፍሪካውያን ጋርም ሆነ ከሌሎች ጋር ከመጋራት በፊት፣ እርስ በርስ ለመስማማት ጥረት ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ አፅንኦት የተሰጠው አንድ ቁምነገር አለ፡፡ ይኸውም ግድቡ በታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ ይህ ነው የሚባል ጉልህ ጉዳት ሳያደርስ ተገንበቶ መጠናቀቁ ነው፡፡ ይህንን ታላቅ ግድብ የአሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት በተጨማሪ ለዓሳ ዕርባታ፣ ለቱሪዝምና ለመዝናኛ ከመጠቀም ውጪ የውኃውን ፍሰት ለመግታት ፍላጎት እንደሌለ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ የዓባይን ውኃ በቅኝ ግዛት ስምምነት ሳይሆን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በእኩልነት ለመጠቀም የቀረበው ሐሳብ፣ በተለይ በግብፅ በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳና በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያን ሰላም የመንሳት እኩይ ድርጊት የተፈጸመበት ነው፡፡ ሱዳን ከግድቡ ተጠቃሚ መሆኗን በተደጋጋሚ ከገለጸች በኋላ ከሐሳቧ እንድታፈገፍግ የተደረገው፣ በግብፅና ከእሷ ጀርባ በተሠለፉ ኃይሎች ግፊት ነው፡፡ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የበለጠ ጫና እንድትፈጥር ታስቦም፣ በሰላማዊ መንገድ መፈታት ያለበትን የድንበር ጉዳይ በመተላለፍ ወረራ የፈጸመችውም በዚህ የሴራ አካል ነው፡፡ ብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን ይህንን አፍጦና አግጥጦ የወጣ ተንኮል በመረዳት ለግድቡ ግንባታ ስኬት የሚፈለግባቸውን ሁሉ ሲወጡ፣ ጥቂቶች ግን እያወቁም ሆነ ሳያውቁ አገራቸውን ችግር ውስጥ ከተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሴራ ፖለቲካ ሳቢያ የደረሰባት መከራ ገና አልተገፈፈም፡፡ አሁንም የዚያ ሴራ አካል የሆነ ጦርነት መሀል ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያ መከራ ሊያበቃ የሚችለው ግን የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሰላማዊ መንገድ መነጋገር ሲችሉ ነው፡፡ የአገራዊ ምክክሩ ኮሚሽን ሁሉንም ወገኖች አስማምቶ በዘርፈ ብዙ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር፣ ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልገው ቅን ልቦና ነው፡፡ ይህ ቅን ልቦና ሥልጣንና ጥቅምን የሚያስቀድም ሳይሆን፣ መተኪያ የሌላትን አገር ዘለቄታዊ ህልውና ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያውያን በእኩልነት መብታቸውና ነፃነታቸው ተከብሮ የሚኖሩባት አገር ጥቅምና ደኅንነት መቅደም አለበት፡፡ በአገራዊ ምክክሩ መደመጥ አለብን የሚሉ ወገኖች ሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ መስተናገድን ማስቀደም አለባቸው፡፡ አንዱ ሰጪ ሌላው ተቀባይነት የሆነበት አሠራር ሳይሆን፣ ሁሉም ወገኖች ተሳትፎ የሚያደርጉበት እንዲሆን አዎንታዊ አስተዋፅኦ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የልመና አኩፋዳዋን ጥላ ለሥራ ታጥቃ መነሳት የምትችለው፣ ከጉልበት ይልቅ ለትብብር ትኩረት ሲሰጥ ነው፡፡ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመሳሰሉና ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶችን ዕውን ለማድረግ፣ በእኩልነትና በመግባባት ተቀምጦ ለመነጋገር ፈቃደኝነት መኖር አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ያስፈልጋታል፡፡ ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ውድመት እንጂ ልማት አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ ጦርነት ውስጥ በመቆየቷ ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ደርሶባታል፡፡ ለልማት መዋል የሚገባው የሰው ኃይልና ሀብት ለጥፋት በመዋሉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር ተዳርጓል፡፡ ጦርነቱ ካደረሰው ዕልቂትና ውድመት በተጨማሪ፣ አስከትሎት የመጣው የኑሮ ውድነት ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱን በማስወገድ የተትረፈረፈ ሀብት ማፍራትና በሰላም መኖር የሚቻለው፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በእኩልነት ለብሔራዊ ምክክሩ ከፍተኛ ትኩረት ሲሰጡ ነው፡፡ እንደ ህዳሴ ግድቡ የመሳሰሉና ሌሎች ፕሮጀክቶችን በሰከነ መንገድ ማቀድ የሚቻለው፣ በብሔራዊ ጉዳዮች በሀቅ ላይ የተመሠረተ ምክክር ለማድረግ ዝግጁነት ሲኖር ነው፡፡ ከሥልጣንና ከጥቅም በላይ ኢትዮጵያን የሚያስቀድም ዝግጅት ሲኖር፣ ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን በማለት ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገርም ሆነ መመካከር አያቅትም፡፡ ግዙፉን ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአንድነት መገንባት የቻሉ ኢትዮጵያውያን፣ በብሔራዊ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ መመካከር አያቅታቸውም፡፡ ይህ ትውልድ ደግሞ ታላቅ ኃላፊነት አለበት!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

በሰባት የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተሰማ

በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ተወስኗል ከ1.4 ቢሊዮን...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...