Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በግማሽ ሒሳብ ዓመት ከ1.16 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ያስመዘገበው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በ2014 ግማሽ የሒሳብ ዓመት ከ51 በመቶ በላይ ብልጫ ያለው ትርፍ ማስመዝገቡንና በግማሽ ዓመቱ አገኛለሁ ብሎ ካቀደው ገቢ 98.5 በመቶውን ማሳካት መቻሉን ገለጸ፡፡

ባንኩ 2014 ግማሽ የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን በማስመልከት ይፋ ባደረገው መረጃ፣ በሒሳብ ዘመኑ አሳካቸዋለሁ ብሎ የያዛቸውን ዕቅዶች በጥሩ አፈጻጸም በማጠናቀቁ፣ በኢንዱስትሪው በከፍተኛ ትርፋቸው ከሚጠቀሱ ባንኮች መካከል ‹‹እንድሠለፍ አድርጎኛል›› ብሏል፡፡

የባንኮች የግማሽ ዓመት ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት እንደሚያመለክተው በግማሽ ዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ካስመዘገቡ ሰባት ባንኮች አንዱ የሆነው

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 1.16 ቢሊዮን ብር ያተረፈ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ የትርፍ ምጣኔ ከቀዳሚው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ51 በመቶ ዕድገት ያለው መሆኑን የባንኩ ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ባንኩ በ2013 የመጀመርያ ግማሽ የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት አስመዝግቦት የነበረው ትርፍ 738 ሚሊዮን ብር እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በ2014 ግማሽ የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ሀብት 57 ቢሊዮን ብር ማድረሱንም ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑንም 43 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን የሚጠቅሰው  መረጃው፣ የተከፈለ ካፒታል መጠኑን ደግሞ 4.5 ቢሊዮን ብር ያደረሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ዘመናዊ የሚባለውንና የቅርብ ጊዜ ሥሪት የሆነውን T24 ኮር ባንኪንግ ሲስተም ሥራ ላይ ማዋሉን በዚሁ መረጃው ላይ አስታውቋል፡፡

‹‹ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በአገራችን የባንክ ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ የሚያደርገውን የዘመኑ ቴክኖሎጂ የደረሰበትና የቅርብ ጊዜ ሥሪት የሆነውን T24 R20 ኮር ባንኪንግ ሲስተም ሥራ ላይ አውሏል፤›› የሚለው የባንኩ መረጃ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሠራሩን በማዘመንና የአገልግሎት አድማሱን ማስፋፋቱን ገልጿልሸ፡ አገልግሎቶቹን ለደንበኞችና ለተገልጋዮች ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ ቀደም ሲል ይጠቀምበት የነበረውን T24-R10 ወደ T24-R20 ማሳደጉን የሚገልጸው የባንኩ መረጃ በተጨማሪም የተለያዩ መሠረተ ልማቶችና የዲጂታል ባንኪንግ አሠራርን በዘመናዊ መልኩ ለመዘርጋት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ይህንን ቴክኖሎጂ ቀዳማይ ለማድረግ በተካሄደው እንቅስቃሴ ያጋጠመው የኔትወርክ ችግር በማቃለል ግንባር ቀደም ባንክ ለመሆን ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠሉንም በመጥቀስ፣ ባንኩ ከምንጊዜውም በተሻለ ሁኔታ ለደንበኞች የተሟላ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዋና መሥሪያ ቤቱን ማራኪና ውብ ባለ 32 ወለል ሕንፃ ገንብቶ ሥራ ላይ ያዋለ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ የክልል ከተሞች በዱከም፣ በወልቂጤ፣ በሆሳዕናና በሐዋሳ እንዲሁም በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ዘመናዊ ሕንፃዎችን በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃቱንም አስታውቋል፡፡

ባንኩ በአሁኑ ወቅት ከ400 በላይ ቅርንጫፎች፣ እንዲሁም ከ7,448 በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡

ከ23 ዓመታት በፊት ባንኩ ሲቋቋም 717 ባለአክሲዮኖችን ይዞ እንደነበር ይታወሳል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች